ሐዋርያዊት መንበር ንብረቶችዋን የምታስተዳደርበት መንገድ ሲቃኝ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
የሐዋርያዊ መንበር የንብርት እና የፋይናንስ አስተዳደር ሥራ አገልግሎቱን በከፍተኛው ግልጽነት የሚያቀርብ ነው። ይህ በተለይ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከተጀመረው ተሐድሶ ጀምሮ በግልጽ እየታየ የመጣ ነው። የቅድስት መንበር የንብርት እና ፋይናንስ አስተዳደር (ኤፒኤስኤ) የቅድስት መንበር ንብረት የማስተዳደር ኃላፊነት ያለበት አካል ሲሆን፥ በአሁኑ ጊዜ የሚመራው በአባ ፋቢዮ ጋስፔሪኒ ፀሐፊነት በሳሌዥያዊ ጳጳስ በአቡነ ጆርዳኖ ፒቺኖቲ የሚመራ ነው።
ታሪካዊ ዳራው
የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ ሦስተኛ፥ በጊዜያቸው የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ የነበሩትን ብጹዕ ካርዲናል ኒናን እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ 1878 ዓ. ም. የቅዱሳን ሕንጻዎች አስተዳዳሪ አድርገው መሾማቸው ይታወሳል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ ሦስተኛ በገዛ ሐዋርያዊ ሥልጣናቸው እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ሚያዝያ 30/1891 ዓ. ም. ኮሚሽኑ የቅዱስ ጴጥሮስ የዕርዳታ ማሰባሰብ መርሃ ግብርን ሌሎች ቅርንጫፎችን እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮችን መቆጣጠርን ጨምሮ ሌሎች የቅድስት መንበር ንብረት በቀጥታ እንዲያስተዳድር እና እንዲከታትል አደራ ሰጡት።
የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፒዮስ 11ኛ፣ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በታኅሣሥ ወር 1926 ዓ. ም. በገዛ ሐዋርያዊ ሥልጣናቸው የከፍተኛ ጳጳሳዊ የአስተዳደር ጽሕፈት ቤቶች እና ልዩ ልዩ ክፍሎች ከቅድስት መንበር ጠቅላላ የንብረት አስተዳደር ጋር እንዲዋሃዱ አዘዙ።
ስለዚህ ከፍተኛ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ሁለት ክፍሎች ያሉት ሲሆን እያንዳንዳቸው በተወካዮቻቸው የሚመሩ ሲሆን፥ ቀደም ሲል ለቅድስት መንበር የንብረት አስተዳደር የተሰጠውን ተግባር ያከናውን የነበረው መደበኛ ክፍል እና እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በየካቲት 11/1929 በ ላተራን ስምምነት ውስጥ በተካተተ የፋይናንስ ስምምነት አፈፃፀም የጣሊያን መንግሥት ለቅድስት መንበር የሚከፍለውን ገንዘብ ለማስተዳደር በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፒዮስ 11ኛ በገዛ ሥልጣን በሰኔ ወር 1929 የተቋቋመ እና ቀደም ሲል በቅድስት መንበር ልዩ አስተዳደር የተሰጡትን ኃላፊነቶች የመወጣት ኃላፊነት የነበረበት ነው።
የተደረጉ ማሻሻያዎች እና የቅርብ ጊዜ ዕድገቶች
የሐዋርያዊ መንበረ የንብረት አስተዳደር፥ የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ጳውሎስ ስድስተኛ፥ “Regimini Ecclesiae Universae” ወይም ሁለንተናዊ የቤተ ክርስቲያን ቁጥጥር” በሚለው በሐዋርያዊ ደንብ መሠረት እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ነሐሴ 15/1967 ዓ. ም. የተመሠረተ ሲሆን፥ ተልዕኮውም በቅድስት መንበር የተያዙ ንብረቶችን ማስተዳደር እና በሌሎች የቅድስት መንበር አካላት እጅ ውስጥ የሚገኙትን ንብረቶች የማስተዳደር ተግባር ሲሆን ይህም የሮማ ኩሪያን ተግባራት ለማስፈጸም አስፈላጊ የገንዘብ ድጋፍ ለመስጠት የታሰበ ነበር።
ነፍስሔር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በሐምሌ 8/2014 ዓ. ም. በገዛ ሐዋርያዊ ስልጣናቸው በሰጡት መግለጫ፣ አዲስ የተቋቋመው የኢኮኖሚ ጽሕፈት ቤት ከተቋማዊ ኃላፊነቱ መካከል የሐዋርያዊ መንበረ ንብረት አስተዳደር እየተባለ የሚጠራበትን ኃላፊነት እንዲወጣ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ1988 ዓ. ም. “Pastor Bonus” ወይም “መልካሙ እረኛ” በሚለው ሐዋርያዊ ደንብ የተሰየበትሙ የሥራ ብቃት ወደ ጽሕፈት ቤትነት እንዲዛወር ወስነዋል።
በአሁኑ ጊዜ የሐዋርያዊ መንበረ ንብረት አስተዳደር ጽሕፈት ቤት የሚተዳደረው፥ ነፍስሔር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በገዛ ሐዋርያዊ ሥልጣናችው እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ሐምሌ 4/2016 ዓ. ም. ባጸደቁት በሐዋርያዊ መንበረ የንብረት አስተዳደር እና በኢኮኖሚ ጽሕፈት ቤት መካከል ያለውን የኃላፊነት ክፍፍል በሚያጎላ ጊዜያዊ ደንብ ነው።
የቀድሞው በንብረት እና በፋይናንስ አስተዳደር ላይ ኃላፊነት ያለበት ሲሆን፥ ኋለኛው ደግሞ በበላይነት የአስተዳደር እና ቁጥጥር እንቅስቃሴዎችን ይከታተላል።
እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በግንቦት ወር 2020 ታትሞ በወጣው ጽሑፍ መሠረት፥ ነፍስሔር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የቅድስት መንበር ኢኮኖሚያዊ እና ፋይናንሻል መረጃ ዳታ ማቀነባበሪያ ማዕከል (ሲኢዲ) ምክንያታዊ አደረጃጀትን የበለጠ ለማረጋገጥ እና ዋና ሞዴሎችን እና ሂደቶችን ዲጂታል ለማድረግ ኃላፊነቱ ከሐዋርያዊ መንበረ የንብረት አስተዳደር “APSA” ወደ ኢኮኖሚው ጽሕፈት ቤት እንዲተላለፍ አዘዙ።
ነፍስሔር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመጨረሻም፥ በገዛ ሐዋርያዊ ሥልጣናቸው እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በታኅሳስ ወር 2020 ዓ. ም. በወጡ አንዳንድ ኢኮኖሚያዊ እና ፋይናንስ ጉዳዮች ላይ ለሐዋርያዊ መንበረ የንብረት አስተዳደር “APSA” የፋይናንስ ኢንቨስትመንቶችን እና በቅድሳት መንበር ጽሕፈት ቤት ባለቤትነት የተያዘውን የሪል እስቴት የአስተዳደር እና የቁጥጥር አደራ ሰጥተዋል።
እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት
ነፍስሔር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ “Praedicate Evangelium” ወይም “ወንጌልን ስበኩ” በሚል ርዕሥ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ 2022 ዓ. ም. ይፋ ባደረጉት ሐዋርያዊ ደንብ መሠረት የሐዋርያዊ መንበረ ንብረት አስተዳደር (APSA) የቅድስት መንበር ተንቀሳቃሽ እና የማይንቀሳቀሱ ንብረቶችን የማስተዳደር እና የመቆጣጠር አደራ የተሰጠው አካል ነው። ይህም የሮማ ኩሪያ አገልግሎቱን ለቤተ ክርስቲያናት ጥቅም እና አገልግሎት አስፈላጊውን ግብዓት እንዲያቀርብ በማለት ነው።
የሐዋርያዊ መንበረ ንብረት አስተዳደር (APSA)፥ ልዩ ልዩ አካላት ለቅድስት መንበር ያበረከቱትን ንብረቶችን፣ የሪል እስቴት እና የፋይናንሺያል ሃብትን ለመከታተል የተቋቋመበትን ልዩ ዓላማ የማስተዳደር ኃላፊነት አለበት። የፋይናንስ እንቅስቃሴዎች የሚካሄዱት በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ ሃይማኖታዊ ሥራዎችን ለሚያካሂዱ የቤተ ክርስቲያኒቱ ተቋማት ገንዘብ በሚያቀርብ (IOR) ተቋም አማካይነት ነው።
የሐዋርያዊ መንበረ ንብረት አስተዳደር (APSA) የሮማን ኩሪያ መደበኛ እንቅስቃሴዎች፣ የግምጃ ቤት ሥራዎችን፣ የሂሳብ አያያዝን፣ ግዥን እና ሌሎች አገልግሎቶችን በመቆጣጠር አስፈላጊነቱን ያረጋግጣል። ከቅድስት መንበር ጋር ግንኙነት ያላቸው ተቋማት የድጋፍ ጥያቄ የሚያቀርቡ ከሆነ ተመሳሳይ አገልግሎት ሊሰጥ ይችላል።
የሐዋርያዊ መንበረ ንብረት አስተዳደር (APSA) በሦስት ውስጣዊ የተግባር አደረጃጀት ዘርፎች የተዋቀረ ሲሆን፥ እነርሱም የሪል እስቴት አስተዳደር፣ የገንዘብ ጉዳዮች እና አስተዳደራዊ አገልግሎቶች ናቸው።