ቅድስት መንበር፥ ድህነትን ለመፍታት አስቸኳይ የሞራል ኃላፊነት እንደሚያስፈልግ አስታወቀች
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣው ወታደራዊ ወጪ በልማት ዘርፎች ዙሪያ እንደ ጤና አጠባበቅ፣ ትምህርት እና መሠረተ ልማት ላሉት የዕድገት ውጥኖች የሚውለውን ከፍተኛ ሃብት የሚያስቀይር መሆኑ እንዳሳሰባት ቅድስት መንበር አስታውቃለች።
በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የቅድስት መንበር የቋሚ ታዛቢ፥ ሞንሲኞር ማርኮ ፎርሚካ ይህን የቅድስት መንበር ስጋት የገለጹት፥ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት፥ ዓለም አቀፍ ሰላምን እና ደኅንነትን አስመልክቶ በድህነት፣ በልማት እጦት እና በግጭት ዙሪያ ሰኔ 16/2017 ዓ. ም. ባካሄደው ግልጽ የውይይት መድረክ ላይ እንደ ነበር ታውቋል።
የድህነትን መንስኤዎችን ለመፍታት የሚያስችል አስቸኳይ የሞራል ሃላፊነት
የቅድስት መንበር የቋሚ ታዛቢ ሞንሲኞር ማርኮ ፎርሚካ በንግግራቸው መጀመሪያ፥ ግልጽ ውይይቱ ትኩረትን ለመሳብ ያለመ መሆኑን በመገንዘብ፥ በድህነት፣ በልማት እጦት እና በግጭት ውስጥ ያሉ ተያያዥነት ያላቸው እና የተሳሰሩ ተግዳሮቶች እውነታ፥ ብዙውን ጊዜ እርስ በርስ የሚጋጩ እና ለዓለም አቀፍ ሰላም እና ደኅንነት ከፍተኛ እንቅፋት የሚፈጥሩ መሆናቸውን አስረድተዋል።
እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ 2030 ዓ. ም. ተፈጻሚ ይሆናል ተብሎ የታሰበውን የዘላቂ ልማት አጀንዳን ያስታወሱት ሞንሲኞር ማርኮ ፎርሚካ፥ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ድህነትን በሁሉም መልኩ እና መጠን ማጥፋት ታላቅ ዓለም አቀፍ ተግዳሮት እና የማይታለፍ የዘላቂ ልማት መስፈርት መሆኑን በመገንዘብ፥ ይህ የጋራ ቁርጠኝነት የድህነትን ዋና መንስኤዎች ለመፍታት ከፍትሕ መጓደል፣ ከማግለል እና ከመሠረታዊ መብቶች ጋር ተያይዞ የሚመጣውን አስቸኳይ የሞራል ኃላፊነት የሚያጎላ መሆኑን አስታውሰዋል።
ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የሄደው የወታደራዊ ወጪ ስጋት
በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የቅድስት መንበር የቋሚ ታዛቢ ሞንሲኞር ማርኮ ፎርሚካ በዚህ ረገድ፥ “ቅድስት መንበር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የሄደው ወታደራዊ ወጪ፥ በልማት ዘርፎች እንደ ጤና አጠባበቅ፣ ትምህርት እና መሠረተ ልማት ሊውሉ ከሚገቡ መዋዕለ ነዋያት ውስጥ ከፍተኛ ሃብትን ማጥፋቱ ቅድስት መንበርን ያሳስባታል” ብለዋል።
“በዚህ ዐውደ ውስጥ ቅድስት መንበር በአሁኑ ወቅት ለጦር መሣሪያ የተመደበውን ሃብት በከፊል ማዘዋወርን የሚደግፍ ዓለም አቀፍ ፈንድ ለማቋቋም ያቀረበችውን ሐሳብ አድሳለች” ብለው፥ ፈንዱ ድህነትን እና ረሃብን ለማጥፋት፣ በዓለም ላይ እጅግ በተጎዱ ክልሎች ልማትን ለማስፋፋት ትርጉም ያለውን አስተዋፅኦ ሊያበረክት ይችላል” ብለዋል። “በዚህም የበለጠ ፍትሃዊ እና ዘላቂ የሰላም መንገድን ማስቀጠል፣ ሰብዓዊ ክብርን ማስጠበቅ እና ማስፋፋት ይቻላል” ብለዋል።
እግዚአብሔር ለእያንዳንዱ ሰው የሰጠው ክብር ነው
በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የቅድስት መንበር የቋሚ ታዛቢ ሞንሲኞር ማርኮ ፎርሚካ፥ ዘላቂ ሰላም ለሰው ልጅ ሁለንተናዊ ልማት ቁርጠኝነት አስፈላጊ እንደሆነ፣ የእያንዳንዱን ሰው ክብር ለማስጠበቅ፣ ፍትህ እና አብሮነት እንዲያብብ ለማድረግ እና ሁኔታዎችን ለማስተዋወቅ ቁርጠኝነት መኖሩ አስፈላጊ እንደሆነ በማስረዳት፥ “ቀጣይነት ባለው የሰላም ግንባታ ውስጥ የሰው ልጅ ዕድገት ማዕከላዊነት ወሳኝ መሆኑን በማጉላት፥ በአባል አገራት መካከል ያለው ዘላቂ ትብብር ሰብዓዊ ልማትን በማስቀጠል ረገድ አስፈላጊ እንደሆነ ቅድስት መንበር አጽንኦት ሰጥታለች” ብለዋል።