MAP

ብፁዕ ካርዲናል ፒየትሮ ፓሮሊን ሽልማቱን በተቀበሉ ጊዜ ብፁዕ ካርዲናል ፒየትሮ ፓሮሊን ሽልማቱን በተቀበሉ ጊዜ  (Terza Loggia )

ካርዲናል ፓሮሊን በቅድስት መንበር ስም ለፍትሃዊ ዓለም በማገልገላቸው የተሰጣቸውን ሽልማት ተቀበሉ

የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብፁዕ ካርዲናል ፓሮሊን በዓለማችን ላይ ፍትሕን ለማስፈን የሚደረገውን የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ጥረት እውን ለማድረግ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ ላበረከቱት አገልግሎት ተሸልመዋል። ሽልማቱን የሰጣቸው “Path to Peace” ወይም “ወደ ሰላም ጎዳና” የተሰኘ ፋውንዴሽን ሲሆን፥ በሥነ-ሥርዓቱ ላይ ብጹዕነታቸው ባደረጉት ንግግር፥ ሽልማቱን የተቀበሉት በጽሕፈት ቤታቸው ስም እንደሆነ ገልጸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ሽልማቱን ለቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብፁዕ ካርዲናል ፒየትሮ ፓሮሊን ያበረከቱት፥ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ1991 ዓ. ም. በተባበሩት መንግሥታት የቅድስት መንበር ቋሚ ታዛቢ ሆነው ባገለገሉበት ወቅት “ወደ ሰላም ጎዳና” የተሰኘ ፋውንዴሽን የመሠረቱት ሊቀ ጳጳስ ሬናቶ ራፋኤሌ ማርቲኖ እንደሆኑ ታውቋል።

ብፁዕ ካርዲናል ፓሮሊን በኒውዮርክ በተካሄደው ሥነ-ሥርዓት ላይ ለተሰጣቸው ሽልማት ምስጋናቸውን አቅርበው፥ የዘንድሮውን ‘ወደ ሰላም ጎዳና’ ሽልማት በማግኘታቸው የተሰማቸውን ታላቅ ክብር ገልጸዋል። ሽልማቱን የተቀበሉት በቅድስት መንበር ስም እና ከሁሉም በላይ በዓለማችን የሰላም እና የፍትህ ጥያቄን ለማራመድ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳትን በመወክል ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይል በሚሠራው በሐዋርያዊ ጽሕፈት ቤታቸው ስም መሆኑንም ገልጸዋል።

ብፁዕ ካርዲናል ፓሮሊን የተሰጣቸው ክብር ከግል በላይ ለፈውስ እና ለእርቅ ድምጹን የሚያሰማ ቅዱስ ተልዕኳቸውን የሚያጠናክር የትብብር መንፈስን ያካተተ እንደሆነ አብራርተው፥ የቅድስት መንበር ተልዕኮ ዋና መሠረቱ ግጭት የሌለበት ዓለምን ለመገንባት ተከታታይ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት የዘረጉት መንገድ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል።

የተያዘው የጎርጎሮሳውያኑ 2025 ዓ. ም.፥ የቀድሞዎቹ ርዕሣነ ሊቃነ ጳጳሳት፥ ቅዱስ ጳውሎስ ስድስተኛ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ታሪካዊ ጉብኝት ያደረጉበት 60ኛ ዓመት መታሰቢያ፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ በተባበሩት መንግሥታት ጉብኝት ያደረጉበት 30ኛ ዓመት መታሰቢያ እና ነፍስሔር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባኤ ንግግር ያደረጉበት 10ኛ ዓመት መታሰቢያ እንደሆነ ታውቋል። ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን በእነዚህ ታሪካዊ ዓመታት ላይ በማሰላሰል እንድተናገሩት፥ “እያንዳንዱ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት በሐዋርያዊ የአገልግሎት ዘመናቸው፣ ወደ ፍትሃዊ እና ሰላማዊ ዓለም ለሚወስደው መንገድ ብርሃንን እና ድንበር ተሻጋሪ ጥበብን እንደሰጡ አስረድተዋል።

የቀደሙት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ንግግሮች

የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ጳውሎስ ስድስተኛ እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ በ1965 ዓ. ም. በመንፈሳዊ እና ሥነ-ምግባራዊ መታደስ ላይ የተመሠረተ ዘላቂ ሰላም ሊኖር ይገባል ሲሉ ግልጽ እና ትንቢታዊ በሆነ መንገድ ካስተላለፉት መልዕክት ጀምሮ የተለያዩ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት የተናገሩትን ካርዲናል ፓሮሊን አስታውሰዋል። ብጹዕነታቸው በማያያዝም እነዚህ ቃላት ዛሬ “የቴክኖሎጂ ዕድገት ከሥነ-ምግባራዊ ዕድገት ውጭ የሰው ልጅ ሚዛናዊ ባልሆነ መንገድ እንዲጓዝ ያደርጋል” በማለት ጠቃሚ ሆነው እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል።

ከዚያም ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ1979 ዓ. ም. የሰው ልጅ ታላቅ በጎም ሆነ ክፋ ተግባራትን ለመፈጸም ያለውን አቅም ማወዳደር እንደሚገባ አጥብቀው ማሳሰባቸውን እንዲሁም ለእያንዳንዱ የሰው ልጅ ውስጣዊ እና የማይደፈር ክብር አጽንኦት የሰጡበትን ንግግር በመጥቀስ፥ እልቂትን እና ሁለተኛው የዓለም ጦርነትን እንደ ታሪካዊ ክስተቶች ብቻ ሳይሆን አሁንም ምላሽ የሚሹ የሞራል ፈተናዎች መሆናቸውን ከግል ልምድ በመነሳት መናገራቸውን አስታውሰዋል።

ለብፁዕ ካርዲናል ፒየትሮ ፓሮሊን የተሰጣቸው “Path to Peace” ወይም “ወደ ሰላም ጎዳና”  ሽልማት
ለብፁዕ ካርዲናል ፒየትሮ ፓሮሊን የተሰጣቸው “Path to Peace” ወይም “ወደ ሰላም ጎዳና” ሽልማት

የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት በነዲክቶስ 16ኛ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ2008 ዓ. ም. ሰብዓዊ መብቶችን የሚደግፉ ሁለንተናዊ እና የማይለወጡ እውነቶች እንዲረጋገጡ እና ሰብዓዊ ክብርን መከላክል የመላው ዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ የጋራ ሃላፊነት ተደርጎ ሊወሰድ እንደሚገባ መናገራቸውንም ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን አስታውሰዋል።

ነፍስሔር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ 2015 ዓ. ም. የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን በጎበኙበት ወቅት ባደረጉት ንግግር፥ ተጠቅሞ በመጣል ባህል ላይ ካቀረቡት ሃይለኛ ትችቶች ጋር በአካባቢ ጥበቃ እና ማኅበራዊ ፍትህ መካከል ትስስር መኖሩን አፅንዖት ሰጥተው መናገራቸውን ካርዲናል ፓሮሊን አስታውሰዋል።

የካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ሐዋርያዊ መሪ ሆነው በቅርቡ የተመረጡት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በተመረጡበት ወቅት ባሰሙት የመጀመሪያ ንግግር፥ የጦር መሣሪያ ትጥቅ ተፈትቶ ሰላም እንዲሰፍን ያቀረቡትን ጥያቄ በማስታወስ፥ ግጭት እና መከፋፈል በሚታይበት ዓለም ውስጥ ሰላም እና አንድነት እንዲመጣ የሚደረግ ጥረት እንደሚቀጥል ተናግረዋል።

የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ በመቀጠልም፥ የአዲሱ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት የስም ምርጫ የተደረገው፥ ፈጣን የቴክኖሎጂ ዕድገት በቤተ ክርስቲያን ማኅበራዊ አስተምህሮ አውድ ላይ የሰውን ክብር እና ፍትህ በመገዳደር ፈተና ሆኖ በቀጠለበት ወቅት መሆኑን አፅንዖት ሰጥተዋል።

የቅድስት መንበር እና የተባበሩት መንግሥታት የሰላም ትብብር

ብፁዕ ካርዲናል ፓሮሊን፥ “ይህ ‘ወደ ሰላም ጎዳና’ ሽልማት ቅድስት መንበር ሰላምን ለማምጣት ላደረገችው ድጋፍ ዕውቅናን የሚሰጥ እና አንዳንድ ጊዜ ቅድስት መንበር ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጋር ያላት ግንኙነት አስቸጋሪ ቢሆንም፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳትን በተልዕኮአቸው ለሚረዷቸው ግለሰቦች እውቅናን የሚሰጥ ነው” ሲሉ ተናግረዋል። “የሰላም መንገድ በትዕግስት እና በፅናት፣ በድፍረት እና በብልሃት መጓዝ ያለበት መሆኑን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት አሳይተውናል” ሲሉም ደግመዋል።


የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብፁዕ ካርዲናል ፒየትሮ ፓሮሊን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በተቋምነት ብቻ ሳይሆን በሥነ-ምግባር እና በመንፈሳዊ ጎኑ ራሱን ማደስ እንዲቀጥል ጠይቀው፥ የዚህ ጥረት እውነተኛነት የሚታየው በሚያደርጋቸው ስምምነቶች ወይም ውሳኔዎች ሳይሆን ነገር ግን የሰውን ልጅ ልብ ወደ ላቀ ፍትህ እና ርህራሄ እንዲሁም የእያንዳንዱን ሰው ክብር በማጠበቅ እውነተኛ ለውጥ በማምጣት እንደሆነ አስረድተዋል።

ብፁዕ ካርዲናል ፒየትሮ ፓሮሊን በንግግራቸው ማጠቃለያ፥ ‘ወደ ሰላም ጎዳና’ የተሰኘው ፋውንዴሽን በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ውስጥ የቅድስት መንበር ቋሚ ታዛቢ ተልዕኮን እና ለቤተ ክርስቲያን የሰላም ተልዕኮ ላደረገው አስተዋጽኦ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

 

 

 

22 May 2025, 17:21