በኢትዮጵያ አዲስ የተሾሙት የቅድስት መንበር ሃዋሪያዊ ተወካይ አዲስ አበባ ሲደርሱ ደማቅ አቀባበል ተደረገላቸው
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
ነፍስሄር ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ከዚህ ዓለም ድካም ከማረፋቸው ጥቂት ቀናት ቀደም ብሎ ሚያዝያ 4 ቀን 2017 ዓ.ም. ሊቀ ጳጳስ ብሪያን ንጎዚን በኢትዮጵያ የቅድስት መንበር ሃዋሪያዊ ተወካይ አድርገው መሾማቸው የሚታወስ ሲሆን፥ ይሄንን ተከትሎ ብጹእነታቸው ባለፈው ሰኔ 12 ቀን 2017 ዓ.ም. ወደ ኢትዮጵያ ሲገቡ በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ደማቅ አቀባበል ተደርጎላቸዋል።
ብፁዕነታቸው አዲስ አበባ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ ብፁዕ ካርዲናል አቡነ ብርሃነኢየሱስ ሊቀ ጳጳሳት ዘካቶሊካውያን፣ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ብጹአን ጳጳሳት እና ካህናት አቀባበል ያደረጉላቸው ሲሆን፥ በኋላም በኢትዮጵያ የቅድስት መንበር ጽህፈት ቤት የቤተክርስቲያኒቱ ሃላፊዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የዲፕሎማቲክ አካላት እና ምእመናን ብጹእነታቸው ወደ ኢትዮጵያ ተመድበው በመምጣታቸው የተሰማቸውን ደስታ በመግለጽ አቀባበል አድርገውላቸዋል።
በናይጄሪያ የሚገኘው የኦርሉ ሀገረ ስብከት ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን አባል የሆኑት ሊቀ ጳጳስ ኡዳግዌ የትውልድ ቦታቸው በደቡብ ምዕራብ ካሜሩን ሲሆን፥ እ.አ.አ. ግንቦት 2 ቀን 1992 ዓ.ም. የክህነት ማዕረግ እንደተቀበሉ እና ሮም በሚገኘው ጳጳሳዊ ኮሌጅ የትምህርት ዝግጅታቸውን በማጠናቀቅ በ 1994 ዓ.ም. በቅድስት መንበር የዲፕሎማቲክ አገልግሎት እንደጀመሩ መረጃዎቻቸው ያሳያሉ።
ሊቀ ጳጳስ ኡዳግዌ ኢትዮጵያ ላይ ከመሾማቸው በፊት በቅድስት መንበር የዲፕሎማቲክ አገልግሎት ከሦስት አስርት ዓመታት በላይ እንዳስቆጠሩ እና ለኢትዮጵያ 13ኛው የቅድስት መንበር ተወካይ እንደሆኑ የተገለጸ ሲሆን፥ ብፁዕነታቸው ለኢትዮጵያ እስከተሾሙበት ጊዜ ድረስ በሲሪላንካ የቅድስት መንበር ሃዋሪያዊ ተወካይ እንደነበሩ እና ከዚያም በፊት በነበራቸው በርካታ የአገልግሎት ዓመታት በዚምባቡዌ፣ በአይቮሪ ኮስት፣ ሃይቲ፣ ቡልጋሪያ፣ ታይላንድ፣ በእንግሊዝ፣ በቤኒን እና በቶጎ ቅድስት መንበርን በመወከል ለዘመናት በዲፕሎማቲክ ዘርፍ በማገልገል ጠንካራ ልምድ እንዳካበቱ ተገልጿል።
በጎረጎሳዊያኑ የዘመን አቆጣጠር ግንቦት 2 ቀን 1992 ዓ.ም. ማዕረገ ክህነት የተቀበሉት ሊቀ ጳጳስ ኡዳግዌ፥ ሐምሌ 1 ቀን 1994 ዓ.ም. በቅድስት መንበር ዲፕሎማሲያዊ አገልግሎት ከመጀመራቸው በፊት ሮም በሚገኘው ጳጳሳዊ የነገረ መለኮት ከፍተኛ የትምህርት ተቋም ትምህርታቸውን እንደተከታተሉ ተገልጿል።
የካቲት 22 ቀን 2013 ዓ.ም. በርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት በነዲክቶስ 16ኛ የቲቱላር ሊቀ ጳጳሳ እና በሱዌሊ የቅድስት መንበር ሐዋርያዊ ተወካይ ሆነው የተሾሙ ሲሆን፥ እንደገና ሚያዝያ 27 ቀን 2013 ዓ.ም. በብፁዕ ካርዲናል ታርቺስዮ በርቶኔ በተመራ መስዋዕተ ቅዳሴ ሢመተ ጵጵስናቸው ተፈጽሟል።
በኋላም በ2013 ዓ.ም. በቤኒን ሃገር እና በመቀጠልም ወደ ቶጎ በመጓዝ የቅድስት መንበር ሃዋሪያዊ ተወካይ ሆነው ያገለገሉ ሲሆን፥ ከዚያም ከሰኔ 13 ቀን 2020 ዓ.ም. ጀምሮ ኢትዮጵያ ላይ እስከተሾሙበት ቀን ድረስ በስሪላንካ ማገልገላቸው ተነግሯል።
በአቀባበል ሥነ-ሥርዓቱ ወቅት በኢትዮጵያ የቅድስት መንበር ጽህፈት ቤት ዋና ጸሃፊ ሞንሲኞር ማሲሞ ካተሪን ሊቀ ጳጳስ ኡዳግዌ ወደ ኢትዮጵያ ተመድበው በመምጣታቸው የተሰማቸውን ልባዊ ደስታ ገልጸው፣ መልካም የሥራ ዘመን እንዲሆንላቸው ተመኝተውላቸዋል።
ከዚህም ባለፈ ሞንሲኞር ማሲሞ ይህን ሹመት ልዩ የሚያደርገው የቀድሞው ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ሊቀ ጳጳሱን ወደ ኢትዮጵያ የላኩት ሕይወታቸው ሊያልፍ ዘጠኝ ቀናት ሲቀረው እንደሆነ እና ይህም ቅዱስ አባታችን ለኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የነበራቸውን ልዩ ትኩረት የሚያሳይ እንደሆነ ጠቁመው፥ “እርስዎ አባታችን እንደመሆንዎ መጠን፣ እኛም ልጆችዎ እንሆናለን፣ ካለዎት የካበተ ልምድ ለመማር ዝግጁ ነን” በማለት ጽህፈት ቤታቸው ለብጹእነታቸው ሙሉ ድጋፍ እና ትብብር እንደሚያደርግላቸው አረጋግጠውላቸዋል።
ሊቀ ጳጳስ ኡዳጊዌ በበኩላቸው ባደረጉት ንግግር ኢትዮጵያ የበርካታ አፍሪካ ሀገራት መናኸሪያ በመሆኗ ያላትን ተደማጭነት ሚና በመጥቀስ፥ ሃገሪቷ ባላት ታሪካዊ እና መንፈሳዊ ፋይዳ ያላቸውን ጥልቅ አድናቆት ገልጸዋል።
ሊቀ ጳጳሱ አክለውም “ለእግዚአብሔር ክብር” የጋራ የሆነ የመደጋገፍ እና የትብብር አስፈላጊነትን በማጉላት፣ ለዚህም የአጥቢያ ቤተ ክርስቲያንን ጥረት ካመሰገኑ በኋላ፥ ልዩ የሆነውን የሹመታቸውን ሁኔታ አስመልክተው እንደተናገሩት ሂደቱ በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ወቅት መጀመሩን እና በርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ መጠናቀቁን አስረድተው፥ ይህም ኢትዮጵያ ላይ የተሰጣቸው ተልዕኮ በቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ውስጥ የተለየ እና ትርጉም ያለው ጉዞ መሆኑን ያሳያል ብለዋል።
ዓመታትን የተሻገረውን ዲፕሎማሲያዊ እና ሃዋሪያዊ ልምዳቸውን ይዘው ወደ ኢትዮጵያ የመጡት ሊቀ ጳጳስ ኡዳግዌ፥ የኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ቀንድ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ከቅድስት መንበር እና ከርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ጋር ያላቸውን ግንኙነት አጠናክረው እንዲቀጥሉ የተቻላቸውን ሁሉ ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።