MAP

የካርዲናሎች ዝግ ጉባኤ በቫቲካን ውስጥ በመካሄድ ላይ እንደሚገኝ ተገለጸ

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ረቡዕ ሚያዝያ 29/2017 ዓ. ም. ከሰዓት በኋላ በተጀመረው ጉባኤ ላይ የሚሳተፉ 133 መራጭ ካርዲናሎች ምርጫው ወደሚካሄድበት የሲስቲን ጸሎት ቤት ዑደት አድርገዋል።

ዘንድሮ በሚካሄደው ታሪካዊ ዝግ ጉባኤ ላይ የሚሳተፉት 133 መራጭ ካርዲናሎች ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳትን ለመምረጥ ወደ ጸሎት ቤቱ ያመሩት በጥንታዊ ሥነ-ሥርዓት እንደ ነበር ተመልክቷል።

የካርዲናሎች ኅብረት መሪ የሆኑት ብፁዕ ካርዲናል ጆቫኒ ባቲስታ ሬ ረቡዕ ከረፋዱ አራት ሰዓት ላይ በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ውስጥ የቀረበውን እና ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ምርጫ ቀደም ብሎ የሚቀርበውን “Missa pro eligendo Romano Pontifice” መስዋዕተ ቅዳሴን መርተዋል።

የዑደቱ ሥነ-ሥርዓት

ረቡዕ በዘጠኝ ሰዓት ከአርባ አምስት ደቂቃ ላይ መራጭ ካርዲናሎች በሐዋርያዊ ሕንጻ ውስጥ በሚገኝ በቅዱስ ጳውሎስ ጸሎት ቤት ውስጥ ከተሰበሰቡ በኋላ በተገላቢጦሽ ቅደም ተከተል ወደ ሲስቲን ጸሎት ቤት ዑደት ያደረጉ ሲሆን በዚህም ወቅት ወደ ቅዱሳን የሚቀርብ የ “ሊጣኒያ” ጸሎት በማዜም የመንፈስ ቅዱስን ዕርዳታ ተማጽነዋል። በቅዱስ መስቀል በተመራው በዚህ የብጹዓን ካርዲናሎች ዑደት ላይ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ምርጫን ለማስተባበር ሃላፊነት የተሰጣቸው አባላት ተካፋይ ሆነዋል።

የቃለ መሐላው ሥነ-ሥርዓት

ብጹዓን ካርዲናሎች ወደ ሲስቲን ጸሎት ቤት ከገቡ በኋላ እያንዳንዳቸው እጃቸውን በቅዱስ ወንጌል ላይ በማስቀመጥ ከጉባኤው በፊትም ሆነ በኋላ ምስጢራዊነቱን እንዲጠብቁ የሚጠይቀይቀውን ቃለ መሐላ፥ “እንግዲህ እግዚአብሔር ሆይ እርዳኝ! እነዚህ በእጄ የምዳስሳቸው ቅዱሳት ወንጌላት ናቸው!” በማለት ቃለ መሐላቸውን ፈጽመዋል።

የሲስቲን ጸሎት ቤት ከመዘጋቱ በፊት በዝግ ጉባኤው የማያስፈልጉ “Extra omnes” አባላት በሙሉ ሥፍራውን ለቅቀው ወጥተዋል። ብፁዕ ካርዲናል ራኒዬሮ ካንታላሜሳ የዕለቱን አስተንትኖ ከማቅረባቸው በፊት ብጹዓን ካርዲናሎች የተመደበላቸውን ቦታ እንዲይዙ ጋብዘዋል።

በዝግ ጉባኤው መካከል የማያስፈልጉ “Extra omnes” አባላት ጸሎት ቤቱን እንዲለቁ ሲታዘዙ

ድምጽ የመስጠት ሥነ-ሥርዓት

የሲስቲን ጸሎት ቤት ከተቆለፈ በኋላ “cum clave” ብጹዓን ካርዲናሎቹ የቅዱስ ጴጥሮስ ተተኪ የሆኑትን 267 ኛ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት መምረጥ ጀምረዋል። አዲስ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳትን ለመምረጥ ሁለት ሦስተኛ ድምጽ የሚያስፈልግ ሲሆን፥ ለዚህም ቢያንስ 89 ድምጽ እንደሚያስፈልግ ተገልጿል። በእያንዳንዱ ቀን እስከ አራት ዙር ድምጽ የሚሰጥ ሲሆን፥ ከድምጽ መስጫው ሥነ-ሥርዓት በኋላ በጸሎት ቤቱ ጣሪያ በኩል የሚወጣው ጥቁር ጭስ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት አለመመረጣቸውን ሲገልጽ፥ በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ደወሎች የሚታጀብ ነጭ ጭስ አዲሱ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት መመረጣቸውን በማያሻማ ምልክት የሚያበስር እንደሆነ ታውቋል።

ከ70 ሀገራት የተውጣጡ መራጭ ካርዲናሎችን ያሳተፈው ይህ ዝግ ጉባኤ በታሪክ እጅግ ልዩ ከሚባሉት መካከል አንዱ እና ነፍስሔር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የቤተ ክርስቲያኒቱን ውክልና ለማስፋት ያደረጉትን ጥረት የሚያሳይ እንደሆነ ታውቋል።

የምርጫው ጠቅላላ ምስጢራዊነት

በሲስቲን ጸሎት ቤት ውስጥ ብጹዓን ካርዲናሎች በሚያስተነትኑበት ወቅት የምርጫውን ጠቅላላ ምስጢራዊነት ለመጠበቅ የገቡት ቃለ መሐላ ተግባራዊ ሆኖ ይቆያል። በጉባኤው መካከል በተለያዩ አገልግሎቶች የተሰማሩ ገዳማውያን እና ምእመናን መኖራቸው ታውቋል። ከእነዚህም መካከል የሕክምና ባለሞያዎች እና የሥርዓተ አምልኮ ሥነ-ሥርዓት አስተባባሪዎች የሚገኙበት ሲሆን፥ እነርሱም ቢሆኑ የጉባኤውን ምስጢራዊነት ለመጠበቅ ቃለ መሐላ መግባታቸው ታውቋል።

በካርዲናሎች ዝግ ጉባኤ ወቅት የቫቲካን ግዛት ጥብቅ የደህንነት ፕሮቶኮሎችን የተጠቀመ ሲሆን፥ ከእነዚህም መካከል የመገናኛ መስመሮች መጨናነቅ እና ሂደቱ በውጪው ዓለም እንዳይደናቀፍ የኤሌክትሮኒክስ መሣሪያዎች ሙሉ በሙሉ መታገዳቸው ታውቋል።

በዓለም ውስጥ ዝነኛ በሆነው በሲስቲን ጸሎት ቤት ውስጥ ምን እየተካሄደ እንደሆነ ማንም ባያውቅም ነገር ግን መላው ዓለም ባሁኑ ጊዜ እጅግ አስፈላጊ የሆነውን በጸሎት ቤቱ የተገጠመውን ጭስ መውጫ እየተመለከተ እንደሚገኝ ታውቋል።

ወደ መራጭ ካርዲናሎች ዝግ ጉባኤ መግቢያ በር

 

 

08 May 2025, 16:23