MAP

የሲስቲን ጸሎት ቤት የአዲሱን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ምርጫን ለማስተናገድ መዘጋጀቱ ተገለጸ

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የቅድስት መንበር መግለጫ ክፍል የሲስቲን ጸሎት ቤት ሚያዝያ 29/2017 ዓ. ም. የሚጀምረውን የብጹዓን ካርዲናሎች ጉባኤ ለማስተናገድ ዝግጅት ላይ እንደሚገኝ ዛሬ ቅዳሜ ይፋ ባደረግው የቪዲዮ ምስሉ ገልጿል። 

ዓርብ ዕለት የቫቲካን የእሳት አደጋ መከላከያ ክፍል ሠራተኞች በሲስቲን ጸሎት ቤት ጣሪያ ላይ ቢያንስ በ89 ድምጽ አዲስ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት መመረጣቸውን በነጭ ጭስ፥ ካልሆነም በጥቁር ጭስ የሚያሳውቀውን የጭስ መውጫ ቱቦን ሲያድሱ ታይተዋል።

በጭስ መውጫው በኩል የሚወጣው ነጭ ጭስ፥ 133 መራጭ ካርዲናሎች ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያንን የሚመሩትን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳትን መምረጣቸውን እንደሚያሳይ ይጠበቃል።

መራጭ ካርዲናሎች አዲስ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳትን ለመምረጥ ከሚያዝያ 29/2017 ዓ. ም. ጀምሮ በሚያደርጉት የጉባኤ ቀናት የመንፈስ ቅዱስን ድጋፍ ለመለመን በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት እንደሚያቀርቡ ታውቋል።

የቫቲካን የእሳት አደጋ መከላከያ ክፍል ሠራተኞች የጭስ መውጫ ቱቦን ሲያድሱ
የቫቲካን የእሳት አደጋ መከላከያ ክፍል ሠራተኞች የጭስ መውጫ ቱቦን ሲያድሱ   (Vatican Media)

በዚያው ዕለት ከሰዓት በኋላ በአሥር ሰዓት ተኩል ላይ 133ቱ መራጭ ካርዲናሎች በአቅራቢያው ወደሚገኘው የሲስቲን ጸሎት ቤት ዑደት ከማድረጋቸው በፊት በቅዱስ ጳውሎስ ጸሎት ቤት ተሰብስበው ወደ ቅዱሳን ዘንድ የሚደረገውን ጸሎት ያደርሳሉ።

ዑደቱን ተከትሎ ብፁዓን ካርዲናሎቹ የመላው ዓለም ቤተ ክርስቲያን ሐዋርያዊ መሪ ሆነው የሚመረጡትን የሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ተተኪን በታማኝነት ለመምረጥ ቃለ መሃላን ይፈጽማሉ።

ቃለ መሃላቸዉ በተጨማሪም በአዲሱ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ምርጫ ወቅትከሁሉም ዝርዝር ነጥቦች ጋር የመራጭ ካርዲናሎች ፍጹም ሚስጥራዊነት የሚያስጠብቅ ሲሆን በተጨማሪም ምርጫውን ለማደናቀፍ ከውጭ የሚመጡ ሙከራዎችን ውድቅ ለማድረግ ቃል ይገባሉ።

የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት የሥርዓተ አምልኮ አስተባባሪ አባት ጉባኤውን መሳተፍ የማይችሉት በሙሉ የሲስቲን ጸሎት ቤት ለቅቀው እንዲወጡ ትዕዛዝ ያስተላልፋሉ።

በመቀጠልም የከፍተኛ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት አባላት ስብከት አቅራቢ በነበሩት በብፁዕ ካርዲናል ራኒዬሮ ካንታላሜሳ የተዘጋጀ ሁለተኛ ዙር የአስተንትኖ ጊዜ እንደሚሰጥ ታውቋል።

በመቀጠል የ90 ዓመቱ ካርዲናል እና የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት የሥርዓተ አምልኮ አስተባባሪ አባት የሲስቲን ጸሎት ቤት ለቀው ከወጡ በኋላ የድምፅ መስጠት ሥነ- ሥርዓት ይጀመራል።

የመጀመሪያው ድምጽ ዕሮብ ሚያዝያ 29/2017 ዓ. ም. ምሽት ላይ ይፋ የሚሆን ሲሆን በቀጣዮቹ ቀናት ውስጥ መራጭ ካርዲናሎች በቀን አራት ጊዜ ማለትም ጠዋት ሁለት ጊዜ እና ከሰዓት በኋላ ሁለት ጊዜ ድምጽ እንደሚሰጡ ታውቋል።

ሁሉም የምርጫ ድምጾች ከተቃጠሉ በኋላ አዲሱ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት መመረጣቸውን የሚያበስር ነጭ ጭስ በጭስ መውጫው በኩል ወጥቶ እንዲታይ ይደረጋል።

 

03 May 2025, 16:59