የተቀደሰ እና የሐዋርያዊ ሕይወት የሚኖሩ ማኅበራት የሚመለከተው የቅድስት መንበር ዋና ጽ/ቤት
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን
ይህ የተቀደሰ እና የሐዋርያዊ ሕይወት የሚኖሩ ማኅበራት የሚመለከተው የቅድስት መንበር ዋና ጽ/ቤት "የተቀደሰ ሕይወት ተቋማት እና ሐዋርያዊ ሕይወት የሚኖሩ ማኅበራት ክርስቶስን በመከተል የማኅበሮቻቸው መስራች መንፈስ በመከተል እና ከጤናማ ወጎች መንፈስ ጋር በሚጣጣም መልኩ ክርስቶስን በመምሰል መንፈሳዊ ሕይወት እንዲያደርጉ ለማረጋገጥ ይሰራል፣ በታማኝነት የራሳቸውን ዋና መንፈሳዊ ግብ እንዲያሳድዱ እና ቤተ ክርስቲያንን ለመገንባት እና በዓለም ላይ ለምትሰጠው ተልዕኮ በብቃት አስተዋጽዖ ያበረክታሉ" ሲሉ የቀድሞ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በላቲን ቋንቋ "Praedicate Evangelium" (ወንጌልን ስበኩ) በተሰኘው ሐዋርያዊ ማሳሰቢያቸው ላይ መግለጻቸው ይታወሳል።
የተቀደሰ እና የሐዋርያዊ ሕይወት የሚኖሩ ማኅበራት የሚመለከተው የቅድስት መንበር ዋና ጽ/ቤት የተቋቋመው እ.አ.አ በ1586 ዓ.ም በወቅቱ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት በነበሩት ሲክሱስ አምስተኛ ሲሆን ይህንንም ይፋ የደረጉት በላቲን ቋንቋ "Sacra Congregatio super consultibus regularium" በአማርኛው በግርድፉ ሲተረጎም (የተቀደሰ ሕይወት የሚኖሩ ማኅበራትን የሚመለከት መደበኛው ምክር ቤት) በሚል መጠሪያ ተቋቋመ። የአሁኑ የተቀደሰ እና የሐዋርያዊ ሕይወት የሚኖሩ ማኅበራት የሚመለከተው የቅድስት መንበር ዋና ጽ/ቤት አስተዳዳሪ ሲስተር ሲሞና ብራምቢላ ናቸው።
ኃላፊነት እና የሥራ ድርሻ
የተቀደሰ እና የሐዋርያዊ ሕይወት የሚኖሩ ማኅበራት የሚመለከተው የቅድስት መንበር ዋና ጽ/ቤት የተለያዩ የኃላፊነት ቦታዎች አሉት። በሮማን ኩሪያ በላቲን ቋንቋ "Praedicate Evangelium" (ወንጌልን መስበክ) በተሰኘው ሐዋርያዊ ማሳሰቢያ እና ሕገ ደንብ ላይ እንደተገለጸው፣ “የተቀደሰ ሕይወት ተቋማትን እና የሐዋርያዊ ሕይወት የሚኖሩ ማኅበራትን እውቅና መስጠት፣ እነሱን ማቋቋም እና እንዲሁም የሀገረ ስብከቱ ሐዋርያዊ ሕይወት ማኅበር ተቋም በጳጳስ በኩል እንዲቋቋም ፈቃድ መስጠትን የሚመለከት ነው"።
“የተቀደሰ ሕይወት ተቋማት እና ሐዋርያዊ ሕይወት የሚኖሩ ማኅበራት እንዲዋሃዱ፣ አንድነት እንዲፈጥሩ ማድረግ እና አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ፈቃዳቸውን መሻር እንዲሁ የጽ/ቤቱ የሥራ ድርሻዎች ናቸው።
“ጽ/ቤቱ ቀደም ሲል በሕግ ዕውቅና የተሰጣቸውን የተቀደሱ የሕይወት ዓይነቶችን ለማጽደቅ እና ለመቆጣጠር ኃለፊነት ተሰጥቶታል" ።
"የማኅበራት፣ ጉባኤዎች፣ እና የተቀደሰ ሕይወት እና ሐዋርያዊ ሕይወት ማኅበራት ሕብረት ማቋቋም ወይም መሻር የተቀደሰ እና የሐዋርያዊ ሕይወት የሚኖሩ ማኅበራት የሚመለከተው የቅድስት መንበር ዋና ጽ/ቤት ተግባር" ነው።
ሌሎች የኃላፊነት ጉዳዮች
የተቀደሰ እና የሐዋርያዊ ሕይወት የሚኖሩ ማኅበራት የሚመለከተው የቅድስት መንበር ዋና ጽ/ቤት ሐዋርያዊ መንበር ሐዋርያዊ ሕይወት የሚኖሩ ማኅበራት ሕይወትና እንቅስቃሴን በሚመለከት፣ በተለይም ሐዋርያዊ የሆኑ ሕገ ደንቦችን ማጽደቅንና ማሻሻያዎቻቸውን በሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ የሐዋርያዊ መንበር ብቃት ያላቸውን ጉዳዮች ይመለከታል። የመደበኛ አባላት የሥነ-ምግባር ጉዳይ፣ የተወሰኑ ደንቦችን እና መመሪያዎችን ጨምሮ የአባላትን ውህደት እና ምስረታ ማጽደቅ፣ ጊዜያዊ ንብረቶችን መቆጣጠር እና አስተዳደራዊ ጉዳዮችን መገምገም፣ ሐዋርያዊ እንቅስቃሴያቸውን መከታተል እና ያልተለመዱ የአስተዳደር ጉዳዮች ሲገጥም እርምጃዎችን የመውሰድ ኃለፊነት አለው።
በህግ ደንቡ መሰረት፣ አንድ የማኅበር አባል ወደ ሌላ ፈቃድ የተሰጠው የተቀደሰ ህይወት የሚኖሩ ማኅበራት ማዛወር እና አባላት ከማኅበራቸው በሚባረሩበት ወቅት የሚሰጣቸውን የስንብት ደብዳቤ ይግባኝ በመጠየቅ መርምሮ ውሳኔ መስጠት ጨምሮ በዚህ ጽ/ቤት የኃላፊነት ድርሻ ነው።
እንዲሁም በዓለም አቀፍ ደረጃ የሁሉንም መንፈሳዊ ማሕበራት የበላይ ዋና አለቆች ምክር ቤት ማቁቋም፣ ደንቦቻቸውን ማፅደቅ እና ተግባራቶቻቸው ከትክክለኛው ዓላማቸው ጋር እንዲጣጣሙ ማድረግ የተቀደሰ እና የሐዋርያዊ ሕይወት የሚኖሩ ማኅበራት የሚመለከተው የቅድስት መንበር ዋና ጽ/ቤት ኃላፊነት ነው።
መዋቅር እና አምስቱ ቢሮዎች
የተቀደሰ እና የሐዋርያዊ ሕይወት የሚኖሩ ማኅበራት የሚመለከተው የቅድስት መንበር ዋና ጽ/ቤት አምስት ቢሮዎችን ያቀፈ ነው።
የመጀመሪያው መሥሪያ ቤት ሁሉንም ዓይነት የተቀደሰ ሕይወትን በተለይም የተቀደሰ ሕይወትና ሐዋርያዊ ሕይወት የሚኖሩ ማኅበራትን ሕይወትና እንቅስቃሴ፣ እንዲሁም ማኅበሮቻቸውን ወይም ጉባኤዎቻቸው በዓለም አቀፍ፣ በአህጉር እና በአገር አቀፍ ደረጃ ያስተዋውቃል። በሁለተኛው የቫቲካን ጉባኤ እና በበተክርስቲያን አስተምህሮ መሰረት በቤተክርስቲያኗ ውስጥ ለተቀደሰ ህይወት ሙላት የሚያበረክቱትን ተነሳሽነት እና ሀሳቦችን ያበረታታል እና ይደግፋል።
ሁለተኛው መሥሪያ ቤት የወንድና የሴት ገዳማዊያን ሕይወት ጉዳዮችን በተገቢው ሕግ መሠረት ይመለከታል። ገዳማትን ለመመስረት፣ ለማቋቋም፣ ለማስተላለፍ፣ ለመዋሃድ እና ለመሻር ኃለፊነት የተሰጠው ነው። የገዳማትን ምስረታ፣ ህይወት እና አስተዳደር እንዲሁም የገዳማትን መደበኛ እና መደበኛ ያልሆነ አስተዳደር የሚመለከተውን ሁሉ ይቆጣጠራል።
ሦስተኛው መሥሪያ ቤት የእያንዳንዱን የተቀደሰ እና የሐዋርያዊ ሕይወት የሚኖሩ ማኅበራት ሕይወት በተናጥል ሐዋርያዊ እና መደበኛ የአስተዳደር ሂደት፣ አሠራር እና ከንብረት አስተዳደር ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን ይመለከታል። ወቅታዊ ሪፖርቶችን ይመረምራል፣ መደበኛ እና ለየት ያሉ የሃይማኖት ቤተሰቦች ስብሰባዎችን ያሰናዳል፣ እናም በአጠቃላይ ምዕራፎች ውስጥ የበላይ ምርጫዎችን በተመለከተ ጉዳዮችን ይመለከታል።
አራተኛው መሥሪያ ቤት ለየት ያለ የአስተዳደር እርምጃዎችን ይመለከታል፣ በተለይም የረዳት፣ ሐዋርያዊ ኃላፊነት የተሰጣቸውን የማሕበር አለቆች፣ እና በቅድስት መንበር የሚሰጡትን የስልጣን ሹመትን በሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ ይሰራል። የሀይማኖት ተቋማት አባላት እና የሐዋርያዊ ህይወት የሚኖሩ ማኅበራት መደበኛ ያልሆኑ ሁኔታዎችን ይመለከታል።
አምስተኛው ጽ/ቤት ለሀገረ ስብከቱ የቅድስና ሕይወት የሚኖሩ ተቋማት (የሃይማኖት ተቋማት፣ ዓለማዊ ተቋማት) እና ማኅበራት ሐዋርያዊ ሕይወት ማኅበራት ፈቃድ የመስጠትና የጵጵስና ፈቃድ የመስጠት ኃላፊነት ነው። የተቀደሰ ሕይወት የሚኖሩ አዲስ ዓይነት ማኅበራትን ሁኔታ አይቶ የማጽደቅ እና የመቆጣጠር እንዲሁም የተቀደሰ ሕይወት ወይም የሐዋርያዊ ሕይወት ማኅበር የመሆን ዓላማ ያለው የሕዝብ ማኅበራትን ለማቋቋም የሚቀርቡ ጥያቄዎችን የማጽደቅ ኃላፊነት አለበት። እንዲሁም ነጻ አስተዳደር ያለቸው ማኅበራትን ለማቋቋም እና ለመሻር እንዲሁም ሁሉንም የተቀደሰ ሕይወት እና የሐዋርያዊ ሕይወት የሚኖሩ ማኅበራትን ማሰባሰብ፣ ማኅበር መፍጠር፣ ውህደት እና የመሻር ኃላፊነት አለበት። ጽ/ቤቱ የዓለማዊ ተቋማትን ምስረታ፣ ሕይወት፣ ደንቦቻቸውን እና ሐዋርያዊ አገልግሎታቸውን ይከተላል።
አዲስ ሕይወት
የተቀደሰ ሕይወት አዲስ ሕይወት ነው፣ ከክርስቶስ ጋር በተገናኘ ዕለት ዕለት የሚታደስ ሕይወት፣ በጸሎት ታማኝነት፣ በወንድማማች ፍቅር፣ በድህነት እና ድሆችን በማገልገል የሚኖር ሕይወት ነው። በቤተክርስቲያን ውስጥ ያለ ትንቢታዊ እይታ ነው፥ እግዚአብሔር በአለም ውስጥ እንዳለ የሚያይ እይታ ነው፡ ፍቅሩን የሚያውጅ ድምጽ በታሪክ አስቸጋሪ በሆኑ ሁኔታዎች ውስጥ የሚሰማ ድምጽ ነው።