በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ውስጥ በኢትዮጵያ ሥርዓት የመስዋዕተ ቅዳሴ ሥነ-ሥርዓት ተፈጸመ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
የምሥራቅ አብያተ ክርስቲያናት የኢዮቤልዩ በዓል አካል የሆነውን እና በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ውስጥ ሰኞ ግንቦት 4/2017 ዓ. ም. በተፈጸመው የመስዋዕተ ቅዳሴ ሥነ-ሥርዓት ላይ የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ካቶሊክ ብጹዓን ጳጳሳት፣ ክቡራን ካኅናት፣ ደናግል እና ምዕመናን ተካፋይ ሆነዋል።
በመስዋዕተ ቅዳሴው ሥነ-ሥርዓት መግቢያ ላይ ብፁዕ ካርዲናል ክላውዲዮ ጉጄሮቲ፥ በቅድስት መንበር የምሥራቅ አብያተ ክርስቲያናት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት መሪ ለእንግዶቹ የመልካም አቀባበል ንግግር አድርገዋል።
የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያናት እንደ ‘ሜትሮፖሊታን’ አብያተ ክርስቲያናት ራሳቸውን ችለው “sui iuris” በሕጋዊ መንገድ የተዋቀሩ እና ሁለቱም የአሌክሳንድሪያ ወግን የተከተለ የግዕዝ ሥርዓተ አምልኮን የሚጋሩ እንደሆኑ ይታወቃል።
ለከፍተኛ መንፈሳዊ ትምህርት ወደ ሮም የሚላኩ የኢትዮጵያ እና የኤርትራ አብያተ ክርስቲያናት ካኅናትም በቫቲካን በሚገኝ የኢትዮጵያ ጳጳሳዊ ኮሌጅ ውስጥ አብረው እየኖሩ ትምህርታቸውን ይከታተላሉ።
የእነዚህ አብያተ ክርስቲያናት መንፈሳዊነት ጥልቅ መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት ያለው ሲሆን፥ በአንደኛ መጽሐፈ ነገሥት ምዕ. 10 እና በ2ኛ ዜና መዋዕል ምዕ. 9 ላይ ተጽፎ እንደምናገኘው፥ ከንግሥተ ሳባ ታሪክ ጀምሮ እስከ ንጉሥ ሰሎሞን መንግሥት ድረስ እንዲሁም የአክሱም ዙፋን ወራሽ ከሆነው ልጃቸው ምኒልክ ጋር የተያያዘ ጥልቅ መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት ያለው እንደሆነ ይታወቃል።
በሐዋርያት ሥራ ምዕ. 8 ላይ የተጻፈው የዲያቆን ፊልጶስ ታሪክ፥ የኢትዮጵያ ንግሥት ከነበረች ከሕንደኬ ጋር መገናኘቱ ሌላውን መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት ይገልጻል።