MAP

በማላዊ የአየር ንብረት ለውጥ ያስከተለው አደጋ በማላዊ የአየር ንብረት ለውጥ ያስከተለው አደጋ  (AFP or licensors)

የብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤዎች እና ምክር ቤቶች የሥነ-ምህዳር ለውጥ አስመልክተው ተማጽኖ አቀረቡ

ከእስያ (SECAM)፣ ከአፍሪካ (FABC) እና ከላቲን አሜሪካ (CELAM) የተውጣጡ የብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤዎች፣ ምክር ቤቶች ከላቲን አሜሪካ ጳጳሳዊ ኮሚሽን ጋር በመተባበር ፍትሃዊ የአየር ንብረት እና የሥነ-ምህዳር ለውጥን የተመለከተ የጋራ ሠነድ አሳትመዋል። ሠነዱ የተባበሩት መንግሥታት የአየር ንብረት ለውጥ ኮንፈረንስ (COP30) መሠረት ያደረገ እንደ ሆነ ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ከእስያ፣ ከአፍሪካ፣ እና ከመካከለኛው እና ከደቡብ አሜሪካ የመጡ የክልል ጳጳሳት ጉባኤዎች እና ምክር ቤቶች፣ ከላቲን አሜሪካው ጳጳሳዊ ኮሚሽን ጋር በመተባበር በዓለም ዙሪያ ፍትሃዊ የአየር ንብረት እና ሥነ-ምህዳራዊ ለውጥ እንዲመጣ ጥሪ በማቅረብ ላይ የሚገኙ ሌሎች ኃይሎችን ተቀላቅለዋል።

በተባበሩት መንግሥታት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (COP30) መሠረት በብራዚል-ቤሌም ከተማ ከኅዳር 1-12/2018 ዓ. ም. ሊካሄድ የታቀደውን የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤን ምክንያት በማድረግ የጋራ ሠነድ ይፋ አድርገዋል። “ለጋራ መኖሪያ ምድራችን ፍትሃዊ የአየር ንብረት እና ሥነ-ምህዳራዊ ለውጥ፣ ተሃድሶ እና የሐሰት መፍትሄዎችን መቋቋም” በሚል ርዕስ የታተመው የጋራ ሠነዱ ይፋ የተደረገው ሰኞ ሰኔ 24/2017 ዓ. ም. የቅድስት መንበር መግለጫ ክፍል ባዘጋጀው መግለጫ እንደሆነ ታውቋል። ሠነዱን ቀደም ብሎ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛም መመልከታቸው ታውቋል።

ሠነዱ ቤተ ክርስቲያን ለፍትሃዊ የአየር ንብረት ያላትን ቁርጠኝነት የሚደግም፣ አገራትን እና መንግሥታትን ወደ ተግባር እንዲተረጉሙት ጥሪ የሚያቀርብ፣ በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ጥሪ አነሳሽነት ጠቅላላ ሥነ-ምህዳርን ለማስተዋወቅ እና ዘንድሮ አሥረኛ ዓመቱን ከሚያከብረው “ውዳሴ ላንተ ይሁን!” የነፍስሔር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሐዋርያዊ መልዕክት ጋር የሚስማማ እንደሆነ ተመልክቷል።

ብጹዓን ጳጳሳቱ ሠነዱን ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ሲያቀርቡ
ብጹዓን ጳጳሳቱ ሠነዱን ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ሲያቀርቡ   (@VATICAN MEDIA)

ለህሊና የቀረበ ጥሪ

በሕንድ የጎዋ-ዳማኦ ሊቀ ጳጳስ እና የእስያ ጳጳሳት ጉባኤዎች ፌዴሬሽን ፕሬዝደንት ብፁዕ ካርዲናል ፊሊፔ ኔሪ ፌራዎ በመግለጫቸው፥ “መልዕክታችን ዲፕሎማሲያዊ ሳይሆን ይበልጥ ሐዋርያዊ፣ ምድራችንን እንደ ሸቀጥ በመመልከት ፍጥረትን ሊያወድም በሚችል ሥርዓት ውስጥ ለኅሊና የቀረበ ጥሪ ነው” ብለዋል።

ከብፁዕ ካርዲናል ፊሊፔ ኔሪ ጋር መግለጫ የሰጡት ካርዲናል ጄይም ስፔንገር፥ በብራዚል የፖርቶ አሌግሬ ሊቀ ጳጳስ፣ የብራዚል ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ (CNBB) ፕሬዚዳንት፣ የላቲን አሜሪካ እና የካሪቢያን ብጹዓን ጳጳሳት ምክር ቤት (CELAM) ፕሬዝደንት፣ ብፁዕ ካርዲናል ፍሪዶሊን አምቦንጎ ቤሱንጉ፣ በኮንጎ ዲሞክራሲያዊት ሪፐብሊክ የኪንሻሳ ሊቀ ጳጳስ፣ የአፍሪካ እና ማዳጋስካር ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤዎች ሲምፖዚየም (SECAM) ፕሬዝዳንት እና ወ/ሮ ኤምሊስ ኩዳ፥ የላቲን አሜሪካ ጳጳሳዊ ኮሚሽን ዋና ጸሐፊ እንደ ነበሩ ታውቋል።

ወ/ሮ ኤምሊስ ኩዳ በመግለጫቸው፥ “በብራዚል-ቤሌም ከተማ ከኅዳር 1-12/2018 ዓ. ም. የሚካሄደውን የተባበሩት መንግሥታት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (COP30) የምንሳተፈው፥ ጉዞ ላይ በምትገኝ ሲኖዶሳዊት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሚስዮናዊ ሐዋርያት በመሆን እና በፍጥረት ላይ በተሰነዘረ ጦርነት ውስጥ ሰላምን ለመፍጠር ነው፣ ፈጣን እርምጃ ካልወሰድን አሁንም ብዙዎች ይሞታሉ” ሲሉ ወ/ሮ ኤምሊስ ኩዳ አስረድተው፥ ይህንን የምናደርገው፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ እንደተናገሩት፥ እንደ ቤተ ክርስቲያን ዘወትር በተለይ በስቃይ ውስጥ ለሚገኙት ቅርብ ለመሆን በመፈለጋችን ነው ብለዋል።

ከአማዞን እስከ አፍሪካ የሚሰማ የቤተ ክርስቲያን ድምጽ

ብጹዕ ካርዲናል ጄይም ስፔንገር፥ በብራዚል የፖርቶ አሌግሬ ሊቀ ጳጳስ፣ የብራዚል ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ (CNBB) ፕሬዚዳንት ላቲን አሜሪካን በማስመልከት በሰጡት መግለጫ፥ የአማዞን አካባቢ አገራት ሕዝቦች፣ በአካባቢው የተከሰተ የአየር ንብረት ለውጥ ሰማዕታት፣ የወንዞች ዳርቻ ነዋሪዎች፣ ነባር የአካባቢው ተወላጆች፣ አፍሪካዊ የዘር ሐረግ ያላቸው፣ በግብርና ሥራ የሚተዳደሩ እና የከተማ ማኅበረሰቦች ማለት እንችላለን” ሲሉ ተናግረዋል።

“በአኗኗር ዘይቤ፣ በአመራረት እና በፍጆታ ላይ ለውጦችን ለማድረግ አስቸኳይ ፍላጎት አለ” ያሉት ብጹዕ ካርዲናል ጄይም ስፔንገር፥ በኢኮኖሚያዊ ፍላጎቶች ላይ ‘ጭንብል’ በማሰር፥ “አረንጓዴ ካፒታሊዝም”፣ “የሽግግር ኢኮኖሚ” እና “በአማዞን ውስጥ አዲስ የነዳጅ ማውጫ ጉድጓዶችን እንከፍታለን” የሚሉ የማታለያ ስሞችን አውግዘው፥ ቤተ ክርስቲያን ተፈጥሮን ወደ ገንዘብነት ለመለወጥ የሚፈልጉ ዘዴዎችን እንደማትቀበል አጽንኦት ሰጥቷል።

ብፁዕ ካርዲናል ፍሪዶሊን አምቦንጎ ቤሱንጉ፣ በኮንጎ ዲሞክራሲያዊት ሪፐብሊክ የኪንሻሳ ሊቀ ጳጳስ፣ የአፍሪካ እና ማዳጋስካር ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤዎች ሲምፖዚየም (SECAM) ፕሬዝዳንት፥

የአፍሪካ አኅጉር ካቶሊክ አብያተ ክርስቲያናትን በመወከል እንደተናገሩት፥ ለዘመናት የተካሄደው የዘር ማጥፋት ወንጀል፣ ባርነት እና ብዝበዛ አፍሪካን ድሃ እንዳደረጋት ተናግረዋል። ማዕድናትን ለመበዝበዝ የሚደረገው ሩጫ፣ መሣሪያ የታጠቁ ቡድኖች መስፋፋት መነሻው ምን እንደሆነ ጠቁመው፥ ለሌሎች ብልጽግና የአፍሪካ ሕዝቦችን መስዋዕት የማያስከፍ ኢኮኖሚ እንዲመሠረት ጥሪ አቅርበዋል። “አፍሪካ ለሁሉም የሰው ልጆች ፍትህ እና ሰላም አስተዋፅኦ ማድረግ እንድምትፈልግ አጥብቀው የተናገሩት ብፁዕ ካርዲናል ፍሪዶሊን አምቦንጎ ቤሱንጉ፣ “የውሸት መፍትሄዎች እንዲያበቁ እና በአየር ንብረት ለውጥ በዋናነት የሚጎዱ ማኅበረሰቦችን ሳያዳምጡ የሚወሰዱ ውሳኔዎች እንዲቆሙ” በማለት አሳስበዋል።

በሕንድ የጎዋ-ዳማኦ ሊቀ ጳጳስ እና የእስያ ጳጳሳት ጉባኤዎች ፌዴሬሽን ፕሬዝደንት ብፁዕ ካርዲናል ፊሊፔ ኔሪ ፌራዎ በእስያ አኅጉር ዕይታ አንጻር በሰጡት መግለጫ፥ “በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በአየር ንብረት ለውጥን አስከፊ ውጤት ማለትም በአውሎ ነፋሶች፣ በግዳጅ ስደት፣ በደሴቶች ውድመት እና በወንዞች መበከል ጉዳት እንደደረሰባቸው ገልጸው፥ “ለሰብዓዊ ክብር ደንታ በሌላቸው በውሸት መፍትሄዎች የተጀመሩ ሜጋ መሠረተ ልማቶች፣ ንጹህ እና አረንጓዴ ሃይል በሚል ስም የተጀመሩ ሥራዎች በሂደት ላይ እንደሚገኙ አብራርተዋል።

“የበለጸጉ አገራት ደቡባዊውን ዓለም ዕዳ ውስጥ ሳያስገቡ የሥነ-ምህዳር ዕዳ እንዳለባቸው ተገንዝበው ሊከፍሉ ይገባል” ብለው፥ ቤተ ክርስቲያን ብዙውን ጊዜ ጉዳት የሚደርስባቸውን እንደ የትምህርት ፕሮግራሞችን፣ አዲስ የኢኮኖሚ መንገዶችን እና ከሴቶች እና ልጃገረዶች ጎን መሆንን የመሳሰሉ አማራጮችን ማስተዋወቅ እንደምትፈልግ አስረድተዋል።

ብፁዕ ካርዲናል ፊሊፔ ኔሪ

የነፍስሔር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ትሩፋት

ብፁዕ ካርዲናል ሚካኤል ቸርኒ፥ በቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለንተናዊ ዕድገት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ሃላፊ መድረኩን ተቀብለው እንደተናገሩት፥ ሠነዱ ከነፍስሔር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ትሩፋት ጋር ያለውን ግንኙነት አጽንኦት ሰጥተው፥ በዚህ ጋዜጣዊ መግለጫ፥ ከአሥር ዓመታት በፊት ይፋ የሆነው “የውዳሴ ላንተ ይሁን” የሚለው ሐዋርያዊ መልዕክት አተገባበር ፍጻሜ አግኝቷል ብሎ የሚገምት ሰው ይኖር ይሆን?” ብለው፥ መግለጫው ከዚህ በፊት ነፍስሔር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ያቀረቡትን ጥሪ እና ተተኪያቸው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ወደፊት ለማስቀጠል ጥሪ ያቀረቡበት መግለጫ ነው” በማለት ለዚህም ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

 

02 Jul 2025, 17:51