የክርስቲያን አንድነትን ለማስፋፋት የሚሰራው የቅድስት መንበር ዋና ጽ/ቤት ዓላማ እና የሥራ ድርሻ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን
በቫቲካን የክርስቲያን አንድነትን ለማስፋፋት የሚሰራው የቅድስት መንበር ዋና ጽ/ቤት ተግባር በቤተክርስቲያኗ ውስጥ እውነተኛ የክርስቲያናዊ ሕብረት መንፈስ እድገት እንዲመጣ መሥራት ነው። ከሌሎች አብያተ ክርስቲያናት እና ክርስቲያናዊ ማኅበራት ጋር በወንድማማችነት ግንኙነት፣ በትብብር እና በሥነ መለኮት ውይይቶች ለክርስቲያኖች አንድነት መጠናከር የበኩሉን አስተዋፅዖ ሊያበረክት በሚችል በሁሉም መስክ ንቁ ተሳትፎ የምያደርግ ጽ/ቤት ነው።
አስተዳዳሪው ብፁዕ ካርዲናል ከርት ኮች ሲሆኑ፣ ጸሐፊያቸው ደግሞ ሊቀ ጳጳስ ፍላቪዮ ፔስ ናቸው። ከሌሎች አብያተ ክርስቲያናት እና የክርስቲያን ማህበረሰቦች ጋር ያለው ግንኙነት በሁለት ክፍሎች የሚተዳደር ሲሆን የምስራቃዊ ክፍል ፣ ለኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት የባይዛንታይን ባህል እና ለምስራቅ ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት (ኮፕቲክ ፣ ሲሪያክ ፣ አርሜናዊ ፣ ኢትዮጵያ ፣ ማላንካራ) እንዲሁም ለምስራቅ አሦራውያን ቤተ ክርስቲያን የሚመለከተው የመጀመሪያው ክፍል ሲሆን፣ የምዕራቡ ክፍል፣ ለምዕራቡ ዓለም የተለያዩ አብያተ ክርስቲያናት እና ከክርስቲያን ማህበረሰቦች ጋር የሚሠራው ክፍል ነው።
ታሪካዊ ዳራ
እ.አ.አ በሰኔ 5 ቀን 1960 ዓ.ም ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ 23ኛ የክርስቲያን አንድነትን የምያስፋፋ ጽ/ቤት ከሁለተኛው የቫቲካን ጉባኤ የዝግጅት ኮሚሽኖች አንዱ አድርገው አቋቋሙ። በተወሰነ መልኩ፣ ይህ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ለክርስቲያኖች ሕብረት እንቅስቃሴ ይፋዊ ቁርጠኝነት መጀመሪያ ምልክት ተደርጎ ይቆጠራል። ጽሕፈት ቤቱ ስለ ክርስቲያኖች ሕብረት "ኢኩሜኒዝም" በላቲን ቋንቋ "Unitatis redintegratio" (አንድነትን መመለስ) የተሰኙ ሰነዶችን አዘጋጅቶ ለሁለተኛ የቫቲካን ጉባኤ አቅርቧል። ክርስቲያን ባልሆኑ ሃይማኖቶች ላይ በላቲን ቋንቋ "Nostra aetate" (በእኛ እድሜ) የተሰንኙ ሰነዶችን አዘጋጅቶ ያቀረበ ሲሆን በሃይማኖት ነፃነት ላይ በላቲን ቋንቋ "Dignitatis humanae" (የሰው ልጅ ክብር) በሚል አርዕስት የተጻፈ ሰነድ፣ እና ከእምነት ጋር የተያያዙ አስተምህሮችን ከሚመለከተው ባለስልጣን ጋር በመተባበር በመለኮታዊ ራዕይ ላይ ያለው የዶግማ ሕግጋትን የተመለከቱ በላቲን ቁንቋ "Dei Verbum" (የእግዚአብሔር ቃል) በሚል አርዕስት የተዘግጁ ሰነዶችን ለሁለተኛ የቫቲካን ጉባኤ ማቅረቡ ይታወሳል።
እ.አ.አ በ1966 ዓ.ም ሁለተኛ የቫቲካን ጉባኤ ከተጠናቀቀ በኋላ፣ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ጳውሎስ ስድስተኛ ጽሕፈት ቤቱን የቅድስት መንበር ቋሚ አካል እንዲሆን ማረጋገጫ ሰጥተዋል። በዚያው ዓመት የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት፣ የእምነት እና ሥርዓት ኮሚሽን እና የክርስቲያን አንድነትን የሚያበረታታ ጽ/ቤት ዓመታዊው የክርስቲያን አንድነት የጸሎት ሣምንት ኦፊሴላዊ ጽሑፍን በጋራ ለማዘጋጀት ለመጀመሪያ ጊዜ ወሰኑ።
እ.አ.አ በ1988 ዓ.ም በላቲን ቋንቋ "Pastor Bonus" (መልካም እረኛ) በተሰኘ አርእስት ይፋ በሆነው የሐዋርያዊ መተዳደሪያ ደንብ በወቅቱ የነበሩት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ጽኃፈት ቤቱን የክርስቲያናዊ አንድነትን ለማበረታታት የተቋቋ ጳጳሳዊ ምክር ቤት ወደ ሚል ስያሜ ቀይረውት ነበር። እ.ኤ.አ. በ2022 በላቲን ቋንቋ "Praedicate Evangelium" (ወንጌልን ስበኩ) በተሰኘ አርዕስት የቀድሞ ነፍስኄር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የክርስቲያን አንድነትን ለማስፋፋት የሚሰራ የቅድስት መንበር ዋና ጽ/ቤት ወደ ሚል ስያሜ መጠሪያውን ቀየሩት።
ብቃት እና የሥራ ድርሻ
እ.ኤ.አ. በ2022 በላቲን ቋንቋ "Praedicate Evangelium" (ወንጌልን ስበኩ) በተሰኘ አርዕስት የቀድሞ ነፍስኄር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ይፋ ባደረጉት ሐዋርያዊ ማሳሰቢያ ውስጥ እንደተገለጸው የዚህ ጽ/ቤት ተግባር "በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ እና ከሌሎች አብያተ ክርስቲያናት እና የክርስቲያን ማህበረሰቦች ጋር ባለው ግንኙነት በክርስቲያኖች መካከል ያለውን አንድነት ወደነበረበት ለመመለስ ወቅታዊ በሆኑ የሕብረት ተነሳሽነቶች እና እንቅስቃሴዎች ውስጥ መሳተፍ" (አንቀጽ 142) እንደ ሆነ ገልጸው ነበር።
አንቀጽ 143
1. የሁለተኛው የቫቲካን ጉባኤ እና ከዚያ ማግሥት የክርስቲያኖችን ሕብረት በተመለከተ ይፋ የሆኑ አስተምህሮዎችን ተግባራዊ ማድረግ የክርስቲያን አንድነትን ለማስፋፋት የሚሰራ የቅድስት መንበር ዋና ጽ/ቤት ተግባር ነው።
2. የክርስቲያናዊ ሕብረት እንቅስቃሴን ለመምራት፣ ለማስተባበር እና ለማዳበር ትክክለኛውን ትርጓሜ እና ታማኝ የሆነ አተገባበርን ይመለከታል።
3. የክርስቲያን ሕብረትን ለማራመድ ተስማሚ የሆኑ የካቶሊክ ስብሰባዎችን እና ዝግጅቶችን በሀገር አቀፍም ሆነ በአለም አቀፍ ደረጃ እንዲከናወኑ ያበረታታል።
4. የክርስቲያን አንድነትን ለማስፋፋት የሚሰራ የቅድስት መንበር ዋና ጽ/ቤት ከቅድስት መንበር ጋር የተያያዙ ሌሎች የቤተ ክርስቲያን ተቋማትን፣ ቢሮዎችን እና ተቋማትን ከሌሎች አብያተ ክርስቲያናት እና የክርስቲያን ማህበረሰቦች ጋር የሚያካሂዱትን የክርስቲያን ሕብረት ተነሳሽነቶች ያስተባብራል።
አንቀጽ 144
1. ከዚህ ቀደም ጉዳዮችን ለሮም ጳጳስ ካቀረበ በኋላ፣ የክርስቲያን አንድነትን ለማስፋፋት የሚሰራ የቅድስት መንበር ዋና ጽ/ቤት ከሌሎች አብያተ ክርስቲያናት እና ክርስቲያን ማህበረሰቦች ጋር ያለውን ግንኙነት ይንከባከባል። የባለሙያዎችን ትብብር በመጠቀም ከእነሱ ጋር አንድነትን ለማጎልበት ሥነ-መለኮታዊ ውይይቶችን እና ስብሰባዎች እንዲደረጉ ያበረታታል።
2. የክርስቲያን አንድነትን ለማስፋፋት የሚሰራ የቅድስት መንበር ዋና ጽ/ቤት የካቶሊክን የስነ-መለኮት ውይይት አባላትን እና የካቶሊክ ታዛቢዎችን እና ልዑካንን ለተለያዩ የክርስቲያን ሕብረት ስብሰባዎችን እንዲሳተፉ ይሾማል። መቼም ተገቢ ሆኖ ሲገኝ፣ በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ወሳኝ በሆኑ ስብሰባዎች እና ዝግጅቶች ላይ ታዛቢዎችን፣ ወይም የሌሎች አብያተ ክርስቲያናት እና ክርስቲያን ማህበረሰቦች የወንድማማችነት ተወካዮችን ይጋብዛል።
አንቀጽ 146
በካቶሊኮች እና በአይሁዶች መካከል ያለውን ግንኙነት ለማራመድ ከአይሁዶች ጋር የሃይማኖት ግንኙነት ኮሚሽን የክርስቲያን አንድነትን ለማስፋፋት የሚሰራ የቅድስት መንበር ዋና ጽ/ቤት ውስጥ ተመስርቷል። ኮሚሽኑ የሚመራው በጽ/ቤቱ ዋና ጸኃፊ ነው።
እውነትን ፍለጋ አብሮ መጓዝ
የክርስቲያን አንድነትን ለማስፋፋት የሚሰራ የቅድስት መንበር ዋና ጽ/ቤት አስተዳዳሪ የሆኑት ብፁዕ ካርዲናል ከርት ኮች “ባለፉት ስልሳ ዓመታት በክርስቲያኖች መካከል የተደረገው ውይይት በታሪክ ከመቼውም ጊዜ የበለጠ እድገት አስገኝቷል” ብለዋል። ለምሳሌ ያህል እንዲህ ብለዋል:- “ለአሥራ አምስት መቶ ዓመታት የዘለቀውን ውዝግብ ያስቆመው ከምሥራቃውያን ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት ጋር የተደረገው የክርስቶሎጂ (የክርስቶስ ባሕሪይ) የተመለከተ መግለጫ ወይም በአሥራ ስድስተኛው መቶ ዘመን የተሐድሶ ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ የተፈታው ጽድቅን የተመለከተ አስተምህሮ ላይ የጋራ የመግባቢያ መግለጫ በማውጣት መጠናቀቁ ይታወሳል። ቢያንስ ክርስቲያኖች እርስ በርሳቸው እንደ ጠላት እንደማይተያዩ፣ ይልቁንም በክርስቶስ ወንድሞችና እህቶች መሆናችንን ያሳያል።
የቀድሞ ነፍስኄር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ እ.አ.አ በግንቦት 2022 ዓ.ም የክርስቲያን አንድነትን ለማስፋፋት የሚሠራ የቅድስት መንበር ዋና ጽ/ቤት በነበረው የምልአተ ጉባኤ ንግግራቸው ማጠቃለያ ላይ ሁላችንም “ወደ ፊት እንድንሄድ፣ በአንድነት እንድንራመድ” በንግግራቸው የጋበዙ ሲሆን አክለውም፣ “እውነት ነው የነገረ መለኮት ሥራ በጣም አስፈላጊ ነው፣ እናም ማሰላሰል አለብን፣ ነገር ግን ወደ አንድነት ጎዳና ከመሄዳችን በፊት የሃይማኖት ምሁራን እስኪስማሙ መጠበቅ አንችልም። በመቀጠልም "አንድ ጊዜ አንድ ታላቅ የኦርቶዶክስ የሃይማኖት ምሁር የነገረ መለኮት ሊቃውንት መቼ እንደሚስማሙ እንደሚያውቅ ነግሮኛል። 'መቼ ነው?' ቢዬ ጠይቄው ነበር። በመጨረሻው ቀን ፍርድ ማግሥት ላይ ነው አለኝ። እስከዚያው ድረስ ግን እንደ ወንድማማቾች በጉዞ፣ በአንድነት፣ በጸሎት፣ በበጎ አድራጎት ስራዎች፣ እውነትን ፍለጋ በጋራ መጓዝ አለብን። ይህ የወንድማማችነት መንፈስ የሁላችንም ነው" ብለው መናገራቸው ይታወሳል።