MAP

በሶርያ ውስጥ የሚካሄደው የፀረ-ሰው ፈንጂ የማምከን ሥራ በሶርያ ውስጥ የሚካሄደው የፀረ-ሰው ፈንጂ የማምከን ሥራ   (ANSA)

ቅድስት መንበር፥ አገራት የተባበሩት መንግሥታት የፀረ-ፈንጂ ስምምነትን እንዲያፀድቁ አሳሰበች

ቅድስት መንበር በልማት እና ትጥቅ በማስፈታት መካከል ያለውን ግንኙነት በማረጋገጥ አገራት የፀረ-ሰው ፈንጂ ኮንቬንሽን እንዲያጸድቁ አሳሰበች።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የቅድስት መንበር ቋሚ ታዛቢ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ኤቶሬ ባሌስትሬሮ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ዘንድሮ በ2025 ዓ. ም. በተዘጋጀው የፀረ-ሰው ፈንጂዎች ኮንቬንሽን ጉባኤ ላይ ተገኝተው ንግግር አድርገዋል።

በኦስሎ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ1997 ዓ. ም. ለመጀመሪያ ጊዜ የቀረበው እና በ1999 ሥራ ላይ የዋለውን የኦቶዋ ኮንቬንሽን በመባል የሚታወቀው “የማርሻል ደሴቶች የፀረ-ሰው ፈንጂ የጦር መሣሪያ ስምምነት” በቅርቡ መጽደቁ ቅድስት መንበርን ያስደሰታት መሆኑን ሊቀ ጳጳስ አቡነ ኤቶሬ ባሌስትሬሮ ዓርብ ሰኔ 13/2017 ዓ. ም. ባሰሙት ንግግር ገልጸዋል።

ሊቀ ጳጳስ አቡነ ባሌስትሬሮ፥ በፈንጂ የተጎዱ ሰዎችን በእጅጉ ለመርዳት እና ተጨማሪ ጉዳቶችን ለመከላከል የሚያስችል አቅም እንዳለው በመግለጽ፥ ኮንቬንሽኑን የማጽደቅ ዋና ዓላማ አጽንተዋል።

“አንዳንድ የመንግሥታ ፓርቲዎች ከስምምነቱ ለመውጣት ያላቸው ፍላጎት ቅድስት መንበርን በእጅጉ አሳስቧታል” ሲሉ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ባሌስትሬሮ ተናግረው፥ “በዚህ የተከበረ የሕግ ማዕቀፍ ውስጥ ገና ያልተካተቱ መንግሥታት በአስቸኳይ እንዲከተሉት እና በደብዳቤም ሆነ በመንፈስ ተግባራዊ እንዲያደርጉት” በማለት ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጦር መሣሪያ ማስፈታትን የሚከታተል ቢሮ (ዩኤንኦዳኤ) እንደገለጸው፥ በኦቶዋ ስምምነት ውስጥ ያልተካተቱ ፀረ-ሰው እና ፀረ-ተሽከርካሪ ፈንጂዎች ባለፉት አሥርተ ዓመታት ውስጥ ከፍተኛ ስቃይ ማስከተላቸውን እና ግጭቶች ካበቁ ከረጅም ጊዜ በኋላም ሰላማዊ ዜጎችን መግደል እና መጉዳት መቀጠላቸውን አስታውቆ፥ ኮንቬንሽኑ ከ40 ሚሊዮን በላይ የተከማቹ ፈንጂዎች እንዲወድሙ ማድረጉን እና የተጎጂዎችም ቁጥር በእጅጉ መቀነሱን ገልጿል።

የኦቶዋው ኮንቬንሽን የሰውን ልጅ ማዕከል ያደረገ መሆኑን የገለጹት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ባሌስትሬሮ፥ ይህም ትጥቅ በማስፈታት እና በልማት መካከል ግልጽ ትስስር ይፈጥራል” ብለዋል።

በየዓመቱ በሚከሰቱ በርካታ ፍንዳታዎች እና የጦርነት ቅሪቶች ምክንያት የሚሞቱ ሰዎችን በማስመልከት  የሚወጡ ዝርዝር ሪፖርቶች እጅግ እንዳሳዘናቸው የገለጹት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ባሌስትሬሮ፥ “አሁን ያሉት ትጥቅ የማስፈታት ስምምነቶች፥ ሕጋዊ ግዴታዎችን ብቻ ሳይሆን የዛሬውን እና የመጪውን ትውልድ የሞራል ቁርጠኝነት የሚወክሉ ናቸው” ሲሉ አስገንዝበዋል።

ሊቀ ጳጳስ አቡነ ባሌስትሬሮ በንግግራቸው፥ “በመንግሥታት መካከል ድክመትን ከማስፋፋት ይልቅ ዓለም አቀፍ ሕግጋትን እና የጦር መሣሪያ ማስፈታት ስምምነቶችን ማክበር፥ ለሰው ልጅ ሁሉ ዘላቂ የጥንካሬ እና የኃላፊነት ምንጭ ናቸው” ሲሉ አስገንዝበዋል።

ጄኔቫ በሚገኘው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የቅድስት መንበር ተወካይ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ባሌስትሬሮ፥ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ 2024 ዓ. ም. ለውትድርና አገልግሎት እና ለጦር መሣሪያ ግዥ የወጣው ከ2.7 ትሪሊዮን ዶላር በላይ ከከባድ ሚዛን መዛባት አልፎ ተርፎ ቅሌትም ነው” ሲሉ አስረድተዋል።

ወታደራዊ ወጪው ለማኅበራዊ ዕርዳታ፣ ለምግብ ዋስትና እና የሰውን ልጅ ሁለንተናዊ ልማትን ለማስፋፋት የሚደረገውን ውስን ሃብት እንደሚቃረን ገልጸው፥ “ይህም እውነተኛ የጦር መሣሪያ ትጥቅን ለማስፈታት እስካልረዳ ድረስ ሰላምን ማምጣት የማይቻል መሆኑን ግልጽ እንደሚያደርገው እና እያንዳንዱ ሕዝብ ራሱን እንዲከላከል የሚጠይቀውን መስፈርት እንደገና ወደ ጦር መሣሪያ ትጥቅ ውድድር መቀየር የለበትም” ሲሉ አስረድተዋል።

ሊቀ ጳጳስ ባሌስትሬሮ በንግግራቸው ማጠቃለያ፥ ሁሉም ሀገራት ወደ ምክንያታዊነት እና ወደ ውይይት እንዲመለሱ ጥሪ አቅርበው፥ ሁሉንም የዲፕሎማሲ መመሪያዎችን በመጠቀም ጦርነትን እና አለመረጋጋትን መከላከል እንደሚገባ አሳስበዋል።

ቅድስት መንበር የሰላም እና የሕይወት ባሕልን በማስተዋወቅ፣ የተባበሩት መንግሥታት የፀረ-ፈንጂ ስምምነት ተግባራዊነት ፣ የሰው ሕይወት ቅድስና እና እግዚአብሔር የሰጠን የማይደፈርስ የሰብዓዊ ክብር ተግባራዊነት እንደሚቀጥል ሙሉ እምነት በመያዝ ጥሪዋን በድጋሚ የምታቀርብ መሆኗን፥ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የቅድስት መንበር ቋሚ ታዛቢ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ኤቶሬ ባሌስትሬሮ በመግለጽ ንግግራቸውን አጠቃልለዋል።

 

23 Jun 2025, 15:24