ቫቲካን ‘ቬሳክ’ ተብሎ ለሚታወቀው የቡድሃ እምነት ተከታዮች ክብረ በዓል መልካም ምኞቷን ገለጸች
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
የቡድሃ ሃይማኖት መስራች የሆነው ቡድሃ ወይም የውልደት ስሙ ሲዳርታ ጓታማ የተወለደበት፣ የተገለጠበት እና ያረፈበት ቀን ተብሎ በእምነቱ ተከታዮች ዘንድ በየዓመቱ በሚያዝያ ወይም ግንቦት ወር ላይ የሚከበረው ‘ቬሳክ’ ወይም የቡድሃ ቀን ግንቦት 4 ቀን 2017 ዓ.ም. ተከብሮ የዋለ ሲሆን፥ በዓሉን በማስመልከት የቅድስት መንበር የሃይማኖት ተቋማት ውይይት ጽህፈት ቤት በዓለም ዙሪያ ላሉ የቡድሃ እምነት ተከታዮች በሙሉ “ቡድሂስቶችና ክርስቲያኖች ለዘመናችን ነፃ የሚያወጣ ውይይት ያደርጋሉ” በሚል ርዕስ መልዕክት መላኩ ተገልጿል።
የቅድስት መንበር የሃይማኖት ተቋማት ውይይት ጽህፈት ቤት ዋና ሃላፊ በሆኑት ብፁዕ ካርዲናል ጆርጅ ጃኮብ ኮቫካድ እና በጽህፈት ቤቱ ፀሐፊ ሞንሲኞር ኢንዱኒል ጃና-ካራትኔ (ኮዲቱዋኩ ካንካናማላጌ) የተፈረመበት መልዕክቱ በካቶሊክ እና ቡድሂዝም መካከል ያለውን የጋራ አቋም ያሳያል ተብሏል።
የጋራ ደስታ
የቬሳክ ቀንን ለሚያከብሩ ሁሉ ከልብ የመነጨ ሰላምታ እና ምኞቶችን በመግለጽ የጀመረው መልዕክቱ፥ “በዚህ ዓመት የምናቀርብላችሁ ሰላምታ በኢዮቤልዩ መንፈስ በመሆኑ ከሌላው ጊዜ የተሻለ እና ያማረ ነው” በማለት በአጽንዖት ገልጿል።
ጽህፈት ቤቱ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ክርስቲያን ካልሆኑ ሀይማኖቶች ጋር ስለምታደርገው ግንኙነት አስመልክቶ በሁለተኛው የቫቲካን ጉባኤ ‘ኖስትራ አታቴ’ ተብሎ የወጣው የሃይማኖት ነፃነት ሰነድን በመጥቀስ “የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን በሌሎች ሃይማኖቶች ውስጥ ያለውን እውነተኛ እና ቅዱስ ነገር አትቃወምም” በማለት በመልዕክቱ በድጋሚ ያረጋገጠ ሲሆን፥ ዘንድሮ 60ኛ ዓመቱን የሚያከብረው ይህ ሁለተኛው የቫቲካን ጉባኤ ሰነድ ለውይይት ቀጣይነት ያለው ቁርጠኝነትን ያበረታታል ብሏል።
ሀይማኖቶች ለሰው ልጅ እንቆቅልሾች ምላሽ ይሰጣሉ
የቅድስት መንበር የሃይማኖት ተቋማት ውይይት ጽህፈት ቤት መልዕክቱ እንደሚያመለክተው የቡድሂዝም ሃይማኖት የሚከተለው የነጻነት መንገድ የጋራ እውነትን እና የህይወት ሙላትን ፍለጋ ላይ ጥልቅ ስሜት ይፈጥራል ያለ ሲሆን፥ “በዚህም አሁን ባለንበት በመከፋፈል፣ በግጭት እና በስቃይ በተሞላው ዓለም ውስጥ ነፃ የሚያወጣ ውይይት እንደሚያስፈልግ ተገንዝበናል” በማለት ከገለጸ በኋላ፥ ነገር ግን ውይይቱ በቃላት ደረጃ ብቻ እንዳይቀር አሳስቧል።
የቫቲካን ጽህፈት ቤት ከዚህም ይልቅ ካቶሊኮች እና የቡድሃ እምነት ተከታዮች ከቃላት በዘለለ መልኩ ለሰላም፣ ለፍትህ እና ለሰብዓዊ ክብር ተጨባጭ እርምጃዎችን እንዲወስዱ አበረታቷል።
በዛሬው ጊዜ በዓለም ላይ እየተንሰራፋ ካለው ኢፍትሃዊነት፣ ግጭትና የደህንነት እጦት አንጻር መልዕክቱ እንዳመላከተው “ሃይማኖቶች ‘በዚህ ጊዜ ለተፈጠሩት የሰው ልጅ እንቆቅልሾች’ ትርጉም ያለው ምላሽ የመስጠት ከፍተኛ አቅም እንዳለን እርግጠኞች ነን” በማለት በሁለቱ ሃይማኖቶች መካከል የሚደረገው ውይይት የጋራ ጥበብን በማካፈል አሁን ያሉትን ዓለም አቀፋዊ ተግዳሮቶች ለመፍታት የሚያስችላቸው መንገድ ላይ አጽንዖት ሰጥቷል።
መልእክቱ በማከልም የሁለተኛው ቫቲካን ጉባኤ ሰነድ የሆነው ‘ኖስትራ አታቴ’ ውስጥ ያለው ሃሳብ ዛሬም ድረስ እጅግ ጠቃሚ መሆኑን በመግለጽ፥ ሰነዱ “በሁሉም ህዝቦች እና ሃገራት መካከል አንድነት እና ፍቅርን” ማጎልበት እንዲሁም “ልዩነታችንን ማድነቅ” የሚለውን ሀሳብ ያበረታታል ብሏል።
የቅድስት መንበር የሃይማኖት ተቋማት የጋራ ውይይት ጽህፈት ቤት ለቡድሃ እምነት ተከታዮች የላከው መልዕክት በመጨረሻም “በሚደረጉ የጋራ ውይይቶች በኩል የየራሳችን ወጎች እና ባህሎች በጊዜያችን ላሉ ተግዳሮቶች ተገቢውን ምላሽ ሊሰጡን እንደሚችሉ” ያለውን ተስፋ በመግለጽ አጠቃሏል።