ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ፥ እያንዳንዱ ማኅበረሰብ ሰላም የሚገኝበት ቦታ እንዲሆን መጠየቃቸው ተገለጸ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
የጣሊያን ካቶሊክ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዝደንት ብፁዕ ካርዲናል ማቴዮ ማርያ ዙፒ፥ በቅድስት መንበር የሩሲያ አምባሳደር ጋር ከተገናኙ በኋላ ሰላምን የሚመለከቱ ጉዳዮችን በማስመልከት ከቫቲካን የዜና አገልግሎት ጋር ቃለ ምልል አድርገዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ የጣልያን ካቶሊክ ብጹዓን ጳጳሳትን ሰኔ 10/2017 ዓ. ም. በቫቲካን በተቀበሏቸው ጊዜ ያስተላለፉትን መልዕክት በማስታወስ ቃለ ምልልሳቸውን የጀመሩት ብፁዕ ካርዲናል ማቴዮ ማርያ ዙፒ፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሁን ካለንበት ወቅታዊ ሁኔታ አንፃር ትክክለኛ እና ጥልቅ ትምህርት መስጠታቸውን ተናግረው፥ ሁሉም ሀገረ ስብከቶች በሠላም ላይ ያተኮረ ሐዋርያዊ አገልግሎት አቀራረብ ማዳበር እንደሚገባ መጠየቃቸውን አስታውሰዋል።
አስፈላጊ እና ወቅታዊ በሆኑ ርዕሠ ጉዳዮች ላይ መወያየታቸውን የገለጹት ብፁዕ ካርዲናል ማቴዮ ዙፒ፥ በሰላም ላይ በሚደረጉ ጥናታዊ ውይይቶች ላይ ብቻ ራስን መገደብ ትክክል እንዳልሆነ ተናግረው፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ኃላፊነት እንደሚሰማው ሰው፥ እያንዳንዱን ማኅበረሰብ ሰላም የሚገኝበት ሥፍራ እንድናደርግ መጠየቃቸው ተጨባጭ እና ውጤታማ ጥሪ መሆኑን አስረድተዋል።
በመጀመሪያ ደረጃ ለጸሎት ያለንን ቁርጠኝነት በተጨባጭ መግለጽ እንደሚገባ የተናገሩት ብፁዕ ካርዲናል ማቴዮ ዙፒ፥ የጣልያን ካቶሊክ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ቋሚ ምክር ቤት በዚህ ጉዳይ ላይ የጴንጤቆስጤ በዓል የሚከበርበትን ዕለት በመምረጥ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ሁሉንም ማኅበረሰቦች ማሳተፍ የሚችልባቸውን ሌሎች አጋጣሚዎችን መፈለግ እንደሚያስፈልግ መጠቆሙን እና ጰንጠቆስጤ በዓል እንደ እውነቱ ከሆነ ሁሉም ሕዝቦች በመንፈስ የሚዋሄዱበት እና ይህ ጊዜ ታላቅ የሰላም ጥሪ የሚቀርብበት እንዲሆን መፈለጋቸውን አስረድተዋል።
በጸሎት ከሌሎች ጋር መተባበር ጥቃትን እና ጦርነትን ለማስቆም ዋና መንገድ እንደሆነ የገለጹት ብፁዕ ካርዲናል ማቴዮ ዙፒ፥ በጦርነት ምክንያት ከፍተኛ ስቃይ የደረሰባቸውን ተቀብሎ መርዳት እና አብሮነትን መግለጽ አስፈላጊ እንደሆነ አስረድተዋል። ብዙ የካቶሊክ በጎ አድራጎት ድርጅቶች የተሳተፉበትን መድረክ እንደ ምሳሌ የጠቀሱት ብፁዕ ካርዲናል ማቴዮ ዙፒ፥ በጦርነት የተጎዱትን ተቀብሎ ማስተናገድን በተመለከተ ቫቲካን እና ቅድስት መንበር ተባብረው በበጋ የዕረፍት ወቅት ከዩክሬን የመጡ ልጆችን ተቀብለው ማስተናገዳቸውን በማስታወስ፥ ይህም ለዓመታት የዘለቀ የአባ ፍራንኮ ፎንታና መልካም ተነሳሽነት መሆኑን ገልጸው፥ ለዚህ መልካም አቀባበል የዩክሬን ፕሬዝደንት አቶ ዘሌንስኪ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳትን ማመስገናቸውንም አስታውሰዋል።
“የሰላም ቤት” እና “የሰላም ትምህርት ቤት” የሚሉት ርዕሦች ከዓለም አቀፍ የሰላም ቀን መልዕክት የተወሰዱ መሆናቸውን ያስታወሱት ብፁዕ ካርዲናል ማቴዮ ዙፒ፥ ዛሬ በሚያሳዝን ሁኔታ ለጦርነት የሚቀሰቅሱ ትምህርቶችም መኖራቸውን ገልጸው፥ እነርሱም የጥቃት፣ የጥላቻ፣ የድንቁርና እና የጭፍን ጥላቻ ቅስቀሳዎች መሆናቸውን አስረድተዋል።
ጦርነት እንደ መብረቅ ብልጭታ በድንገት የሚመጣ ሳይሆን ነገር ግን ስለ ሰላም ትምህርት በማይሰጥባቸው አካባቢዎች ቀድሞውኑ ያለ እና የቆየ መሆኑን በመግለጽ፥ ስለ ሰላም ማስተማር ማለት ሰዎች እርስ በርስ እንዲተዋወቁ ማድረግ፣ በመካከላቸው መተሳሰርን፣ መከባበርን እና መተሳሰብን መፍጠር ማለት እንደሆነ አስረድተዋል።
የሰላም ቤትን ለመገንባት በትምህርት ቤቶች፣ ከትምህርት ውጭ እና በቁምስናዎች ውስጥም በየጊዜው ልዩ ልዩ ስልጠናዎችን መስጠት መጀመር አስፈላጊ እንደሆነ ተናግረው፥ ለዚህም የጣሊያንኛ ቋንቋ ትምህርት ቤቶችን እንደ ምሳሌ በመጥቀስ፥ ቁምስናዎች እና ማኅበረሰቦች እነዚህን ትምህርት ቤቶች እንደሚያደራጁ እና ቋንቋ አንድ ሰው የሚኖርበትን አካባቢ እንደ ቤቱ አድርጎ እንዲመለከተው ለማድረግ የመጀመሪያው መንገድ መሆኑን አስረድተዋል።
በውጭ አገራት የሚገኙ የስደተኛ ቤተሰብ ልጆች ዛሬም ቢሆን እንደ ባዕድ እንደሚቆጠርሩ የተናገሩት ብፁዕ ካርዲናል ማቴዮ ዙፒ፥ እነዚህ ልጆች የአገሩ ዜጎች ልጆች የክፍል ጓደኞቻቸው በመሆናቸው እነርሱን መርዳት፣ መንከባከብ እና የተጎዱበትን ሁኔታ ለይቶ በማወቅ መርዳት ተፈጥሯዊ ግዴታ ሊሆን እንደሚገባ አሳስበዋል።
እነዚህ በብዙ ቦታዎች የሚያዩዋቸው ምልክቶች በመሆናቸው የሰላም ትምህርት ቤቶችን መመሥረት አስፈላጊ እንደሆነ፣ ይህን ለማመቻቸት የእርስ በርስ ግንኙነትን ማሳደግ እና እየተከሰተ ያለውን ነገር ለመረዳት የሚያግዝ የትምህርት፣ የእውቀት እና ጥሩ መረጃ የማግኛ መንገዶችን ማግኘት አለብን ብለዋል።
“ሰላምን ለማምጣት ለሚደረገው ጥረት መሠረቱ ግልፅ ነው” ያሉት ብፁዕ ካርዲናል ማቴዮ ዙፒ፥ ሰላምን ለማምጣት ቤተ ክርስቲያን ምን ማድረግ አለባት? ለሚለው ጥያቄ መልሱ፥ ቤተ ክርስቲያን ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ በሰፊው መናገር እንዳለባት አሳስበው፥ ነፍስሔር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ከመናገር ሌላ ምንም እንዳላደረጉ፥ ከመጀመሪያው አንስቶ “ከወንጌል የሚገኝ ደስታ” የሚለውን ሐዋርያዊ መልዕክት ይፋ ማድረጋቸውን እና የዚህ መልዕክት ዋና ጭብጥ ኢየሱስ ክርስቶስን ለዓለም ማወጅ እንደሆነ አስረድተዋል።
ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ መናገር ደግሞ ወደ ታሪክ መግባት ማለት እንደሆነ፥ በስብከተ ወንጌል እና በሰው ልጅ ዕድገት መካከል፣ በቅዱስ ቁርባን ማዕድ እና በድሆች ማዕድ መካከል፣ የቅዱስ ቁርባን ማዕድ በማዘጋጀት እና ለሌሎች ትኩረት የሚሰጡ መድረኮችን በማዘጋጀት መካከል በጣም የጠበቀ ትስስር መኖሩን በማስገንዘብ፥ “በፍቅር እና በእውነት መካከል፣ በስብከተ ወንጌል እና በሰዎች ዕድገት መካከል ያለው አንድነት ፈጽሞ ሊጠፋ አይገባም” ብለዋል።
አንዳንድ ጊዜ የሰው ልጅ ዕድገት ቀድሞ እንደሚመጣ የተናገሩት ብፁዕ ካርዲናል ማቴዮ ዙፒ፥ ዓይኖቻችንን ከፍተን ስንመለከት ባልንጀራን እንደራስ መውደድ፣ ኢየሱስ በእርሱ ውስጥ እንዳለ መረዳት፣ በተቸገረ ጊዜ ማገዝ፣ በእንግድነት በቀበል፣ የታረዘ እንደሆነ ማልበስ እና በእነዚህ ሁለት ድርጊቶች መካከል ጥልቅ ግንኙነት መኖሩን አስገንዝበዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ “ቁምስናዎችን ሠላም የሚገኝባቸው ቤቶች ማድረግ ይገባል” ማለታቸውን በማስመልከት በሰጡት አስተያየት፥ ቁምስናዎች ከወዲሁ እየተለወጡ መሆናቸውን በእርግጠኝነት የተናገሩት ብፁዕ ካርዲናል ማቴዮ ዙፒ፥ በተለይም በመካከለኛው እና በሰሜኑ የአገራቸው ክፍል ብቻውን የሆነ የቀረ ቁምስና ማግኘት ከሞላ ጎደል ብርቅ እየሆነ መምጣቱን ገልጸው፥ በጥቅሉ ብዙ ቁጥር ያላቸው ቁምስናዎች አንድነትን እና ኅብረትን መፍጠር በኅብረት ለማደግ እንደሚረዳ አስረድተዋል።
“ዋናው ነጥብ ቁምስና የሁሉ ሰው ቤት እንዲሆን ማድረግ ነው” ያሉት ብፁዕ ካርዲናል ማቴዮ ዙፒ፥ ለዚህም እውቅናን በመስጠት ማኅበረሰብን መገንባት፣ እውቀትን ማጎልበት እና የግንኙነት አቅምን መፍጠር እንደሚገባ አሳስበዋል።
በእርስ በርስ ግንኙነት ጭብጥ ላይ ብዙ ጊዜ መወያየታቸውን ያስታወሱት ብፁዕ ካርዲናል ማቴዮ ዙፒ፥ ይህም ራስን ብቻ ማገዝ፥ አብረው ጊዜ ማሳለፍ ወይም የኮንዶሚኒዬም ቤት ሳይሆን ነገር ግን እንደ ቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ አገላለጽ መሠረት፥ ሁሉም ሰው ቤቱ እንደሆነ እንዲሰማው ማድረግ ነው ብለዋል።
ዛሬ እርስ በርስ በሚያጋጨን እና በሚለያየን ዓለም ውስጥ ይህን ተግባራዊ ማድረግ ትልቅ ፈተና መሆኑን ይበልጥ መናገር እንደሚፈልጉ የተናገሩት ብፁዕ ካርዲናል ማቴዮ ዙፒ፥ በጣሊያን ውስጥ ከሦስት የቤተሰብ አባላት መካከል አንዱ በብቸኝነት ስሜት የተጠቃ እና የወሊድ መጠን እየቀነሰ ሲመጣ ይህ ቁጥር እንደሚጨምር አስረድተው፥ “ቤተ ክርስቲያን ማዕዷ ዘወትር ሰፊ የሆነ፣ በብኝነት ስሜት የተጠቁትንም ጨምሮ ሁሉም ሰው ብዙ ወንድሞች እና እህቶች እንዳሉት የሚያውቅበት ቦታ መሆን አለባት” ብለዋል።
“የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ መመረጥ ያለ ጥርጥር ታላቅ የደስታ ምንጭ ሆኗል” ያሉት ብፁዕ ካርዲናል ማቴዮ ዙፒ፥ ያለፉት ሁለት ወራት ቅዱስነታቸው በብዙ የዋህነት እና ቁርጠኝነት ጉዞውን ለመቀጠል ፍላጎት እንዳላቸው የሳዩበት እንደሆነ በመግለጽ፥ የቤተ ክርስቲያን ትውፊት ጥልቅ እና አንድ ሰው በልቡ ውስጥ ያለውን ለማስተላለፍ ሳያቋረጥ የሚጥርበት፥ በተመሳሳይም በእያንዳንዱ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት መካከል ያሉትን ትክክለኛ ልዩነቶች የሚያሳይ እንደሆነ ተናግረው፥ በእያንዳንዳችን ውስጥ ያለው ስሜት በእያንዳንዱ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ውስጥም የሚገኝ መሆኑን አስረድተዋል።
እነዚህ ያለፉት ሁለት ወራት በቅዱስ ዓመት አውድ ውስጥ በጠንካራ የመጋራት፣ እርስ በርስ የመገናኘት፣ አብሮ በመሆን በኅብረት መጓዝ የተጀመሩባቸው በመሆናቸው ጠቃሚ እንደሆኑ ገልጸው፥ በዚህ ዐውድ ውስጥ ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ በመታዘዝ ከሁሉም በላይ በጸሎታችን መደገፍ እንደሚገባ አሳስበዋል። ሁሉም ሰው ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ መታዘዝ እንደሚገባ ሲናገሩ እውነት እና አስፈላጊ ነገር መሆኑን እየተናገሩ መሆኑን ገልጸው፥ አንድ ሰው ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት መታዘዝ ማለት የሚታዘዝላቸው ስለተስማማው ብቻ ሳይሆን ዘወትር መታዘዝ አለበት ሲሉ አክለዋል።
ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት መታዘዝ እና ከጎናቸው መሆን ማለት ቅርበታችን እንዲሰማቸው ማድረግ እና በዚህ የኢዮቤልዩ አውድ ውስጥ ሁሉም ሰው የኅብረት ጉዞን ውበት እንዲረዳ ዕድል በመስጠት ለተስፋ የሚዘጋጀውን ተስፋን እንዲያገኝ ማድርግ መሆኑን አስረድተዋል።
እንደ ዛሬ ባለው ዓለም ውስጥ ቅዱሱ ዓመት፣ የተስፋ ኢዮቤልዩ፣ ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ጋር ለመሆን በእውነት ታላቅ ዕድል መሆኑን እንደሚያምኑ ገልጸዋል።