MAP

ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ሪኖ ፊዚኬላ የወጣቶች ኢዮቤልዩ በዓልን በማስመልከት በቫቲካን መግለጫ የሰጡበት ሥነ-ሥርዓት  ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ሪኖ ፊዚኬላ የወጣቶች ኢዮቤልዩ በዓልን በማስመልከት በቫቲካን መግለጫ የሰጡበት ሥነ-ሥርዓት   (@Vatican Media)

የወጣቶች ኢዮቤልዩ፥ በዓለም ውስጥ ሰላምን ለመገንባት አንድ እርምጃ እንደሚሆን ተገለጸ

ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ሪኖ ፊዚኬላ፥ በቅድስት መንበር የስብከተ ወንጌል አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ረዳት ሃላፊ፥ ከሰኞ ሐምሌ 21-25/2017 ዓ. ም. ድረስ የሚከበረውን የወጣቶች ኢዮቤልዩ በዓል በማስመልከት ማብራሪያ ሰጥተዋል። አቡነ ሪኖ ፊዚኬላ በማብራሪያቸው፥ በዓሉ የዓለም ወጣቶች በኅብረት ሆነው የሚያከብሩት፣ በጦርነት ቀጣና የሚኖሩት ወጣቶችንም በማሳተፍ በዓለም ውስጥ ሰላምን ለመገንባት አንድ እርምጃ እንደሚሆን አስረድተዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በኢዮቤልዩ የተስፋ ዓመት ካቶሊካዊ ተጽዕኖ ፈጣሪዎች እና የዓለም ወጣቶች በኅብረት ከሰኞ ሐምሌ 21-25/2017 ዓ. ም. ድረስ የሚያከብሩት በዓሉ መድብለ-ባህላዊ እና ልዩ ልዩ ሁነቶች የሚቀርቡበት መሆኑን ሊቀ ጳጳስ አቡነ ሪኖ ፊሲኬላ ከበዓሉ ቀደም ብሎ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ገልጸዋል።

ሊቀ ጳጳስ ሪኖ ፊሲኬላ በመግለጫቸው፥ ከመላው ዓለም የተወጣጡ ወጣቶች ወደ ሮም መጥተው የሚሳተፉበት ይህ በዓል ምናልባትም በዓመቱ ውስጥ እጅግ ሲጠበቅ የቆየ እንደሆነ ገልጸዋል። ለአንድ ሳምንት በሚቆይ በዚህ በዓል ላይ 146 ሀገራትን የሚወክሉ ወጣቶች እንደሚሳተፉ፥ ከእነዚህም መካከል 78 በመቶ የሚሆኑት ከአውሮፓ ሀገራት፥ የተቀሩት 22 በመቶዎቹ ግጭት ውስጥ ካሉ እንደ ኢራቅ፣ ደቡብ ሱዳን እና ሊባኖስ የሚመጡትን ጨምሮ የመላው ዓለም ወጣቶች የሚሳተፉበት መሆኑን አስረድተዋል።

ሊቀ ጳጳስ ሪኖ ፊሲኬላ በማከልም፥ “በዋነኛነት ይህ በዓል የደስታ እና ከዓለም ዙሪያ የሚመጡ ወጣቶችን እንዲያቅፍ ለማድረግ የታሰበ፥ እውነተኛ የሰላም ጊዜ እና በዓለማችን ሰላምን ለመገንባት የሚያስችል እርምጃ ምልክት ነው” ሲሉ አብራርተዋል።

በመቶ ሺዎች ለሚቆጠሩት የተከፈቱ በሮች

“ሐምሌ 21/2017 ዓ. ም. ቢያንስ ግማሽ ሚሊዮን የሚሆኑ ወጣቶች ወደ ሮም እንደሚደርሱ ይጠበቃል” ያሉት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ሪኖ ፊሲኬላ፥ ይህ ትልቅ ትርጉም ያለው ቁጥር እንደሆነ ገልጸው፥ የኢዮቤልዩ በዓላቸውን ለማክበር ወደ ሮም የሚመጡትን በሺዎች የሚቆጠሩ ወጣቶችን ተቀብሎ ለማስተናገድ 370 ቤተ ክርስቲያናት፣ 400 ትምህርት ቤቶች እና በርካታ ቤተሰቦች በሮቻቸውን ከፍተው እንደሚጠብቁ አስረድተዋል።

እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ 2000 ዓ. ም.  በ “ቶር ቬርጋታ” ዓለም አቀፍ የወጣቶች ቀን ሲከበር
እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ 2000 ዓ. ም. በ “ቶር ቬርጋታ” ዓለም አቀፍ የወጣቶች ቀን ሲከበር

የበዓሉ አስተባባሪዎች ለወጣቶቹ ምግብ የሚቀርብበትን ዘዴ ጨምሮ በሁሉም ረገድ ዝግጅቶችን ሲያደርጉ መቆየታቸውን፣ በከተማዋ ከሚገኙ 3,500 ምግብ ቤቶች በተጨማሪ  20 የምግብ ማደያ ጣቢያዎች እንደሚኖሩ፣ የተመዘገቡ ወጣቶች ምሳ እና እራት የሚያገኙበትን ዕድል እንዳመቻቹ፥ ቁርሳቸው ደግም በየመጠለያ ጣቢያዎቻቸው እንደሚዘጋጅላቸው እና የሚፈልጉ ከሆነ ከጤናቸው ጋር ተስማሚ የሆኑ ምግቦችን የማግኘት አማራጮች መኖራቸውን ሊቀ ጳጳስ አቡነ ሪኖ ፊሲኬላ ጠቁመዋል።

ጠንካራ የእምነት፣ የመዝናኛ እና የጓደኝነት ሳምንት

ወጣቶች ከሮም ከተማ ጋር በሚደርጉት ግንኙነት የሚጀምረው የአንድ ሳምንት የወጣቶች ኢዮቤልዩ በዓል፥ በሦስት የሳምንቱ ቀናት ማለትም ማክሰኞ፣ ረቡዕ እና ሐሙስ በሮም ዙሪያ በሚገኙ የተለያዩ አደባባዮች የሚካሄዱ 70 ልዩ ልዩ ዝግጅቶችን የሚያካትት ሲሆን፥ የዝግጅቶቹ አስተባባሪዎችም ማኅበራት፣ ቡድኖች እና የጳጳሳት ጉባኤዎች እንደሆኑ ተገልጿል።

በሮም አደባባዮች ከሚቀርቡ ዝግጅቶች መካከል “Duc in Altum” የተሰኘ የቲያትር ቡድን በከተማው ጎዳናዎች እየዞረ የሚያሳየው የሊዚዩ ቅድስት ቴሬዛ የሕይወት ታሪክ አንዱ እንደሚሆን ይጠበቃል። “ካሪታስ” በተሰኘ ዓለም አቀፍ ካቶሊካዊ የዕርዳታ ድርጅት ተልዕኮ ውስጥ የተሳተፉ ወጣቶችን የሚያሳይ የቪዲዮ ቅንብር እና “Mary's Meals” የተባለ የበጎ አድራጎት ድርጅት በዓለም ዙሪያ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሕጻናትን ከድህነት ለማላቀቅ የሚያደርገውን ሥራ በማስመልከት የዘጋጀው የውይይት መድረክ እንደሚቀርብ ተነግሯል።

በዕለቱ ፍፃሜ በአገሩ አቆጣጠር ከምሽቱ አንድ ሰዓት ላይ ወጣቶችን በይፋ ለመቀበል ታስቦ የተዘጋጀ የመስዋዕተ ቅዳሴ ሥነ-ሥርዓት በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ የሚቀርብ ሲሆን፥ ዓርብ ሐምሌ 25/2017 ዓ. ም. በ “Circus Maximus” አደባባይ በተተከሉ ድንኳኖች ውስጥ 200 የሚያህሉ ካህናት በሺዎች የሚቆጠሩ ወጣቶችን ንስሐ የሚያስገቡበት ሥነ-ሥርዓትም ተዘጋጅቷል።

እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ 2000 ዓ. ም. የዓለም ወጣቶች ቀን በተከበረበት “ቶር ቬርጋታ” ሰፊ ሜዳ ላይ ቅዳሜ ሐምሌ 26/2017 ዓ. ም. ምሽት ትልቅ የጸሎት ዝግጅት የሚካሄድ ሲሆን፥ በመቶ ሺዎች ሚቆጠሩ ወጣቶች በሚሳተፉበት በዚህ የጸሎት ሥነ-ሥርዓቱ ላይ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ተገኝተው ሥነ-ሥርዓቱን እንደሚመሩት እና በሥነ-ሥርዓቱ ላይ ከሜክሲኮ፣ ከዩናይትድ ስቴትስ እና ከጣሊያን የመጡ ሦስት ወጣቶች ለቅዱስነታቸው ጥያቄዎችን እንደሚያቀርቡ ይጠበቃል።

እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በያዝነው የተስፋ ዓመት የሚከበረው ይህ የዓለም ወጣቶች የኢዮቤልዩ በዓል ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ እሁድ ሐምሌ 27/2017 ዓ. ም. በሚመሩት የመስዋዕተ ቅዳሴ ሥነ-ሥርዓት የሚጠናቀቅ መሆኑን የበዓሉ መርሃ-ግብር ያመለክታል።

24 Jul 2025, 14:07