ሊቀ ጳጳስ አቡነ ፖል ሪቻርድ ጋላገር በሕንድ ሐዋርያዊ ጉብኝት መጀመራቸው ተገለጸ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ፖል ሪቻርድ ጋላገር፥ በቫቲካን የመንግሥታት እና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ግንኙነት ክፍል ዋና ጸሐፊ እሑድ ሐምሌ 6/2017 ዓ. ም. ወደ ሕንድ ተጉዘዋል።
በቅድስት መንበር የውጭ ጉዳይ ጽሕፈት ቤት @TerzaLoggia በ X ገጹ ባሠፈረው ዘገባ፥ ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ፖል ሪቻርድ ጋላገር በሕንድ የሚያደርጉትን ጉብኝት ሲያበስር እንደገለጸው፥ ዋና ጸሐፊው የእስያ አገር በሆነች ሕንድ ውስጥ እስከ ቅዳሜ ሐምሌ 12/2017 ዓ. ም. ድረስ እንደሚቆዩ አስታውቋል።
የሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ፖል ሪቻርድ ጋላገር ጉብኝት ዋና ዓላማ፥ በቅድስት መንበር እና በሕንድ ሪፐብሊክ መካከል ያለውን የወዳጅነት እና የትብብር ትስስር ማጠናከር መሆኑን ጽሕፈት ቤቱ በ X ገጹ ላይ ባሠፈረው ጽሑፍ ገልጿል።
ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን አብላጫ የሕንዱ እምነት ተካታይ ባለባት ሕንድ ውስጥ ከፍተኛ ቁጥር ያለውን ቤተ ክርስቲያን እንደምትወክል ታውቋል።
ምንም እንኳን ካቶሊካዊ ምዕመናን ከጠቅላላው የሕንድ ሕዝብ መካከል ከሁለት በመቶ በታች ቢሆንም በአንጻራዊነት ቁጥራቸው ከ23 ሚሊዮን በላይ መሆናቸው ይነገራል።
በሕንድ የምትገኝ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን በሦስት የአምልኮ ሥነ-ሥርዓቶች የተከፈለች ሲሆን እነርሱም የላቲን፣ የሲሮ-ማላባር እና የሲሮ-ማላንካራ ሥነ-ሥርዓቶች እንደሆኑ ታውቋል።