የላቲን አሜሪካ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ፍትሃዊ የሥነ-ምህዳር ሽግግር እንዲደረግ ጥሪ አቀረበች
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
በኮሎምቢያ እና በቅድስት መንበር መካከል ለ190 ዓመታት የዘለቀውን የዲፕሎማሲ ግንኙነት ከማስታወስ በተጨማሪ፥ በሮም የጎርጎሮሳዊ ጳጳሳዊ ዩኒቨርሲቲ እና በቅድስት መንበር የኮሎምቢያ ኤምባሲ በጋራ ባዘጋጁት የውይይት መድረክ፥ የላቲን አሜሪካ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን በብዝሃ ሕይወት እና በአየር ንብረት ለውጥ ላይ ያላትን አመለካከት በማስመልከት ውይይት ተደርጓል።
“ፍትሃዊ ሽግግሮች” በሚል ርዕሥ የተወያየው መድረኩ፥ የላቲን አሜሪካን ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና የአካባቢ ዘላቂ ልማት ራዕይን በመቅረጽ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን የምትጫወታቸውን ሚናዎች አጢኗል።
የውይይት መድረኩ ብዙ የላቲን አሜሪካ አገሮች የሚያጋጥሟቸውን ሁለት ፈተናዎች በማስታወስ፥ በአንድ በኩል አካባቢያዊ እርምጃዎችን የማራመድ አስፈላጊነት በማስመልከት፥ በሌላ በኩል ሦስት ዓለም አቀፍ ቀውሶችን እነርሱም የአየር ንብረት ለውጥ፣ የብዝሃ ሕይወት ጥፋት እና ብክለት ተጽእኖ የሚመጣውን የእኩልነት ማጣት ችግርን በመፍታት አስፈላጊነት ላይ ተወያይቷል።
የተስፋ እና የማስጠንቀቂያ ድምፅ
የላቲን አሜሪካ እና የካሪቢያን ጳጳሳት ምክር ቢርት ፕሬዝዳንት ካርዲናል ጄይም ስፔንገር ለመድረኩ ባደረጉት ንግግር፥ “አሁን የምንገኝበት ጊዜ እኛን የሚደግፈን ዓለም እየፈራረሰ እንደሆነ የሚያመላክት ይመስላል” ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
በሰጡት ምላሹም በላቲን አሜሪካ የምትገኘው ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ወቅታዊውን የአካባቢ እና የማኅበራዊ መራቆት ሁኔታን በማውገዝ የተስፋ ድምጽ እንድትሆን አሳስበዋል። ካርዲናል ስፔንገር አክለውም፥ በገበያ አመክንዮ መሠረት ተፈጥሮን ወደ ፋይናንሺያል እሴት የሚቀይሩ የውሸት የአየር ንብረት መፍትሄዎችን ተችተው፥ መፍትሔው አስቸኳይ መዋቅራዊ ለውጦችን የሚያካትት መሆን እንዳለበት አሳስበዋል።
ካርዲናል ስፔንገር የላቲን አሜሪካን የተፈጥሮ ሃብት ቅርምት እና የመበዝበዝ ፈተናዎችን በመጥቀስ እንደተናገሩት፥ የአገሬው ተወላጆች ግዛቶቻቸውን እንዲጠብቁ፣ ለአነስተኛ ደረጃ የግብርና ሥራ ድጋፍ እንዲደረግ እና ተፈጥሮን ወደ ገንዘብ የሚቀይር ሥርዓትን መቃወም እንደሚገባ አሳስበዋል።
ጉዳዩ ከቃላት በላይ ነው!
በሮም የሚገኝ ጎርጎሮሳዊ ጳጳሳዊ ዩኒቨርሲቲ ርዕሠ መምህር እና የኢየሱሳዊያን ማኅበር ካኅን አባ ማርክ አንድሪው ሉዊስ ለቫቲካን የዜና አገልግሎት እንደተናገሩት፥ የትምህርት ተቋማቸው የመድረኩን ተልዕኮ በተግባራዊ ደረጃ ለማሳደግ እየሠራ እንደሚገኝ እና በሥነ-ምህዳር ዙሪያ ዕውቀቶችን የሚያጎናጽፍ የዲፕሎማ ፕሮግራም መጀመራቸውን አብራርተዋል።
ለአካባቢ ጥበቃ የሚደረግ እንክብካቤ በሳይንቲስቶች እና ምሁራን ብቻ የተገደበ ባለመሆኑ የዩኒቨርሲቲው ፕሮግራም በሁሉም የሕይወት ዘርፎች የሚገኙ ሰዎች እንዲሳተፉ በመርዳት ላይ ያተኮረ እንደሆነ በማስረዳት ተግባራዊ ተፅእኖ እጅግ አስፈላጊ መሆኑንም አባ ማርክ አንድሪው ሉዊስ አሳስበዋል።
“ውዳሴ ላንተ ይሁን” ከሚለው ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሐዋርያዊ ቃለ-ምዕዳን እና በሐዋርያዊ የቤተ ክርስቲያን መሪነት አገልግሎታቸው ዓመታት ወስጥ ከለገሱት አስተምህሮ ጠቃሚ ሃሳቦችን እና እቅዶችን በመውሰድ በተግባር ማዋል አስፈላጊው መሆኑን አባ ማርክ ጠቁመዋል።
“ሥነ-ምኅዳርን መንከባከብ በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ አልተጀመረም” ያሉት አባ ማርክ፥ ቤተ ክርስቲያን ከዚህ በፊት በአካባቢ ላይ አወንታዊ ተጽዕኖ ሊያሳድሩ የሚችሉ ተግባራዊ መንገዶችን ለመጠቀም መሞከሯን አስታውሰዋል።
“ውዳሴ ላንተ ይሁን” የሚለው የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሐዋርያዊ ቃለ-ምዕዳን፥ የድርጊት ጥሪው ተጠናክሮ እንዲቀጥል እና አዲሱ ትውልድ የጋራ መኖሪያ ምድራችንን እንዲንከባከብ እና ተልዕኮውን እንዲያበረታታ ማገዙን አስረድተዋል።
ስለ ወደ ፊት ዕጣ ፈንታ ማሰብ
አባ ማርክ፥ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ 1970ዎቹ የተካሄዱ ሥነ-ምህዳራዊ እንቅስቃሴውችን በማስታወስ፥ የሚያስፈልገው ዘላቂ ልማትን ማምጣት እንደሆነ ተናግረው፥ ማንም ተግባራዊ ሊያደርገው የማይችለውን ነገር ማሰብ ከንቱ እንደሆነ በማስረዳት፥ “በተግባር ሊገለጹ የሚችሉ ዘላቂ ሃሳቦች ያስፈልጉናል” ሲሉ አፅንዖት ሰጥተዋል።