“በዓለም አቀፍ ግዴለሽነት ምክንያት በሕዝብ ላይ ጥቃት እየተፈጸመ ይገኛል!”
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
የጥቃቱን ክብደት የሚያሳዩ ምስሎችን ዋቢ አድርጎ አስተያየቱን የገለጸው አንድሬያ ቶርኔሊ፥ ከእስራኤል የጦር ታንክ በቀጥታ የተሰነዘረው ተኩስ፥ በጋዛ ብቸኛ በሆነው የቅድስት ቤተሰብ ካቶሊካዊ ካቴድራል ላይ ጉዳት ማስከተሉ ታውቋል።
የእስራኤል ጦር ሠራዊት በጋዛ በሚፈጽመው ጥቃት መኖሪያቸው የወደመባቸው አምስት መቶ ሰዎች ሁለት ቤተ ክርስቲያኖች እና አንድ ትምህርት ቤት በሚገኝበት ቅጥር ግቢ ውስጥ ለሁለት ዓመታት ያህል ተጠልለዋል።
ጋዛ ውስጥ በሚገኝ ብቸኛው የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ላይ የእስራኤል ጦር ሐሙስ ሐምሌ 10/2017 ዓ. ም. ማለዳ በከፈተው ተኩስ የቁምስናው መሪ ካህን አባ ገብርኤል ሮማኔሊን ጨምሮ አሥር ሰዎች ሲቆስሉ ሦስት ሰዎች ተገድለዋል።
ከተጎዱት መካከል አንዱ፥ “ሎዜርቫቶሬ ሮማኖ” ለተሰኘ የቅድስት መንበር ዕለታዊ ጋዜጣ ጽሑፎችን የሚያቀርብ ወጣት ሱሃይል ይገኝበታል።
ወጣት ሱሃይል “ፍቅር ከጦርነት የበለጠ ጠንካራ ነው” በሚል ርዕሥ ሐምሌ 1/2017 ዓ. ም. ለጋዜጣው የሚከተለውን ጽሑፍ ልኮ ነበር።
“ይቅርታን እና እርቅን በማድረግ በጋዛ ብቻ ሳይሆን በመላው ዓለም አንድ ቀን ሰላም እንዲወርድ እንጸልይ፤ ምክንያቱም ፍቅር ከጦርነት የበለጠ ጠንካራ ነው” ብሏል
የተፈጸመው ጥቃት ስህተት መሆኑን ተገንዝበው የእስራኤል ባለስልጣናት ይቅርታ ጠይቀዋል። እስራኤል የአምልኮ ቦታዎችን እንደምታከብር እና በድርጊቱ ላይ ምርመራ እንደሚካሄድም ገልጸዋል።
እንደዚህ ያሉ መግለጫዎች ተፈጻሚነትን ማመን አይቻልም። መስጊዶች ወደ ፍርስራሽነት መቀየራቸውን እና በአብያተ ክርስቲያናት ላይ የሚሰነዘረውን ጥቃት ስለሚቃረኑ ብቻ ሳይሆን፥ ለምሳሌ በቅዱስ ፖርፊሪየስ ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን ላይ በተደረገው ወረራ የበርካታ ሰዎች ሕይወት ጠፍቷል። ነገር ግን ከአንድ ዓመት ተኩል በኋላ በጋዛ በሚገኝ ቁምስና ውስጥ በተፈጸመ ተኩስ በተገደሉ ሁለት ክርስቲያን ሴቶች ላይ በተደረገው ምርመራ እስካሁን ምንም ውጤት አልተገኘም።
በዚህ ረገድ በተለይ በጣሊያን የእስራኤል አምባሳደር ጆናታን ፔሌድ፥ “ሲቪል ተቋማትን በአደጋ ላይ የመጣል ዓላማ የለንም፤ ነገር ግን በሚያሳዝን ሁኔታ አሸባሪዎች እንደ ትምህርት ቤቶች እና የአምልኮ ቦታዎችን በመሳሰሉ ሁሉም ቦታዎች ጭምር ይገኛሉ” በማለት ተናግረዋል።
የእነዚህ ዓረፍተ ነገሮች አስገራሚነት፥ “ስህተት ነው” ተብሎ የተገለጸውን አውድ ስለሚያቀርቡ ነው። አምስት መቶ ንጹሃን ሰዎች፥ አብዛኞቹ በመደበኛነት ለመቁጠርያ ጸሎት የሚሰበሰቡ ነበር። ነገር ግን ሳያውቁ የጥቃቱ ዒላማ ሆነዋል። ምክንያቱም አምባሳደር ፔሌድ እንዳሉት፥ “እነዚህ አንዳንድ ጊዜ የጦርነት ውጤቶች ናቸው”።
የቫቲካን ዜና አንባቢዎች እና አድማጮች በሚገባ እንደሚያውቁት፥ በጋዛ በየቀኑ በደርዘን የሚቆጠሩ ንጹሐን ሕጻናት፣ ሴቶች እና ወንዶች ይገደላሉ።
ጋዛ ውስጥ በየቀኑ የሚገደሉ ክርስቲያኖችን ሳንጨምር አስተማማኝ የምግብ ዕርዳታን ማረጋገጥ በሚገባቸው ሰዎች በየሳምንቱ በርካታ ሰዎች ይገደላሉ።
ዛሬ ጋዛ ውስጥ ጉዳት የሚደርስባቸውን ሰዎች በማስመልከት የምንዘግበው ተጎጂዎቹ ክርስቲያን ስለሆኑ ወይም ሱሃይል ስለተጎዳ አይደለም።
ሁሉም ንጹሐን ተጎጂዎች ወደ እግዚአብሔር ፊት ቀርበው ድምጾቻቸውን ስለሚያሰሙ፥ እያንዳንዱ ሕይወት የተቀደሰ በመሆኑ እና በጋዛ ውስጥ የሚገኙ የየትኛውም ቤተ እምነት ተከታዮች የፍልስጤም ሕዝብ ዕጣ ፈንታ በሁሉም ነገር ይካፈላሉ።
እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ጥቅምት ወር 2023 ዓ. ም. የሐማስ አሸባሪዎች በእስራኤል ላይ ያደረሱትን ኢ-ሰብዓዊ ጭፍጨፋ ቅድስት መንበር በማያሻማ ቃል አውግዛው፥ ሁሉም ታጋቾች እንዲፈቱ እና እስራኤል ራሷን የመከላከል መብት እንዳላት ታምናለች።
ይሁን እንጂ በብዙ ንጹሐን ዜጎች ላይ የተፈጸመው ኢ-ሰብዓዊ ግድያ የ60,000 ሰዎችን ሞት እና የከተሞችን መውደም ትክክለኛነት ሊያረጋገጥ አይችልም። ያላዩ የሚመስሉ የብዙ ሰዎች ዝምታን እና እልኽኝነት ሊያረጋገጥ አይችልም።
እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ሰኔ 26/2025 ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ለምሥራቅ አብያተ ክርስቲያናት ዕርዳታን ለሚያቀርቡ ድርጅቶች (ROACO) የተናገሯቸውን ቃላት በመድገም፥ የዚህን ጦርነት ሞኝነት ማውገዝ የማይታክተው ለዚህ ነው።
ሁላችንም የማጭበርበር ንግግሮችን እና የሐሰት ዜናዎችን ወደ ብርሃን ለማውጣት ጥረት እንድናደርግ፣ ዓለም አቀፍ ግዴለሽነትንም እንድናሸንፍ፣ በመካከለኛው ምሥራቅ ያለውን ሁኔታ እና የጦርነት መባባስን በተጨባጭ እንድንመለከት ተጠርተናል።
ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ባዘጋጃቸው የሕግ መሣሪያዎች አማካይነት ጣልቃ ለመግባት ድፍረቱን የምንቀዳጅበት፣ የጦር መሣሪያዎችን ዝም ለማሰኘት፣ ጭፍጨፋን ለማስቆም እና በሺዎች የሚቆጠሩ ንፁሃን ዜጎችን ዋጋ የሚያስከፍል የሃይል ጨዋታዎችን የምናስቆምበት ጊዜ አሁን ነው።