MAP

ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ በቅድስት መንበር ኢዮቤልዩ በዓል ላይ ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ በቅድስት መንበር ኢዮቤልዩ በዓል ላይ   (ANSA)

የቅድስት መንበር እንደራሴ ተግባር የወንጌል ዲፕሎማሲን ተከትሎ ሰላምን መዝራት እንደሆነ ተገለጸ

የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብፁዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን፥ የቅድስት መንበር ኢዮቤልዩ በዓልን ምክንያት በማድረግ ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ጋር የሚያደርጉትን ግንኙነት በማስመልከት ቃለ ምልል አድርገዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ብፁዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን ከቫቲካን ሚዲያ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፥ “የቅድስት መንበር ሐዋርያዊ እንደራሴ ጽሕፈት ቤቶች ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳትን በየአገራቱ ከሚገኙ አብያተ ክስቲያናት፣ ቤተ ክርስቲያንን ከመንግሥታት እና የቆሰለውን ዓለምን ከወንጌል ተስፋ ጋር የሚያገናኙ ድልድዮች ናቸው” ሲሉ ገልጸዋቸዋል።

ብፁዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን ከዚህ ጋር በማያያዝ፥ “የቅድስት መንበር ጳጳሳዊ ተወካይ የቅዱስ ወንጌል ዲፕሎማሲ የሚያራምድ፥ ራሱን ለሽምግልና እና ለውይይት የሚሰጥ እና የሰላም ዘሪ የመሆን ግዴታ አለበት” ሲሉ ተናግረዋል።

ብፁዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን፥ ሰኔ 2/2017 ዓ. ም. የተከበረውን የቅድስት መንበር ኢዮቤልዩ በዓል እና እንዲሁም የቅድስት መንበር ሠራተኞች ማክሰኞ ሰኔ 3/2017 ዓ. ም. ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ጋር የሚያደርጉትን ስብሰባ በማስመልከት ከቫቲካን መገናኛ ብዙኃን ጋር ቃለ ምልልስ አድርገዋል።

የቅድስት መንበር ኢዮቤልዩ በዓል ቤተ ክርስቲያን ከዓለም ጋር እንዴት መሥራት እንዳለባት ለማሰላሰል ዕድል እንደሚሰጥ እና በቅድስት መንበር ሥር በሚገኙ ዲፕሎማሲያዊ አካላት በተለይም ለቅድስት መንበር ሐዋርያዊት እንደራሴዎች ከፍተኛ ፋይዳ እንዳለው የገለጹት ብፁዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን፥ በዓሉ ለቅድስት መንበር ሠራተኞች እንስ እንዲሁም ለጳጳሳዊ ተወካዮችም ጠቃሚ የአንድነት ጊዜ እንደሆነ ገልጸዋል።

ጳጳሳዊ ተወካዮች እያንዳንዳቸው በአንድ ቦታ ብቻ በቋሚነት የሚሠሩ ሳይሆን ነገር ግን በቀጣይነት ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ተዛውረው የሚሠሩ እንደሆነ፥ ቢሆንም የብቸኝነት ሳይሆን ከሌሎች ጋር በኅብረት የሚሠሩ እንደሆነ ገልጸው፥ “ይህ ተልዕኮ ገና አንድ ባልሆነ ዓለም ውስጥ ወደየአገራቱ ተልከው የሚሠሩትን ወደ ሮም በመጥራት ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ጋር የሚያገናኝ የቤተሰባዊነት ምስልን ወደ አእምሮው የሚያመጣ ነው” ሲሉ አስረድተዋል።

ከቅዱስነታቸው ጋር የሚደረግ ስብሰባ በቤተ ክርስቲያኗ አካባቢያዊ እና ሁለንተናዊ ልኬቶች መካከል ያለውን ትስስር ግልጽ እንደሚያደርገው የገለጹት ብፁዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን፥ ጳጳሳዊ ተወካይ ከሁሉ በፊት የኢየሱስ ክርስቶስ አገልጋይ በሆኑት በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት እና በተላከባቸው ማኅበረሰቦች መካከል ድልድይ ሆኖ እንደሚሠራ ተናግረው፥ እንደዚሁም በተመሳሳይ መንገድ በአገራቱ በሚገኙ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያናት እና በሐዋርያዊ መንበር መካከል ያለውን ግንኙነት የሚያጸና እንደሆነ በማስረዳት በማከልም፥ የቅድስት መንበር ጽሕፈት ቤትም በሮም እና በመላው ዓለም የሚገኙ ጳጳሳዊ ተወካዮች ተልዕኮን በመደገፍ ይህንን አንድነት የማስተባበር ሚና እንደሚጫወት ተናግረዋል።

በየአገራቱ የሚገኙ የቅድስት መንበር ሐዋርያዊ እንደራሴዎች በእርግጥም ለመንግሥታት እና ለዓለም አቀፍ ተቋማት የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ተወካዮች እንደሆኑ የገለጹት ብፁዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን፥ ከዚህ አንፃር ሚናቸው በግልጽ ዲፕሎማሲያዊ በመሆኑ ከሲቪል ባለስልጣናት ጋር መቀራረብ፣ ልዩነትን ለመፈወስ መሥራት እና ሰላምን፣ ፍትህን እና የእምነት ነፃነትን ማሳደግ እንደሆነ ተናግረው፥ “ይህንን የሚያደርጉት ብሔራዊ ጥቅምን ለማስከበር ሳይሆን ነገር ግን ወንጌልን ማዕከል ባደረገ በአለም አቀፍ ግንኙነት ራዕይ በመመራት ነው” ሲሉ አስረድተዋል።

ይሁን እንጂ ሚናቸውን ወደ ተቋማዊነት ብቻ ዝቅ ማድረግ የማይቻል እና በእውነተኛ ሐዋርያዊ መገኘት ላይ የተመሠረተ መሆን እንዳለበት፥ የቅድስት መንበር ሐዋርያዊ እንደራሴ መሆን ስለሌሎች ኃላፊነት የካኅን ግንዛቤ ያለው፣ የቤተ ክህነት አመለካከትን የሚጠይቅ፥ ከምንም በላይ የቤተ ክርስቲያን ሰው፣ መጋቢ እና የመልካም እረኛውን የኢየሱስ ክርስቶስን ምሳሌ እንዲከተል የተጠራ እንደሆነ፥ መጋቢ መሆን ማለት ለጳጳሳት፣ ለካኅናት፣ ለገዳማውያን እና ገዳማውያት እንዲሁም ለማገልገል ወደ ተላኩ ማኅበረሰቦች ቅርብ የሆነ ማለት እንደሆነ አስረድተዋል።

“በዚህ መንገድ የቅድስት መንበር ሐዋርያዊ እንደራሴ፥ በሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ተተኪ እና በአገራት አብያተ ክርስቲያናት መካከል፣ በቤተ ክርስቲያን እና በመንግሥታት መካከል እንዲሁም በቆሰለው ዓለም እና በቅዱስ ወንጌል ተስፋ መካከል ድልድይ ይሆናል” ብለዋል።

በተለይም ዛሬ ባለው ውስብስብ ታሪካዊ አውድ ውስጥ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ተወካይ አስፈላጊ ባሕርያት ሦስት እንደሆኑ የተናገሩት ብፁዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን፥ በመጀመሪያ ከልብ የሚመነጭ ትሕትና እንደሆነ እና ይህም አንድ ሰው ራሱን ዝቅ እንዲያደርግ እና እግዚአብሔር በእርሱ በኩል ታላላቅ ነገሮችን ማከናወን እንደሚችል እንዲተማመን ያስችለዋል ብለዋል። በጥላቻ እና በዓመፅ በተሞላ ዓለም ውስጥ ተስፋ የመቁረት አደጋ መኖሩን ገልጸው፥ ሆኖም አስቸጋሪ ወይም ያልተጠበቁ ኃላፊነቶች ሲያጋጥሙን፣ ከተልዕኮው ጋር አብሮት በሚጓዝ እና በሚደግፍ ጸጋ ላይ እምነት እንድሚያደርጉ አስረድተዋል።

ከትሕትና ጎን ለጎን ለወንጌል ቅንዓትን አጽንዖት የሰጡት ብፁዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን፥ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ተወካይ የወንጌል ዲፕሎማሲ አራማጅ እንደሆነ ተናግረው፥ የኢየሱስ ክርስቶስን ብርሃን ራቅ ወዳሉ የምድር ማዕዘናት የማምጣት አደራ እንዳለበት አስረድተዋል።

በመጨረሻም የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ተወካይ የእርቅ ሰው መሆን እንዳለበት የተናገሩት ብፁዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን፥ የጳጳሳዊ ዲፕሎማሲ ተልዕኮ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት፥ በእውነት፣ በፍትህ እና በሰላም ላይ የተመሠረተ ዓለምን ለመገንባት የሚያደርጉትን ጥረት መደገፍ እንደሆነ ገልጸው፥ በዛሬው ዐውደ ውስጥ ጳጳሳዊ ተወካይ ራሱን ለሽምግልና እና ለውይይት እንዲሰጥ የተጠራ፣ ይህም በተከፋፈሉ ወገኖች መካከል ያለውን የሰላም ፍላጎት ለመለየት ብቸኛው መንገድ ይህ እንደሆነ አስረድተዋል።

 

10 Jun 2025, 17:20