እህት ቤከርት፥ “አዲሱ ሠነድ በቤተ ክርስቲያናት መካከል ሲኖዶሳዊነት እውን ለማድረግ ያግዛል” አሉ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ባለለፈው ዓመት ከተካሄደው ሁለተኛ ዙር የሲኖዶስ ጠቅላላ ጉባኤ በኋላ ጠቅላይ ጽሕፈት ቤቱ ለቀጣዩ የሲኖዶሱ ጉዞ መመሪያ የሚሆን አዲስ ሠነድ አዘጋጅቷል። “የሲኖዶስ የተግባር ምዕራፍ” በሚል የተዘጋጀው ሠነዱ፥ በቤተ ክርስቲያናት እና በጠቅላይ ጽሕፈት ቤት መካከል ውይይት እንዲኖር እና በአብያተ ክርስቲያናት መካከል የሲኖዶሳዊነት ልምድ ልውውጥ እንዲኖር ለማድረግ ያለመ እንደሆነ ታውቋል።
የሠነዱን መዘጋጀት በማስመልከት ከቫቲካን የዜና አገልግሎት ጋር ቃለ ምልልስ ያደረጉት የጠቅላይ ጽሕፈት ቤቱ ዋና ጸሐፊ እህት ናታሊ ቤከርት፥ ስለ ሲኖዶሱ የአፈጻጸም ምዕራፍ፣ ስለ ሲኖዶሳዊነት ትርጉም፣ ስለ ሲኖዶሳዊነት አቀባበል እና የአዲሱን ሠነድ ዓላማዎች አብራርተዋል።
“የሲኖዶሱ የተግባር ምዕራፍ” ሠነድ ዝግጅት እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በጥቅምት ወር 2024 ዓ. ም. በሮም በተካሄደው ጉባኤ ከተጠናቀቀ በኋላ የተጀመረ መሆኑን ያስታወሱት እህት ቤከርት፥ “Episcopalis communio” ወይም “የጳጳሳት አንድነት” የተሰኘው ሐዋርያዊ ደንብ የሲኖዶሱን አፈጻጸም ማለትም የሲኖዶሱን ፍሬ በተግባር ላይ ማዋል በጣም አስፈላጊ እንደሆነ ማሳሰቡን ገልጸዋል።
ነፍስሔር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለመጀመሪያ ጊዜ የሲኖዶሱን የመጨረሻ ሠነድ ማጽደቃቸውን ያስታወሱት እህት ቤከርት፥ ቀጣዩ ሥራ በሠነዱ ውስጥ የተጠቀሱ የጉባኤው ፍሬዋችን በተግባር መግለጽ ነው ብለዋል።
እንደ ጎርጎሮሳውያኑ እስከ ጥቅምት 2028 ድረስ የትግበራ ምዕራፍ ፍሬዎችን ለመካፈል እና አንድ ዓይነት ግምገማ ላይ ለመድረስ በተወሰኑ ደረጃዎች ላይ እንደሚገኙ ገልጸው፥ ይህ ደግሞ በአገር ውስጥ በሀገረ ስብከት እና በአህጉር ደረጃ ባሉት የጳጳሳት ጉባኤዎች የሚጀምር መሆኑን አስረድተዋል።
ሲኖዶሳዊነትን በሁሉም ቦታ፣ በሁሉም የቤተ ክርስቲያን ደረጃዎች ለመተግበር ጊዜ እንደሚወስድ የተናገሩት እህት ቤከርት፥ ነገር ግን እጅግ አስፈላጊው ሂደቱን ደረጃ በደረጃ በመጓዝ ወደ ፊት መራመድ መሆኑን አስረድተዋል።
በሲኖዶሱ የመጨረሻ ሠነድ ውስጥ ፍቺ መኖሩን የገለጹት እህት ቤከርት፥ ሲኖዶሳዊነትን በሁለት የተለያዩ መንገዶች መረዳት እንደሚቻል፥ የመጀመሪያው፥ “ሲኖዶሳዊነት በአጭሩ ሁለተኛው የቫቲካን ጉባኤ ነው” ያሉትን አውስትራሊያዊ የነገረ መለኮት ምሑርን ኦርመንድ ራሽን ጽሑፍ ጠቅሰዋል። ሁሉም ሠነዶቻችን እነዚህን መንገዶች ተከትለን የምናደርገው ነገር የሁለተኛው የቫቲካን ጉባኤ ራዕይን የሚያመለክት መሆኑን አስረድተዋል።
ሲኖዶሳዊነት የምክር ቤቱን የአቀባበል ደረጃ ሁለተኛውን የቫቲካን ጉባኤ የምንረዳበት መንገድ ማለት እንችላለን ብለው፥ ሁለተኛው የቫቲካን ጉባኤ ሠነድ በሁሉም አካባቢ በእኩል ደርጃ በተግባር አለመገለጹን መረዳት የሚቻልበት መንገድ እንደሆነ አስረድተዋል።
ሲኖዶሳዊነትን በሁለት መንገድ መረዳት አለብን ያሉት እህት ቤከርት፥ ቤተ ክርስቲያን የመሆን መንገድ፣ በኢየሱስ ክርስቶስ ወንድሞች እና እህቶች፣ ከሌሎች ጋር በመሥራት ቤተ ክርስቲያን የመሆን መንገድ ነው ሲሉ አስረድተዋል።
ከሲኖዶሳዊነት ጠንካራ ፍሬዎች መካከል አንዱ ከክርስቲያኖች ጋር አብሮ መጓዝ እንደሆነ ገልጸው፥ በሃይማኖቶች መካከል የጋራ ውይይት ማድረግ፥ ከኅብረተሰቡ ጋር መገናኘት፣ ከሁሉም ሰው ጋር በተለይም ድሆችን እና የተገለሉ ሰዎችን ማዳመጥ እና እንግዳ ተቀባይ ቤተ ክርስቲያን ለመሆን ከሁሉም ጋር ወንጌልን ለመመስከር ፈቃደኛ መሆን አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል።
“የሲኖዶሱ የተግባር ምዕራፍ” ሠነድ አንዳንድ ቀላል ጥያቄዎችን ለመመለስ ሲፈልግ፥ በቅድሚያ ሲኖዶሳዊነትን በአገራት ደረጃ ተግባራዊ ለማድረግ ማገዝ እና በአገራቱ ውስጥ በሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት መካከል የሲኖዶሳዊነት ልምድን መለዋወጥ እንደሚገባ ማሳሰቡን ተናግረዋል።
የሲኖዶሳዊነት ልምድ ልውውጥ እሳቤ የፍጻሜ ሠነዱ የሲኖዶሳዊት ቤተ ክርስቲያን ዋና ሃሳብ እንደሆነ አስረድተው፥ የእግዚአብሔር ሕዝቦች በሆኑ የቤተ ክርስቲያኑ አባላት መካከል ልምድ መለዋወጥን ተግባራዊ ልናደርገው እንችላለን ብለው፥ ሁላችንም የምንሰጠው እና የምንቀበለው ስጦታ አለን ያሉት እህት ቤከርት፥ በመሆኑም በአብያተ ክርስቲያናት መካከል ስጦታን መለዋወጥ አስፈላጊነት መሆኑን ልንረዳ እንችላለን ብለዋል።