ብጹእ ካርዲናል ቶለንቲኖ የዛይድ ሽልማት የዳኞች ኮሚቴ ውስጥ አንዱ ሆነው ተሾሙ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
በቫቲካን የባህል እና የትምህርት ጉዳዮችን በበላይነት የሚቆጣጠረው ጳጳሳዊ ጽህፈት ቤት ዋና ጸኃፊ የሆኑት ብጹእ ካርዲናል ጆዜ ቶሌንቲኖ ዴ ሜንዶንካ ለሰባተኛው የዛይድ ሽልማት ለሰብአዊ ወንድማማችነት የዳኞች ኮሚቴ አባል ሆነው መሾማቸው የተነገረ ሲሆን፥ የአንድ ሚሊዮን ዶላር ሽልማት ያለው ይህ የሽልማት መርሃ ግብር የተቋቋመው የካቲት 2011 ዓ.ም. ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ከታላቁ ኢማም አል-አዝሃር ጋር ያደረጉትን ታሪካዊ ውይይት እና ሰብአዊ ወንድማማችነትን አስመልክተው ያወጡትን የጋራ ሰነድ ተከትሎ እንደሆነ ይታወቃል።
የሰብአዊ ወንድማማችነት ሰነዱ ፊርማ የተካሄደው በአሁኑ ወቅት ሽልማቱን ስፖንሰር እያደረገች በምትገኘው የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች ሲሆን፥ ሽልማቱም በመስራቹ ሼክ ዛይድ ቢን ሱልጣን አል ናህያን ስም መሰየሙ ተገልጿል።
ዳኞቹ
ተሸላሚዎቹ የሚመረጡት በየዓመቱ በሚቀያየሩ ገለልተኛ ዳኞች ሲሆን፥ ከኮሚቴ አባላቱ መካከል ሁል ጊዜ በየዓመቱ አንድ በርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት፣ አንድ በታላቁ ኢማም አል-አዝሃር እና አንድ በተባበሩት መንግስታት ዋና ፀሃፊ የሚመረጥ ሰው እንደሚኖር ተገልጿል።
ከብፁዕ ካርዲናል ቶለንቲኖ በተጨማሪ በዘንድሮው የዳኞች ኮሚቴ የተካተቱት የዩኒሴፍ ዋና ዳይሬክተር ካትሪን ራስል፣ የቀድሞ የአውሮፓ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት እና የቤልጂየም ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት ቻርለስ ሚሼል፣ የቀድሞ አፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር እና የቻድ ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት ሙሳ ፋኪ ማሃማት፣ የኡዝቤኪስታን ሪፐብሊክ ፕሬዚዳንት አስተዳደር ኃላፊ ወይዘሮ ሳይዳ ሚርዚዮቫ እንዲሁም የዛይድ ሽልማት ለሰብአዊ ወንድማማችነት ዋና ፀሀፊ ዳኛ ሞሃመድ አብደልሰላም ይገኙበታል።
ብፁዕ ካርዲናል ቶለንቲኖ በሰጡት መግለጫ ሹመቱ ሽልማቱ እንዲቋቋም ትልቅ ሚና የተጫወቱት እና የክብር ተሸላሚ የሆኑት የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ውድ ትሩፋት አካል መሆኑን ጠቁመዋል።
ካርዲናሉ በማከልም የሰብዓዊ ወንድማማችነት እሴቶችን በተግባር የሚያሳዩትን ለማክበር በርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ የተሰጣቸውን ኃላፊነት መቀበላቸውን ገልጸው፥ በአገልግሎት መንፈስ እና ለርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ያላቸውን ታዛዥነት ለማሳየት እጩዎችን በታማኝነት ለመገምገም እና በዓለም ዙሪያ ለውጥ እያመጡ ከሚገኙ በርካታ ሰዎች ጋር ለመተዋወቅ ያላቸውን ጉጉት ገልጸዋል።
ሽልማቱ
የዛይድ ሽልማት ዓላማ የሰብዓዊ ወንድማማችነትን በማሳደግ፣ ሰላማዊ አብሮ መኖርን በማስፈን እንዲሁም የመቻቻል እና የመተሳሰብ እሴቶችን በማበረታታት የላቀ አስተዋጾ ላደረጉ ግለሰቦች እና ቡድኖች እውቅና መስጠት እንደሆነ የገለጹት ብጹእነታቸው፥ በዚህ የአንድ ሚሊዮን ዶላር የገንዘብ ስጦታን በሚያካትተው ሽልማት ከዬትኛውም ታሪካዊ ዳራ፣ ሃይማኖት ወይም ዜግነት ያላቸው ግለሰቦች እና ድርጅቶች ሊሸለሙ እንደሚችሉ አስረድተዋል።
በተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች የቅድስት መንበር ሐዋርያዊ ተወካይ የሆኑት ሊቀ ጳጳስ ክሪስቶፍ ኤል ካሲስ በ 2025 ዓ.ም. በተካሄደው የዛይድ ሽልማት ሥነ-ሥርዓት ላይ ለቫቲካን ዜና አገልግሎት እንደተናገሩት የሰብዓዊ ወንድማማችነት ጽንሰ-ሐሳብ በሁለቱ ሃገራት መካከል ለሚደረገው ግንኙነት ያለውን ጠቀሜታ በአጽንዖት ገልጸው፥ በሃገራቱ መካከል ያለው ግንኙነት በአሁኑ ወቅት “በጣም ጥሩ” የሚባል ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።
የሁለቱ ሃገራት የትብብራቸው ዋና ትኩረት በዓለም ዙሪያ የሰብዓዊ ወንድማማችነትን ማበረታታት እንደሆነ ያስታወሱት ሊቀ ጳጳሱ፥ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ እና የታላቁ ኢማም ትብብር “ለሌሎች አርአያ” እንደሚሆን እንዲሁም “ሁላችንም አንድ ቤተሰብ ነን” የሚለውን የሚያስታውሰን ነው ሲሉ የዛይድ ሽልማትን አስፈላጊነት አጽንኦት ሰጥተው ገልጸዋል።