MAP

እህት ፓኦላ ፎሶን የ2025 የፓውሊን የኮሙዩኒኬሽን እና የባህል ሽልማትን ለቫቲካን የኮሚዩኒኬሽን ጽህፈት ቤት ዳይሬክተር ሲሰጡ እህት ፓኦላ ፎሶን የ2025 የፓውሊን የኮሙዩኒኬሽን እና የባህል ሽልማትን ለቫቲካን የኮሚዩኒኬሽን ጽህፈት ቤት ዳይሬክተር ሲሰጡ  

ፓኦሎ ሩፊኒ ወንጌልን መሰረት ባደረገ የሥራ ክንውናቸው የ2025 የፓውሊን ሽልማት ማሸነፋቸው ተነገረ

የቅድስት መንበር የኮሚዩኒኬሽን ጽህፈት ቤት ዳይሬክተር ዶ/ር ፓኦሎ ሩፊኒ በማህበራዊ ሚዲያ ላይ ከጋዜጠኝነት ዘገባ ጋር የተያያዙ የስነ ምግባር ጉዳዮች ላይ ለመወያየት በሮም በተካሄደ ዝግጅት ላይ የ2025 የፖውሊን የኮሚዩኒኬሽን እና የባህል ሽልማትን መቀበላቸው ተገልጿል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

የቀድሞው ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ በ59ኛው የዓለም የኮሚዩኒኬሽን ቀን ያስተላለፉት መልዕክት ላይ በማተኮር በሊበራ ማሪያ ዩኒቨርስቲ የተካሄደው ጉባኤ “ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ፡ በልባችሁ ያለውን ተስፋ በየዋህነት አካፍሉ” የሚል ርዕስ የነበረው ሲሆን፥ ጉባኤው ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ በኮሚዩኒኬሽን ላይ ያላቸውን አስተምህሮ ከጋዜጠኝነት ሥነ ምግባር ጋር ለማገናኘት ታስቦ እንደተካሄደም ተገልጿል።

የክልላዊ የጋዜጠኞች ማህበር፣ የብሄራዊ እና የላዚዮ ካቶሊክ ጋዜጠኞች ህብረት (UCCI) እንዲሁም የጣሊያን ዌብ-ካቶሊኮች ተቋም (WeCa) በጋራ ሆነው ያዘጋጁት ይህ ጉባኤ ከውይይት በተጨማሪም የ2025 የፓውሊን ሽልማትንም ማዘጋጀቱ ተመላክቷል።

ከር.ሊ. ጳጳሳቱ መልዕክት አንፃር ጋዜጠኝነትን እንደገና ማጤን
በጉባኤው ወቅት ንግግር ያደረጉ ተሳታፊዎች እንደገለጹት አዳዲስ ሚዲያዎች የዜና ዘገባ በሚያቀርቡበት ወቅት የሚያሳዩትን የሥነ ምግባር ጉድለቶችን ያነሱ ሲሆን፥ የሚዲያ ሰዎች ሙያቸውን በትክክለኛው መንገድ ለመምራት ለወንጌል ታማኝ ሆነው መስራት እንደሚገባቸው መክረዋል።

የፓውሊን የኮሙኒኬሽን እና ባህል ማህበር ፕሬዝዳንት እህት ፓኦላ ፎሶን የ2025 የፓውሊን ሽልማትን ለቫቲካን የመገናኛዎች ጽህፈት ቤት ዳይሬክተር ዶ/ር ፓኦሎ ሩፊኒ የሰጡ ሲሆን፥ በመርሃ ግብሩ ወቅት እህት ፓውላ እንደተናገሩት የዳይሬክተሩን “የሃሳብ ልውውጥን የሚያጎላ” እና ‘ለወንጌል መልዕክት ታማኝ’፣ እንዲሁም አካታች የሆነውን የአሰራር ዘይቤ” አወድሰዋል።

በጉባኤው ወቅት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ “ኮሚዩኒኬሽን ከፖለቲካ ወገንተኝነት እና ከጠብ አጫሪነት የጸዳ እንዲሆን ያቀረቡት ጥሪ የተነሳ ሲሆን፥ ይሄንን ተግዳሮት አዲስ የተመረጡት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ራሳቸው ግንቦት 4 ቀን 2017 ዓ.ም. በሮም ከተለያዩ ሃገራት የምርጫ ሂደቱን ለመዘገብ ከመጡ የመገናኛ ብዙኃን ተወካዮች ጋር ባደረጉት ውይይት ላይ ደጋግመው አንስተውት እንደነበረ የሚታወስ ሲሆን፥ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ በወቅቱ “ቃላቶቻችንን ከግጭት ጠማቂነት ስናፀዳ፣ ምድራችን ትጥቅ አልባ እንድትሆን እንረዳለን” በማለት ጋዜጠኞቹን አሳስበዋል።

በመረጃ ውስጥ ጨዋነት
የዌብ ካቶሊኮች ተቋም ፕረዚዳንት የሆኑት ፓውሎ ፓድሪኒ እንደገለጹት በጋዜጠኝነት ሙያ ውስጥ ጨዋነት እጅግ አስፈላጊ ነገር መሆኑን ጠቁመው ፥ በመጀመሪያ ደረጃ ጨዋነትን ማሳየት የሚገባን በቋንቋ አጠቃቀማችን ላይ እንደሆነ እና አንድን መረጃ ትክክለኛነት በቁርጠኝነት መመርመር እና ለእውነት ታማኝ መሆን እንደሚገባ በአፅንዖት ገልጸዋል።

የሮማ ሀገረ ስብከት የማህበራዊ ግንኙነት ቢሮ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አባ ስቴፋኖ ካቺዮ በበኩላቸው ‘ጋዜጠኝነት መረጃን ማስተላለፍ ብቻ ሳይሆን የሰው እና የዲጂታል ባህሎች መፍጠር እንዲሁም ለውይይት እና ለግንኙነት የሚመች ከባቢን መፍጠር ነው’ ሲሉ ያብራሩ ሲሆን፥ የቅዱስ ጳውሎስ ሴት ልጆች ማህበር አባል የሆኑት እህት ሮዝ ፓካትም ይህንን የተስፋ መልዕክት አስተጋብተዋል።

የጋዜጠኞች ኃላፊነት
በቅድስት መንበር የመገናኛዎች ጽህፈት ቤት የኤዲቶሪያል ዳይሬክተር የሆኑት አንድሪያ ቶርኒዬሊ ሰሞኑን በድህረ ገጽ ላይ በፍጥነት ሲሰራጩ የነበሩትን ቪዲዮዎችን በመጥቀስ፥ የሐሰት ዜናዎች የሚያደርሱትን ከፍተኛ ጉዳት አንስተዋል።

አቶ አንድሪያ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስን መልዕክት በመጥቀስ፥ ጋዜጠኞች የግል እና የጋራ ኃላፊነትን የግንኙነቶች ማዕከል እንዲያደርጉ አሳስበው፥ በተለይ ማህበራዊ ሚዲያ በቀላሉ ሊያሳስት እና ሊያዘናጋ ስለሚችል የግል አጀንዳዎችን ወደጎን በመተው እውነትን ብቻ በመያዝ ትክክለኛ ሥራ መስራት እንደሚገባ አሳስበዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ በወቅቱ እንዳስጠነቀቁት በዲጂታል ሥርዓቶች አማካይነት ለእውነታ ያለንን ግንዛቤ የሚያዛባ ሆን ተብሎ ትኩረትን የመበታተን አዝማሚያ እንዳለ መናገራቸውን አስታውሰዋል።

የሙያዊ ሥነ-ምግባር አስፈላጊነት
ጋዜጠኞች ይህንን የእውነታ መዛባት ማረም እንደሚገባቸው የጠቆሙት ሃላፊው፥ “ከወንጌል መንፈስ” ጋር የሚስማማ አንድ ኃይለኛ መሣሪያ ቢኖር የሥነ ምግባር ደንብ ነው” ብለዋል።

የብሄራዊ እና የላዚዮ የጋዜጠኞች ማህበር ፕሬዝዳንቶች የሆኑት ካርሎ ባርቶሊ እና ጊዶ ዲ ኡባልዶ፣ የላዚዮ የሥነ ምግባር ካውንስል ከሆኑት ሮቤታ ፌሊዚያኒ ጋር በመሆን እንደገለጹት ስነ-ምግባር ለይስሙላ የሚቀመጥ ህግ ብቻ ሳይሆን ጥብቅ ማዕቀፍ ኖሮት ሊሰራበት እንደሚገባ አጽንዖት ሰጥተዋል።

በዚህ መንገድ ጨዋነት ማለት በትኩረት ማዳመጥ፣ አስተዋይ ፍርድ መስጠት፣ ሰውን ማክበር እና ከስሜታዊነት የፀዳ ታሪክ መተረክ ሆኖ ሊገለጽ ይችላል ተብሏል።
 

29 May 2025, 14:33