MAP

የካቶሊክ ዲጂታል ሚስዮናውያን እና ተፅዕኖ ፈጣሪዎች ኢዮቤልዩ የካቶሊክ ዲጂታል ሚስዮናውያን እና ተፅዕኖ ፈጣሪዎች ኢዮቤልዩ 

የካቶሊክ ዲጂታል ሚስዮናውያን እና ተፅዕኖ ፈጣሪዎች በኢዮቤልዩ በዓል ላይ ተስፋን እንደሚጋሩ ተገለጸ

በዓለም ዙሪያ የሚገኙ በመቶዎች የሚቆጠሩ የካቶሊክ ዲጂታል ሚሲዮናውያን እና ተጽዕኖ ፈጣሪዎች ለመጀመሪያ ጊዜ በተዘጋጀላቸው የኢዮቤልዩ በዓል ላይ ለመገኘት ወደ ሮም መጥተዋል። አባላቱ በሁለት የበዓል ቀናት ውስጥ የሚገናኙት ኅብረትን ለማጎልበት፣ ተልዕኮን ለማጠናከር እና በዲጂታል መድረኮች ተስፋን ለመጋራት እንደ ሆነ ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ከሰኞ ሐምሌ 21-25/2017 ዓ. ም. ድረስ የሚከበረው የወጣቶች ኢዮቤልዩ በዓል አካል የሆኑትን  የካቶሊክ ዲጂታል ሚሲዮናውያን እና ተፅዕኖ ፈጣሪዎችን ለኢዮቤልዩ በዓል ያስተባበረው በቅድስት መንበር የስብከተ ወንጌል አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ሲሆን፥ ዓላማው በመስመር (በይነ-መረብ) ላይ ወንጌልን የሚሰብኩ ሰዎችን አንድ ላይ ማሰባሰብ፣ ድንበር በሌላት አንዲት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ በኅብረት እንዲያስተነትኑ፣ እንዲጸልዩ እና በዓላትን በኅብረት እንዲያከብሩ ማድረግ እንደሆነ ታውቋል።

“የሰዎች የአውታረመረብ ላይ ግንኙነት እንጂ አልጎሪዝም አይደለም"

ዶ/ር ፓውሎ ሩፊኒ፥ የቅድስት መንበር መገናኛ ጽሕፈት ቤት ተጠሪ፣ በሮም ባሰቡት የዝግጅቱ መክፈቻ ንግግር፥ የበዓሉ ተሳታፊዎች እርስ በርስ የመደማመጥ እና የመገናኘት ቅዱስ ሥፍራ መምጣታቸውን በማስታወስ አቀባበል አድርገውላቸዋል።

“በአካል መገናኘት እጅግ መልካም ነው” ያሉት ዶ/ር ፓውሎ ሩፊኒ፥ ዲጂታል መድረኮች ቢያገናኙንም በእርግጥ እርስ በርስ የሚያስተሳስረን ዲጂታል በይነ-መረብ ሳይሆን ከእኛ በላይ የሆነ እግዚአብሔር ራሱ ነው” ብለዋል።

ቤተ ክርስቲያን በይነ-መረብ ከመፈጠሩ ከረጅም ጊዜ በፊት እንደ ነበረች እና አንድነትን በተጨባጭ የምትገልጽ “በይነ-መረብ” እንደ ሆነች ገልጸው፥ ይህ አንድነት በኮድ ወይም በይዘት ያልተመሠረተ ነገር ግን ፍጹም ባልሆኑ እና በተለያዩ፣ በአንድ ጥምቀት እና በአንድ እምነት በተዋሃዱ ሰዎች የተመሠረተ መሆኑን አስረድተው፥ በሥፍራው የተገኙት ራሳቸውን ከፍ ከፍ የማድረግ ፈተናዎችን ተቋቁመው ተልዕኳቸውን በትህትና እንዲወጡ አሳስበዋል።

ነፍስሔር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን በመጥቀስ ማስተዋል የሚገባቸውን ጥያቄዎች ያቀረቡት ዶ/ር ፓውሎ ሩፊኒ፥ በተስፋ መቁረጥ ውስጥ ስንገኝ እንዴት ተስፋን መዝራት እንችላለ? መለያየትን እንዴት መፈወስ እንችላለን? ግንኙነታችን በጸሎት ላይ የተመሠረተ ነው ወይስ የጋራ ስምን ለማግኘት ነው?” ሲሉ ጠይቀዋል።

እነዚህ ጥያቄዎች ቀላል እንዳልሆኑ የተናገሩት ዶ/ር ፓውሎ ሩፊኒ፥ ዛሬ ባለው የዲጂታል ባሕል ውስጥ ወንጌልን ለመስበክ ለሚፈልግ ማንኛውም ሰው መድረኩ እምቅ አቅም የሚገኝበት ቢሆንም ነገር ግን ጥልቅ ሃላፊነት መውሰድን የሚጠይቅ መሆኑን አስገንዝበዋል።

በአዳራሹ ውስጥ ለነበሩት ወጣቶች ባቀረቡት ምክር፥ “በዚህ ማዕበል መበላት እንደማይቻል መመስከር አለብን” ብለው፥ “መረባችንን ስጋት ወዳለበት አቅጣጫ መወርወር የለብንም” ሲሉ ወጣቶችን አበርታተዋል።

ዶ/ር ፓውሎ ሩፊኒ፥
ዶ/ር ፓውሎ ሩፊኒ፥

“ዲጂታሉ ዓለም ተስፋን ይፈልጋል”

የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ፒየትሮ ፓሮሊን በአዳራሹ ለተገኙት ወጣቶች ባደረጉት ንግግር፥ ወጣቶች ከተስፋ ጋር እንዲቆራኙ ጥሪ አቅርበዋል። የተሳሳተ መረጃ በሚሰራችበት፣ መከፋፈል እና ማግለል በበዛበት ዘመን የበይነ-መረብ ላይ ግንኝነትን ሊቆጣጠር እንደሚችል ገልጸው፥ “ዲጂታል ሚስዮናውያን ከዚህ በተለየ መንገድ የኢየሱስ ክርስቶስን ብርሃን ወደ ዓለም እንዲያመጡ ተጠርተዋል” ብለዋል።

“እናንተ ይዘት ፈጣሪዎች ብቻ ሳትሆኑ ነገር ግን የወንጌል መስካሪዎች፥ መድረክ አዘጋጆች ብቻ ሳትሆኑ የመገናኛ ድልድይን የምትገነቡ ናችሁ” ያሉት ብጹዕ ካርዲናል ፒየትሮ ፓሮሊን፥ በበይነ-መረብ ላይ የክርስቲያኖች መገኘት እውነትን በመናገር፣ በበጎ አድራጎት እና በትህትና መታወቅ እንዳለበት ተናግረው ዓላማውም የእርስ በርስ ግንኝነት ባሕልን የሚያስተዋውቅ መሆን እንዳለበት አሳስበዋል።

“አጭር መልዕክት እንኳ ቢሆን በእምነት እና በፍቅር ከተጋሩት የጸጋ ነጸብራቅ ሊሆን ይችላል” ብለው፥ ተጽዕኖ ፈጣሪዎች በጸሎት፣ በቅዱሳት መጻሕፍት እና ምስጢራ እንዲጸኑ አበረታትተው፥ ይህም ከቤተ ክርስቲያን ማኅበረሰብ ጥንካሬን እንደሚያገኝ አስረድተዋል።

ብጹዕ ካርዲናል ፒየትሮ ፓሮሊን
ብጹዕ ካርዲናል ፒየትሮ ፓሮሊን

የጸሎት፣ የማዳመጥ እና የተልዕኮ መንገድ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ እሁድ ሐምሌ 20/2017 ዓ. ም. ረፋድ ላይ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት ባቀረቡበት ወቅት ባሰሙት ንግግር፥ አንድ ሳምንት በሚቆይ የኢዮቤልዩ በዓል ላይ ለመገኘት ወደ ሮም ለሚመጡ ወጣቶች የእንኳን ደህና መጣችሁ በማለት አቀባበል ማድረጋቸው ሲታወስ፥ በዓሉ ቅዳሜ ሐምሌ 26/2017 ዓ. ም. በሚቀርብ የዋዜማ ጸሎት እና በነጋታው እሁድ በሚቀርብ የመስዋዕተ ቅዳሴ ሥነ-ሥርዓት እንደሚጠናቀቅ ታውቋል።

ይህ በንዲህ እንዳለ፣ የወጣቶች ኢዮቤልዩ በዓል ዝግጅቶች ሰኞ ሐምሌ 21/2017 ዓ. ም. በቫቲካን ዙሪያ በሚገኙ ቁምስናዎች በቀረቡ የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት የተጀመረ ሲሆን፥ ተከታታይ ኮንፈረንሶች፣ አስተያየቶች እና የጠረጴዛ ዙሪያ ውይይቶች ተካሂደዋል። ከኢየሱሳውያን ማኅበር ካኅናት አባ ዴቪድ ማክለም እና አባ አንቶኒዮ ስፓዳሮ የቀረቡ ትምህርቶችን ጨምሮ፣ ቤተ ክርስቲያን ለ “አልጎሪዝም” እና ለበይነ-መረብ ባሕል ዘላቂ በሆነ የወንጌል ጥበብ እንዴት ምላሽ መስጠት እንደምትችል ተበራርቷል።

ለወጣቶች የተዘጋጁ ወርክሾፖች በዲጂታል የወንጌል ስርጭት፣ በገሃዱ ዓለም ተግዳሮቶች እና ዕድሎች ላይ ያተኮሩ ሲሆን፥ የጸሎት እና የጋራ ጊዜያት ከስልክ መስኮቶች በላይ የመተሳሰብ ስሜትን የፈጠሩ እንደነበር ተመልክቷል። በበዓሉ መክፈቻ ላይ የቀረቡ ዝግጅቶች ለበዓሉ ልዩ ድምቀቶችን የሰጡ ሲሆን፥  ከእነዚህም መካከል በብጹዕ ካርዲናል ሮድሪጌዝ ማራዲያጋ እና በብጹዕ ካርዲናል ሆሴ ኮቦ ካኖ የተመሩ የአምልኮ እና የንስሐ ስነ-ሥርዓቶች እንዲሁም በታይዜ ማኅበረሰብ የተመራ የዋዜማ ጸሎት ሥነ-ሥርዓት ይገኝበታል።

እንደ “የእግዚአብሔር ተጽዕኖ ፈጣሪነት” ለእመቤታችን ማርያም የተሰጠ ተልዕኮ

ሐምሌ 22/2017 የበዓሉ ተሳታፊ ወጣቶች በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ቅዱስ በር በኩል በማለፍ ብጹዕ ካርዲናል ሉዊስ አንቶኒዮ ታግል የሚመሩትን መስዋዕተ ቅሴን እንደሚካፈሉ ታውቋል። አብረው በዕለቱ የቫቲካን የአትክልት ሥፍራን በሚጎበኙበት ወቅት፥ ዶ/ር ፓውሎ ሩፊኒ “የእግዚአብሔር የመጀመሪያ ተጽእኖ ፈጣሪ” በማለት ለጠሯት እመቤታችን ቅድስት ማርያም  እንደ ዲጂታል ልኡካን ራቸውን ያቀርባሉ።

ዶ/ር ፓውሎ ሩፊኒ “ወጣት ነጋዲያን ወደ ሮም የመጡት የዲጂታል ፈጠራ እና የእርስ በርስ ግንኙነት ተልዕኳቸውን በትህትና፣ በማስተዋል እና በፍቅር ለመወጣት ያላቸውን ፍላጎት ለመግለጽ፥ የሚዲያ ተከታዮቻቸውን ለማሳደድ ወይም የራሳቸውን ስም ለማስተዋወቅ ሳይሆን ነገር ግን በዲጂታል ዘመን ውስጥ ሚስዮናውያን ደቀ መዛሙርት ለመሆን ነው” ሲሉ አስገንዝበዋል።

የዲጂታል ሚስዮናውያን እና የካቶሊክ ተፅእኖ ፈጣሪዎች ኢዮቤልዩ በዓል፥ ሮም ውስጥ በሚገኝ በሪሶርጂሜንቶ አደባባይ በሚቀርቡ የሙዚቃ እና የምስክርነት ዝግጅቶች እንደሚጠናቀቅ የተገለጸ ሲሆን፥ ይህ በዓል የብዝሃነት፣ የአንድነት እና ከዓለም ጋር ተስፋን የመጋራት ደስታን የሚያሳይ እንደሆነ ታውቋል።

በእምነት መተሳሰር

በሳምንቱ ውስጥ የሚቀርቡ ዝግጅቶችን በሙሉ የቫቲካን ዜና አገልግሎት ከቫቲካን ቮክስ መተግበሪያ እና ከቫቲካን ሬድዮ ጋር በመሆን በሥፍራው በአካል መገኘት ላልቻሉት የዓለም ወጣቶች በተለያዩ ቋንቋዎች በቀጥታ እንዲደርሳቸው ሽፋን እየሰጠ እንደሚገኝ ታውቋል።

“ብቻችን አይደለንም” ያሉት የቅድስት መንበር መገናኛ ጽሕፈት ቤት ተጠሪ ዶ/ር ፓውሎ ሩፊኒ፥ እኛ ነጠላ ሕዝቦች በዲጂታሉ ዓለም ውስጥ አንድ ላይ የተገናኘን ብቻ ሳንሆን ነገር ግን ዲጂታሉን ዓለም እውነተኛ ሰብዓዊ እና እውነተኛ ክርስቲያናዊ ለማድረግ የተጠራን ነን” ሲሉ አስገንዝበዋል።

የካቶሊክ ዲጂታል ሚስዮናውያንን እና ተፅዕኖ ፈጣሪዎችን በእንግድነት ከሚቀበሉ የኮሚቴ አባላት መካከል
የካቶሊክ ዲጂታል ሚስዮናውያንን እና ተፅዕኖ ፈጣሪዎችን በእንግድነት ከሚቀበሉ የኮሚቴ አባላት መካከል
29 Jul 2025, 17:33