MAP

ወላጆች ለልጆቻቸው የሚያሳዩት ፍቅር ወላጆች ለልጆቻቸው የሚያሳዩት ፍቅር 

ቅድስት መንበር፥ ፖሊሲዎች ቤተሰቦችን፣ እናትነትን እና እኩልነትን መደገፍ እንዳለባቸው አሳሰበች

በተባበሩት መንግሥታት የቅድስት መንበር ቋሚ ታዛቢ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ገብርኤል ካቻ፥ ሀገራት በሴቶች እና በወንዶች መካከል ያለውን እኩልነት ከማስፈን ጋር ቤተሰብን፣ እናትነትን እና ወላድነትን የሚደግፉ እና የሚያስጠብቁ ፖሊሲዎችን እንዲተገብሩ ጥሪ አቅርበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ሊቀ ጳጳስ አቡነ ገብርኤል ካቻ፥ “በሴቶች እና በወንዶች መካከል ያለውን እኩልነት ከማስፈን ጎን ለጎን ቤተሰብን፣ እናትነትን እና ወላድነትን የሚደግፉ እና የሚያስጠብቁ ፖሊሲዎች መተግበር አለባቸው” ብለዋል።

ብጹዕ አቡነ ገብርኤል ይህንን የገለጹት፥ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዘላቂ ልማት ግብ 3 (Sustainable Development Goal 3) አተገባበርን አስመልክቶ የከፍተኛ ደረጃ የፖለቲካ መድረክ በሁሉም የዕድሜ ክልል ውስጥ ያሉ ሰዎች ደህንነት ማስፈንን እና ጤናማ ሕይወት ማረጋገጥን በማስመልከት ሐምሌ 7/2017 ዓ. ም. ባካሄደው እና ሴቶችን እና ልጃገረዶችን ለዘላቂ ልማት ማብቃት በማስመልከት ሐምሌ 8/2017 ዓ. ም. ባካሄደው ውይይት ላይ እንደሆነ ታውቋል።

ጤናማ ሕይወትን ማረጋገጥ እና ደህንነትን ማስተዋወቅ

በዘላቂ ልማት ግብ 3 (SDG3) አተገባበር ላይ ትኩረት ያደረጉት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ገብርኤል፥ ጤናማነት ከበሽታ ነጻ መሆን ብቻ ሳይሆን፥ የአካላዊ፣ ሥነ-ልቦናዊ፣ ማኅበራዊ፣ መንፈሳዊ እና ስሜታዊ ደህንነት አጠቃላይ ሁኔታ እና የሰው ልጅ ሁለንተናዊ ዕድገት ወሳኝ አካል መሆኑን አጽንኦት ሰጥተው አስፈላጊ እንደሆነም ጠቁመዋል።

ሆኖም ወደ ዘላቂ ልማት ግብ 3 ስኬታማነት የሚደረገው ግስጋሴ ያልተመጣጠነ እንደሆነ ገልጸው፥ “ደካማ የጤና ሥርዓቶች፣ በቂ ያልሆነ የገንዘብ ድጋፍ፣ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ክብደትን ጨምሮ የማያቋርጡ መሰናክሎች አሁንም የጤና አጠባበቅ አለመመጣጠነን እያባባሱት ይገኛሉ” ብለዋል።

እነዚህን ተግዳሮቶች ለማሸነፍ እና የሁሉን ሰው ጤና እና ደህንነት እውን ለማድረግ፥ ዘላቂ ልማት ግብ 3 ከሌሎች ግቦች ጋር ያለውን ትስስር የሚገነዘቡ አጠቃላይ እና የተቀናጁ ፖሊሲዎች ሊተገበሩ ይገባል ብለዋል።

የሁሉን ሰው ጤና እና ደህንነት ማረጋገጥ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ያሳሰቡት ቋሚ ታዛቢው፥ ትኩረቱ በተለይም አቅመ ደካሞችን ጨምሮ ገና ላልተወለዱት፣ ለሕጻናት፣ ለአዛውንቶች፣ ለአካል ጉዳተኞች፣ ለስደተኞች እና ግጭት በተከሰተባቸው አካባቢዎች ለሚኖሩ ሰዎች ልዩ ትኩረት ሊሰጥ እንደሚገባ ገልጸው፥ በዚህ ዐውድ ውስጥ ርዕዮተ ዓለማዊ ወይም ኢኮኖሚያዊ አጀንዳዎች የጤና እንክብካቤ ሥርዓትን ፈጽሞ መቅረጽ እንደሌለባቸው፥ ሥርዓቱ  ከሁሉም በፊት ሰውን ያማከለ ሊሆን እንደሚገባ አሳስበዋል።

በዚህም ምክንያት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ገብርኤል፥ የካቶሊክ የጤና ተቋማትን ጨምሮ የእምነት ድርጅቶች ወሳኝ ሚና እንደሚጫወቱ፥  ከእነዚህ ተቋማት ጋር ያለውን ትብብር ማጠናከር የጤና አጠባበቅ ሰውን ያማከለ እንዲሆን ለማድረግ ይረዳል ብለዋል።

ለጤና አጠባበቅ ትርጉም ያለው አስተዋፅዖን ከማድረግ አንፃር ሊቀ ጳጳስ አቡነ ገብርኤል፥ በዓለም ዙሪያ ካሉት የጤና ተቋማት ሩብ ያህሉን የምታስተዳድረው ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን እንደሆነች ገልጸው፥ ለድሆች እና ራቅ ባሉ አካባቢዎች ለሚኖሩ ሕዝቦች እንክብካቤን መስጠት እንደምትቀጥል አስረድተዋል።

የሥርዓተ ፆታ እኩልነትን ማሳካት፣ ሁሉንም ሴቶች እና ልጃገረዶች ማብቃት

ቋሚ ታዛቢው፥ በማግስቱ የተካሄደውን የዘላቂ ልማት ግብ 5 የሥርዓተ ፆታ እኩልነት ለማስፈን እና የሁሉንም ሴቶች እና ልጃገረዶች ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተዘጋጀውን ውይይት በደስታ ተቀብለውታል።

“የሥርዓተ ፆታ እኩልነት የተመሠረተው እግዚአብሔር ለእያንዳንዱ ወንድ እና ሴት በሰጠው የእኩልነት  ክብር ላይ ነው” ብለው፥ “ይህም በወንድ ወይም በሴት የማይሻር ማንነት ላይ የተመሠረተ፣ በሁሉም ሁኔታዎች ውስጥ እና ከዚያ በላይ እውነትነቱ የተረጋገጠ ነው” ብለዋል።

ሊቀ ጳጳስ አቡነ ገብርኤል ለዚህ የእኩል ክብር እውቅናን መስጠት የዘላቂ ልማት ግብ 5ን (SDG 5) ለማሳካት ወሳኝ መነሻ ነው ብለው፥ ነገር ግን ዕውቅናን መስጠት ብቻውን በቂ እንዳልሆነ ተናግረዋል። “እኩልነት የሴቶች እና ልጃገረዶች ሁለንተናዊ ዕድገት፣ ጥራት ያለው የትምህርት እና የጤና አገልግሎት የማግኘት እና ለሴቶች በሁሉም የሕይወት ዘርፍ ጨዋነት ያለውን የሥራ ዕድል እና ተሳትፎ የሚያግዙ ሁኔታዎችን መፍጠርን ይጠይቃል” ብለዋል።

በዘላቂ ልማት ግብ 5 ላይ የሚደረግ ማንኛውም ትርጉም ያለው ውይይት ድህነትን፣ ጥቃትን እና መገለልን ማስወገድ ጨምሮ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሴቶች እና ልጃገረዶች በሁለንተናዊ ዕድገት ላይ ያሉ ሥርዓታዊ እንቅፋቶችን መፍታት አለበት ብለዋል።

“እነዚህን ኢ-ፍትሃዊ ድርጊቶች መፍታት የሞራል ግዴታ እና የረዥም ጊዜ ልማት እና ዕድገት ቅድመ ሁኔታ ነው” ሲሉ አስምረውበት፥ በዚህም ሴቶች እና ወንዶች በቤተሰብ እና በማኅበረሰቦች ውስጥ የሚጫወቱት ሚና ሊጠበቅ እንደሚገባ አጥብቀው ተናግረዋል።

ቤተሰብን፣ እናትነትን እና ወላድነትን የሚደግፉ እና የሚያስጠብቁ ፖሊሲዎች በሴቶች እና በወንዶች መካከል ያለውን እኩልነት ከማስፈን ጎን ለጎን ሊተገበሩ እንደሚገባ የተናገሩት ቋሚ ታዛቢው፥ የሴት እና የልጃገረድ ክብር ምንጊዜም የልማት ጥረቶች ማዕከል መሆን እንዳለበት፣ ሴቶችን ኢኮኖሚያዊ ወይም ፖለቲካዊ አጀንዳ ብቻ እንዲሆኑ የሚያደርጉ አቀራረቦች መወገድ እንዳለባቸው አሳስበዋል።

በተባበሩት መንግሥታት የቅድስት መንበር ቋሚ ታዛቢ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ገብርኤል ካቻ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ገብርኤል በመጨረሻም፥ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ የ2030 አጀንዳ እውንነት እስኪፈጸም ድረስ ባሉት አምስት ዓመታት ውስጥ ልዑካን ቡድናቸው፥ “ለእያንዳንዷ እናት እና ልጃገረድ ሁለንተናዊ ዕድገት አዲስ ቁርጠኝነት እንዲኖር ይጠይቃል” ብለዋል።

17 Jul 2025, 13:18