MAP

የርዕሠ ሊቃነ ጳጳስትን ሐዋርያዊ አስተምህሮ የሚያቀርብ አዲስ ይፋዊ ድረ-ገጽ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳስትን ሐዋርያዊ አስተምህሮ የሚያቀርብ አዲስ ይፋዊ ድረ-ገጽ  

ቫቲካን የርዕሠ ሊቃነ ጳጳስት ሐዋርያዊ አስተምህሮን የሚያቀርብ አዲስ ይፋዊ ድረ-ገጽ አስተዋወቀ

ቫቲካን ቫ “Vatican.va” በመባል የሚታወቀው የቅድስት መንበር ይፋዊ ድረ-ገጽ በአዲስ እና ዘመናዊ ንድፉ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳትን አስተምህሮን ለዓለም ይበልጥ ተደራሽ በሆነ መልኩ ለማቅረብ መዘጋጀቱን የቅድስት መንበር መገናኛ ጽሕፈት ቤት አስታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ጽሕፈት ቤቱ ሐሙስ ግንቦት 20/2017 ዓ. ም. እንዳስታወቀው፥ ቫቲካን.ቫ በመባል የሚታወቀው ተቋማዊ ድረ-ገጹ አዲስ የግራፊክ ዲዛይን እንዳለውም ገልጾ፥ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳትን ሐዋርያዊ አስተምህሮን እና የካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ልብ ወደ መላው ዓለም ለማቅረብ እንደሚፈልግ አስረድቷል።

አዲሱ ድረ-ገጽ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛን እና ከእርሳቸው በፊት የነበሩት ርዕሣነ ሊቃነ ጳጳሳት አስተምህሮዎችን የበለጠ ግልጽ እና ተደራሽነት ባለው መንገድ ለማቅረብ የተነደፈ ሲሆን፥ ጎብኝዎችንም በደስታ ለመቀበል መዘጋጀቱ ተገልጿል።

ድረ-ገጹን የማሻሻል ሂደት በተለያዩ ደረጃዎች የተዋቀረ ሲሆን፥ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ከታህሳስ ወር 1995 ዓ. ም. ጀምሮ በድረ-ገጽ በኩል ሲያቀርብ የቆየውን አገልግሎት ወደ አዲስ ደረጃ ለማሸጋገር ያቀደ ሰፊ የአርትዖት እና የዕድገት ጥረት አካል እንደሆነ ተገልጿል።

የቀድሞው እና የአዲሱ ድረ-ገጽ ንድፎች
የቀድሞው እና የአዲሱ ድረ-ገጽ ንድፎች

ገፆቹን ተደራሽ ለማድረግ ክህሎት ያላቸው ቡድኖች ሥራቸውን የቀጠሉ ሲሆን፥ እነዚህም የሁሉንም ይዘቶች ተደራሽነት የሚያረጋግጥ የሠነድ ቡድን እና በቅድስት መንበር መገናኛ ጽሕፈት ቤት ሥር ሆኖ መዋቅሩን ያዘጋጀው የመረጃ ቡድን መሆናቸው ታውቋል።

ለአዲሱ ድረ-ገጽ ሕይወት የሰጠው፥ በቅድስት መንበር መገናኛ ጽሕፈት ቤት የሚመራ እና “በዲጂታሉ ዓለም ውስጥ እምነትን መመስከር” የተባለ የትምህርት መርሃ ግብር የመጀመሪያ ተማሪ የሆነው ግራፊክ ዲዛይነር ፔሯዊው ሁዋን ካርሎስ ይቶ እንደሆነ ታውቋል።

ድረ-ገጹ ለስማርት ስልኮችም ጭምር የተቻቸ ነው
ድረ-ገጹ ለስማርት ስልኮችም ጭምር የተቻቸ ነው

ሁዋን ካርሎስ ይቶ በቅድስት መንበር መገናኛ ጽሕፈት ቤት ድረ-ገጹ በኩል በሰጠው መግለጫ፥ ከአዲሱ ድረ-ገጽ ንድፍ እና እይታ በስተጀርባ ያለውን ግብ ሲያብራራ፡- “በዲጂታሉ ዓለም ውስጥ ቤተ ክርስቲያኒቱን መወከል እንዳለበት፣ የቅድስት መንበር ይፋዊ ድረ-ገጽን ለማደስ መታሰቡ ሲሰማ ወደ አእምሮው የመጣው የመጀመሪያው ነገር እንደ ነበር አስረድቷል።

ጃን ሎሬንዞ በርኒኒ የቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለመንደፍ የተከተለውን ክብ ቅርፅ በመውሰድ፥ እጆቿ የተከፈቱ፣ ለዓለም ይበልጥ ተደራሽ፣ ግልጽ፣ ቅርብ የሆነች የዘመናችን ቤተ ክርስቲያን የሚገልጽ ንድፍ ለማዘጋጀት ማሰቡን አስረድቷል።

የድረ-ገጹ ቀለሞች ከሰማይ፣ ከምድር እና ከድንጋይ ቀለማት ጋር ሆኖ ፈካ ያለ ግራጫ እና ነጭ ቀለማት ካሉት ከሮም ሰማይ ሰማያዊ ቀለሞች የመጡ መሆናቸውን አስረድቶ፥ “በድረ-ገጹ መጀመሪያ ላይ የሚታዩ ትላልቅ እና ታዋቂ ፎቶግራፎች፥ በጉዞ ላይ የምትገኝ ሕያው ቤተ ክርስቲያንን ለማሳየት ነው” ሲል አክሏል።

ሁዋን ያዘጋጃቸው የድረ-ገጹ ቀለሞች ከሰማይ፣ ከምድር እና ከድንጋይ ቀለማት ጋር የሚመሳሰሉ ናቸው
ሁዋን ያዘጋጃቸው የድረ-ገጹ ቀለሞች ከሰማይ፣ ከምድር እና ከድንጋይ ቀለማት ጋር የሚመሳሰሉ ናቸው

 

29 May 2025, 16:37