MAP

ለአካለ መጠን ያልደረሱ ህፃናት ጥበቃ ጳጳሳዊ ኮሚሽን አባላት ኅዳር ወር 2016 ዓ.ም. ሪፖርት ሲያቀርቡ የተነሰሱት ፎቶ - ከማህደር ለአካለ መጠን ያልደረሱ ህፃናት ጥበቃ ጳጳሳዊ ኮሚሽን አባላት ኅዳር ወር 2016 ዓ.ም. ሪፖርት ሲያቀርቡ የተነሰሱት ፎቶ - ከማህደር  

ለአካለ መጠን ያልደረሱ ህፃናት ጥበቃ ጳጳሳዊ ኮሚሽን ለብጹአን ካርዲናሎች ዝግ ጉባኤ (ኮንክሌቭ) የሚደረገውን ጸሎት ተቀላቀለ

ለአካለ መጠን ላልደረሱ ህፃናት ጥበቃ የሚያደርገው ጳጳሳዊ ኮሚሽን አዲሱን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ለመምረጥ ሚያዝያ 29 ቀን 2017 ዓ.ም. ረቡዕ ዕለት የሚጀመረው የብጹዓን ካርዲናሎች ዝግ ጉባኤ ከመካሄዱ በፊት ቤተክርስቲያኒቷ ስታደርገው የነበረውን ጸሎት ተቀላቅሏል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

የቅዱስ ካርዲናሎች ህብረት አባላት ቀጣዩን የሮም ሊቀ ጳጳስ ለመምረጥ ከአንድ ቀን በኋላ ለሚደረገው የመራጭ ብጹአን ካርዲናሎች ጉባኤ ወይም የኮንክሌቭ ዝግጅት በሮም በተሰባሰቡበት በአሁኑ ወቅት፥ ለአካለ መጠን ያልደረሱ ሕፃናት ጥበቃ ጳጳሳዊ ኮሚሽን በጋዜጣዊ መግለጫ እና በጸሎት ለመራጭ ካርዲናሎች ያለውን መንፈሳዊ ቅርበት እና ድጋፍ ገልጿል።

በመላው ቤተ ክርስቲያን የህፃናት ጥበቃ ባህልን የማስተዋወቅ እና የማበረታታት አደራ የተሰጠው ኮሚሽኑ በመግለጫው የወቅቱን አሳሳቢነት በመጥቀስ፥ በመንፈስ ቅዱስ ለሚመራው የአዲስ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ምርጫ ሥነ ስርዓት ስኬታማነት በዓለም አቀፉ ቤተክርስቲያን የሚደረገውን ጸሎት እንደተቀላቀለ አስታውቋል።

ተቋሙ በመግለጫው “ድምጻችንን ከእግዚአብሔር ሕዝብ ጋር አንድ በማድረግ በመንፈስ ቅዱስ በመመራት የሚካሄደው የምርጫ ሥነ ስርዓት ስኬታማ እንዲሆን ጸሎታችንን የምናቀርብ ሲሆን፥ በቤተክርስቲያኑ ውስጥ በደል የደረሰባቸው ሰዎች ጩኸት ሰሚ እንዲያገኝም ጭምር እንጸልያለን” ብለዋል።

ለህፃናት ጥበቃ ያለው ድፍረት፣ ትህትና እና ቁርጠኝነት
ኮሚሽኑ በብጹአን ካርዲናሎች ህብረት ላይ ያለውን ጥልቅ ኃላፊነት በመገንዘብ፥ በቤተ ክርስቲያኒቱ ሕይወት ውስጥ ያሉ አቅመ ደካሞችን የመጠበቅን አስፈላጊነት በማስታወስ፥ “ለአናሳዎች ጥበቃ ባላቸው ድፍረት፣ ትህትና እና ቁርጠኝነት እንዲመሩ እና ቀጣዩን የጴጥሮስን ምትክ የመምረጥ ከባድ ሀላፊነት ለሚሸከሙ ብጹአን ካርዲናሎች እንጸልያለን” በማለት አብሮነታቸውን ገልጿል።

የኮንክሌቭ ጉባኤው ከመጀመሩ ከቀናት በፊት በሮም ከተማ በብጹአን ካርዲናሎች መካከል በተደረጉት ውይይቶች ለአቅመ ደካሞች ጥበቃ ማድረግ ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ መሆኑን ኮሚሽኑ በማበረታታት የገለጸ ሲሆን፥ የቤተክርስቲያኑ ተዓማኒነት እና የሞራል ግዴታ ‘በእውነተኛ ተጠያቂነት፣ ግልጽነት እና በፍትህ ተግባር ላይ የተመሰረተ’ መሆኑን አረጋግጧል።

የምርጫ ሂደቱን ለቅዱስ ዮሴፍ አደራ መስጠት
ኮሚሽኑ የምርጫ ሂደቱን የህፃኑ ኢየሱስ ክርስቶስ ጠባቂ በሆነው በቅዱስ ዮሴፍ በኩል ልዩ ጸሎትን በአደራ እና በአማላጅነት መንፈስ ያቀረበ ሲሆን፥ ከዚህም ባሻገር በመራጮች ላይ መለኮታዊ ሃይል እንዲመጣ ጸሎት ማድረጉን ገልጿል።

ጸሎቱ “መንፈስ ቅዱስህ በስምህ በተሰበሰቡት ብጹአን ካርዲናሎች ላይ ይውረድ” የሚል ሲሆን፥ “የቅዱስ ጴጥሮስን ተተኪ በመንፈስ ቅዱስ ሃይል በሚመርጡበት ወቅት ለእግዚአብሔር ሕዝብ ጥበቃ እና እንክብካቤ ቅድሚያ እንዲሰጡ እንጸልያለን” በማለት ከቀጠለ በኋላ፥ ከዚህም በተጨማሪ ጸሎቱ በቤተክርስቲያኒቱ ውስጥ በግፍ ለተጎዱት ቤተክርስቲያን ያላትን ሃላፊነት ጠለቅ ያለ ግንዛቤ እንዲኖር የሚጠይቅ ሲሆን፥ የእውነት እና የፍትህ አስፈላጊነት ቅሌትን በመፍራት እንዳይደበዝዝ ወይም ለዝና በመጨነቅ እንዳይዘገይ ያሳስባል።

በፍትህ እና በእውነት ላይ የተመሰረተ የአመራር ራዕይ
የኮሚሽኑ ጸሎት ቀጣዩ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ግልጽነት እና ጥበቃ ለማድረግ የሚተጉ እረኛ እንደሚሆኑ እና ብጹአን ካርዲናሎቹ ራሳቸው የተጣለባቸውን የተቀደሰ አደራ ለመጠበቅ ንቁ እንደሚሆኑ ያለውን ተስፋ በመግለጽ፥ ጸሎቱ በመቀጠል “ብጹአን ካርዲናሎቻችን ለአቅመ ደካሞች ከለላ እና ጥበቃ የሚያደርጉ መሪዎች፣ ለንጹሀን ተሟጋቾች እና ለተጎጂዎች ተሟጋቾች እንዲሆኑ ሃይልህን ስጣቸው” ይላል። በመጨረሻም፥ “ለጠንካራ ፖሊሲዎች እና ሂደቶች እንዲሁም የዲሲፕሊን እርምጃዎች ቅድሚያ የመስጠት ጸጋውን እንዲያገኙ እንጸልያለን” በማለት ያጠቃልላል።
 

06 May 2025, 16:43