MAP

ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን፥ ቅድስት መንበርን ለሰላም ያላትን ቁርጠኝነት ሲናገሩ ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን፥ ቅድስት መንበርን ለሰላም ያላትን ቁርጠኝነት ሲናገሩ  

ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን፥ በዩክሬን እና በሩስያ መካከል መተማመን አለመኖሩን ገለጹ

የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብፁዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን፥ በሮም ከተካሄደ አንድ ስብሰባ ጎን ለጎን ባደረጉት ንግግር፥ የቅድስት መንበርን የሰላም ቁርጠኝነት በድጋሚ ተናግረው፥ “በሩስያ እና በዩክሬን መካከል ሰላምን ለማውረድ ቅድስት መንበር የሚቻላትን ሁሉ ብታደርግም ነገር ግን ከሚሰጣት ምላሽ ተስፋ አለ ብዬ አላምንም” ብለዋል። ብጹዕንታቸው ከዚህም ጋር በጋዛ ተኩስ እንዲቆም፣ ታጋቾች እንዲለቀቁ እና የዕርዳታ አቅርቦት እንዲደርስ ጥሪ አቅርበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብፁዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን በዩክሬን በመካሄድ ላይ ባለው ጦርነት የተሰማቸውን ሐዘን ገልጸው፥ ጦርነቱን ለማስቆም እስካሁን ምንም ዓይነት መፍትሔ የተገኘ አይመስልም ብለዋል። በሁለቱ ወገኖች ማለትም በሩስያ እና በዩክሬን መካከል ያለው መሠረታዊ ችግር የመተማመን መንፈስ አለመኖር እና በዚህም እርስ በርስ ለመስማማት ዝግጁዎች አለመሆናቸውን ገልጸው፥ “አስፈላጊው ነገር እርስ በርስ ገንቢ በሆነ መንገድ እንዲነጋገሩ የሚያስችላቸውን የመተማመን መንፈስ ማምጣት ነው” ብለዋል።

ብጹዕነታቸው፥ “የእርስ በርስ ግንኙነትን ደረጃ በደረጃ በማሳደግ፥ በድርድሮች አማካይነት መተማመንን በመፍጠር እና በስምምነት ወቅት የገቡትን ቃል ማክበር ይገባል” ብለዋል።

የሰላም ተስፋ

“ቤተ ክርስቲያን በበኩሏ፥ ስለ ሰላም ዘወትር ትጸልያለች” ያሉት ብፁዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን፥ የሰው ልጅ ጥረት ብቻውን በቂ እንዳልሆነ ተናግረው፥ ቅድስት መንበር በበኩሏ ለሰላም ትኩረትን በመስጠት ዕድሎችን ማመቻቸቷን እና ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በሐዋርያዊ የአገልግሎት ሥልጣን መጀመሪያ ላይ ያቀረቡትን የሰላም ጥሪ መቀበል እንድሚያስፈልግ ተናግረዋል።

በጋዛ ሰርጥ እየተካሄደ ያለውን አስከፊ ሁኔታ በማስመልከት የተናገሩት ካርዲናሉ፥ በዶሃ እየተካሄደ ያለውን ድርድር በማስታወስ አንዳንድ መልካም ውጤቶችን ተስፋ አድርገዋል። “ችግሩ ሁሌም አንድ አይነት ነው” ያሉት ብፁዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን፥ የተኩስ አቁም ስምምነት ማድረግ፣ ታጋቾችን በሙሉ ነጻ ማድረግ እና በሕይወት ያሉት ሆነ የሞቱትን ወደ የአገራቸው መመለስ፣ ሰብዓዊ ዕርዳታን እና የሕክምና አገልግሎት በተመለከተ ደህንነቱ የተጠበቀ ተደራሽነትን ማረጋገጥ እንደሆነ በድጋሚ ተናግረዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳት ሊዮ 14ኛ ከብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን ጋር ያደረጉት ስብሰባ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ከቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብፁዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን ጋር ሐሙስ ግንቦት 28/2017 ዓ. ም. ለመጀመሪያ ጊዜ በይፋ እንደሚገናኙ የተነገረ ሲሆን፥ በሁለቱ መካከል ያለው ትብብር የጀመረው፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ የሐዋርያዊ አገልግሎት ሥልጣን መጀመሪያ ቅጽበት እንደሆነ ተገልጿል።

ብፁዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን ይህን በማስመልከት ሲናገሩ፥ ቅዱስነታቸው በሐዋርያዊ ሥልጣናቸው   ቤተ ክርስቲያኒቱን በትክክክ እንደሚያስተዳድሩ ያላቸውን እምነት ገልጸው፥ ቅዱስነታቸው የቤተ ክርስቲያኒቱን ውጤታማ አስተዳደር ለማረጋገጥ በእጃቸው ላይ ያሉ ስልቶችን ከሌሎች የቤተ ክርስቲያኒቱ አባቶች ጋር በጋራ ለመጠቀም እንደሚፈልጉ በቅድሚያ መናገራቸውን አስታውሰዋል።

 

05 Jun 2025, 17:19