MAP

የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቤነዲክቶስ 16ኛን በጎበኟቸው ጊዜ የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቤነዲክቶስ 16ኛን በጎበኟቸው ጊዜ 

“አማኞች ከመሆናችን በፊት ሰው ለመሆን ተጠርተናል።"

የቅድስት መንበር መገናኛዎች ርዕሠ አንቀጽ ዝግጅት ክፍል ሃላፊ አንድሬያ ቶርኔሊ፥ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ቃላት ከቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቤነዲክቶስ 16ኛ ጋር ተመሳሳይነት እንዳላቸው የሚገልጽ አስተያየት በርዕሠ አንቀጽ እንደሚከተለው አስፍሯል፥

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛው ረቡዕ ግንቦት 20/2017 ዓ. ም. ለታዳሚዎች ባቀረቡት ሳምንታዊ የጠቅላላ ትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ላይ፥ “አማኞች ከመሆናችን በፊት ሰው እንድንሆን ተጠርተናል” በማለት ያቀረቡት ቃለ-ምዕዳን ከአስተምህሮአቸው ማዕከላዊ ክፍሎች አንዱ ነበር።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በደጉ ሳምራዊ ምሳሌ ላይ በማሰላሰል ባቀረቡት ስብከት፥ “በሕይወታችን ውስጥ በምናደርገው የእርስ በእርስ ግንኝነት መካከል እኛ ማን እንደሆንን፣ ሌሎች ሰዎችን ስግር ሲያጋጥማቸው መንከባከብ ወይም ያላየን ልንመስል እንችላለን” ብለዋል።

“ኢየሱስ ክርስቶስ በተናገረው ምሳሌ ላይ የተፈጸመው ይህ ነው” ያሉት ቅዱስነታቸው፡- ሁለቱ መንፈሳዊ አገልጋዮች በኢየሩሳሌም ወደሚገኘው ቤተ መቅደሱ የመግባት መብት ቢኖራቸውም፥ በወንበዴዎች እጅ ቆስሎ በመንገድ ዳር ወድቆ የተገኘውን ሰው ለመርዳት አልፈለጉም። ርኅራኄ የተሰማው፥ በአይሁዳውያን ዘንድ እንደ ርኩስ የሚቆጠር ሳምራዊ ሰው ነበር የራራለት። ሃይማኖታዊ ትውፊት እንደ ጠላት የሚቆጥረውን ሰው የተንከባከበው ይህ ሳምራዊ ሰው ነበር።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ረቡዕ ግንቦት 17/2017 ዓ. ም. ባቀረቡት ሳምንታዊ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮአቸው፥ “የአምልኮ ሥርዓት አንድን ሰው ርኅሩኅ አያደርገውም። ርኅራሄ ሃይማኖታዊ ጉዳይ ከመሆኑ በፊት ሰው መሆንን የሚመለከት ጉዳይ ነው!” ብለዋል።

አማኞች መሆን እና እምነትን በተግባር መለማመድ፣ የእግዚአብሔር አገልጋይ መሆን ርኅሩኅነትን አያረጋግጥም። ራሳችንን በምናገኘው የችግር ሁኔታዎች ውስጥ ለጉዳት መዳረጋችንን አያረጋግጥም።

“አማኞች ከመሆናችን በፊት ሰው እንድንሆን ተጠርተናል።” ወንጌልን ለመመስከር ዕድል የሚሆነው ይህ ስብዕና እና ይህ ርህራሄ ነው።

ይህ ሃሳብ በቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቤነዲክቶስ 16ኛ እንደ ጎርጎሮሳውያን በ1959 ዓ. ም. በዚያን ጊዜ አባ. ጆሴፍ ራትዚንገር በወቅቱ በቦን ዩኒቨርሲቲ የሥነ-መለኮት ፕሮፌሰር በነበሩበት ወቅት በትንቢታዊነት ተገልጾ ነበር።

“አዲስ አረማውያን እና ቤተ ክርስቲያን” በሚለው ጥናታዊ ጽሑፋቸው ገጽ 59 ላይ፥ በዓለማዊነት በተራቀቁ ማኅበረሰቦች ሁኔታ ላይ በማሰላሰል፥ ስለ ሚሲዮናውያን ምስክርነት እንዲህ በማለት ጽፈው ነበር፥ “ክርስቲያ ሰው በሌሎች ሰዎች መካከል ወንድም መሆን በማይችልባቸው ጎረቤቶች መካከል ደስተኛ መሆን አለበት። በሌላ አነጋገር እንደ ደጉ ሳምራዊ ጎረቤት ብቻ መሆን ማለት ነው።

የወደፊቱ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቤነዲክቶስ 16ኛ አክለውም፥ “እኔ እንደማስበው፥ ከማያምን ጎረቤቱ ጋር ባለው ግንኙነት ከሁሉም በላይ ሰው ብቻ መሆን ያስፈልጋል።  በማያቋርጥ የመለወጥ ሙከራ እና ስብከት የሚያናድድ ወይም የሚያስቆጣ መሆን የለበትም። ይልቁንም በሚያምር ግልጽነት እና ቀላልነት ሰው ብቻ መሆን አለበት”

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቤነዲክቶስ 16ኛ ቤተ ክርስቲያን እንዴት እንደተወለደች እና እንደገና እንደምትወለድ በግልፅ ተረድተዋል። ማለትም ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ ከተሳቡት ወንዶች እና ሴቶች ምስክርነት፣ በሕይወታቸው፣ በርኅራሄያቸው፣ በሚያገኙት ማንኛውም ሰው ጉዞ ላይ አጋር በመሆን ኢየሱስን መመስከር ይችላሉ።

በሌላ በኩል እምነትን ወደ ትውፊታዊነት በመቀነስ፣ ለቡድን አባልነት ወይም የተወሰኑ የፖለቲካ ዕቅዶችን በሚደግፍ የምዕራቡ ዓለም ርዕዮተ ዓለማዊ ክርስትና ወደ ውድቀት የሚደረገውን ጉዞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቤነዲክቶስ 16ኛ ቀድሞውንም ያውቁ ነበር።

ይህ ነው በመጨረሻ የተልዕኮው ዋና ቁልፍ! ማለትም በእኛ ዘመን ሰዎች በመጀመሪያ ደርጃ ሰው በመሆን ሌሎችን ለማገልገል ራሳቸውን አዘጋጅተው ሩህሩሆች እንዲሆኑ ተጠርተዋል።

ከሌሎች ስዎች እንደሚበልጡ የማይሰማቸው ክርስቲያን ወንዶች እና ሴቶች፥ ብዙውን ጊዜ ባዕዳን የምንላቸው ሰዎች በቅዱስ ወንጌል ውስጥ እንደተጠቀሰው ደጉ ሳምራዊ ርኅራኄን ለመመስከር ተጠርተዋል።” በማለት የቅድስት መንበር መገናኛዎች ርዕሠ አንቀጽ ዝግጅት ክፍል ሃላፊ አንድሬያ ቶርኔሊ ርዕሠ አንቀጹን ደምድሟል።  

 

09 Jun 2025, 18:24