ብጹአን ካርዲናሎችን በአንድ ክፍል ውስጥ ቆልፎ ማቆየት እንዴት ‘ኮንክሌቭ’ (ዝግ ጉባኤ) በመባል ሊጠራ ቻለ?
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
ሮም ሁሌም የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት የስልጣን መቀመጫ መንበር ከተማ እንዳልነበረች የሚታወቅ ሲሆን፥ በቤተክርስቲያኒቷ ታሪክ ተመራጭ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ለሁለት ጊዜያት ከሮም ውጭ መኖራቸው የታሪክ ድርሳናት የሚያሳዩ እንደሆነ እና በዚህም ከዘላለማዊቷ ከተማ ሮም ርቀው የቅዱስ ጴጥሮስ ተተኪ በመሆን የአገልግሎት ጊዜያቸውን እንዳሳለፉ ይታወቃል።
በ 14ኛው ክፍለ ዘመን በካቶሊክ ቤተክርስቲያን እና ከፈረንሣይ ንጉሠ ነገሥት መካከል የተፈጠረውን ግጭት ተከትሎ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ለ 68 ዓመታት የደቡባዊ ምስራቅ ፈረንሳይ ከተማ በሆነችው አቪኞን መኖራቸው የሚታወቅ ሲሆን፥ በዚህም መሰረት አብዛኛው ሰው እንደሚያውቀው ‘አቪኞን ፓፓሲ’ ወይም የአቪኞን መንበር ተብሎ ይጠራ እንደነበር ይነገራል።
ነገር ግን፥ ምናልባት ብዙም ያልታወቀው እና የበለጠ ጉልህ ጊዜ ሊሆን የሚችለው ከሮም በሰሜን አቅጣጫ፣ በ90 ደቂቃ መንገድ ርቀት ላይ የምትገኘው ቪቴርቦ የምትባለዋ ትንሽዬ ከተማ የዘጠኝ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት መኖሪያ ብቻ ሳይሆን፣ ዛሬ ላይ የሚታወቀውን የዝግ ጉባኤ ወይም ‘ኮንክሌቭ’ ተብሎ የሚጠራው ጉባኤ የተጀመረባት ከተማም ጭምር ነበረች።
ይህች የቪቴርቦ ከተማ በወቅቱ የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት መቀመጫ እንድትሆን የተመረጠችበት ምክንያት የተለያዩ ሃሳቦች ይጠቀሳሉ።
ከሮም በስተሰሜን 90 ማይል ርቀት ላይ ትገኛለች
በ13ኛው ክፍለ ዘመን ሮም ዛሬ ከምናየው በጣም የተለየች እንደነበረች የሚታወቅ ሲሆን፥ በአመጽ እና በመከፋፈል የተሞላች፣ ከዚህም በተጨማሪ ጓልፍ እና ጊቤሊንስ የሚባሉ ሁለት ቤተሰቦች በዛን ወቅት ጳጳሳትን እና አባቶችን የመሾም ስልጣን ላይ እርስ በርሳቸው ከፍተኛ ግጭት ውስጥ እንደነበሩ መረጃዎች ያሳያሉ። ከሁለቱ ቤተሰቦች ውስጥ አንደኛው ዓለማዊው ገዢ ሥልጣን እንዳለው ያምን የነበረ ሲሆን፥ ሌላኛው ደግሞ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ መንግስታዊውንም ሥልጣን ጭምር እንዳላቸው ይሟገታል።
በዚህም ምክንያት የሮም ከተማ በግጭት የተሞላች እና ደህንነቱ ያልተጠበቀ የነበረ ስለሆነ በወቅቱ የነበሩት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት አሌክሳንደር አራተኛ የጳጳሱን መንበር ወደ ቪቴርቦ ለማዛወር ተገደዋል።
ትንሿ ከተማ ቪቴርቦ ለሮም ያላት ቅርበት፣ ከጓልፍ ቤተሰብ ጋር ያለው ትስስር እና በሁለት ማይል ተኩል ዙሪያ በግንብ የታጠረች መሆኗን ጨምሮ በተለያዩ በርካታ ምክንያቶች ልትመረጥ እንደቻለች ይነገራል።
የቪቴርቦ ከተማ ክርስቲያኖች ‘ቪያ ፍራንቺ-ጌና’ ብለው የሚጠሩት እና ወሳኝ መንፈሳዊ ንግደት የሚያደርጉበት መስመር ላይ ስለነበረች ትልቅ ቦታ የሚሰጧት ከተማ እንደሆነም ጭምር ይታወቃል።
በእነዚህ ሁሉ ወሳኝ ሁኔታዎች ምክንያት በጎረጎሳዊያኑ በ 1257 ዓ.ም. ሮም የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት መኖሪያነቷ ቀርቶ፥ ቪቴርቦ እንደተመረጠች የቤተክርስቲያኗ ታሪክ ይናገራል።
በወቅቱ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት እንዴት ይመረጡ ነበር?
ከ 1257 እስከ 1281 ዓ.ም. ድረስ፣ ለ 24 ዓመታት በቪቴርቦ የሚገኘው የጳጳሳት መኖሪያ ህንፃ የሊቃነ ጳጳሳት መኖሪያ ሆኖ ያገለገለ ሲሆን፥ በነዚህም ዓመታት የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን መሪ እንዲሆኑ ዘጠኝ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት የተመረጡት በዚህ ቦታ ነበር።
ይሁን እንጂ እስከ 1268 ዓ.ም. ድረስ የምርጫው ሂደት ከዛሬው በጣም የተለየ፥ በጣም ግልጽ እና ጥልቅ እንደነበር ይገለፃል።
የታሪክ ተመራማሪዎች እና የቀኖና ሊቃውንት በአጠቃላይ እስከ 13ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ድረስ የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳዊነት ሚና እንደሌሎች የሀገረ ስብከት ጳጳሳት ሁሉ ተቀራራቢ የነበረ መሆኑን የሚገልጹ ሲሆን፥ ይህም ማለት የአዲስ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ምርጫ የሚደረገው በአጎራባች ጳጳሳት፣ ቀሳውስት እና የሮም ምዕመናን እንደሆነ የሚገልጹ እንዳሉ ሁሉ፥ ሌሎች ደግሞ ምእመናን በምርጫው ሂደት ውስጥ የተካተቱት ከርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሲልቬስተር 1ኛ በኋላ እስከ 4ኛው ክፍለ ዘመን ድረስ እንደሆነ ይከራከራሉ። ከዚህም በተጨማሪ አንዳንድ ጊዜ የአውሮፓ ንጉሠ ነገሥታት እና ንግሥታት የጴጥሮስ ተተኪን ለማግኘት በሚደረገው ምርጫ እንደሚሳተፉ ይነገራል።
የሆነ ሆኖ፥ የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ምርጫ ሂደት ላይ ከፍተኛ ለውጥ እንዳመጣ በሚነገረው የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ክሌመንት አራተኛ እስካረፉበት ዓመት ድረስ የኮንክሌቭ ወይም ዝግ ጉባኤ ሐሳብ እንዳልተጀመረ ይገለፃል።
እስኪወስኑ ድረስ ይቆለፍባቸዋል
እ.አ.አ. በ 1268 ዓ.ም. ቤተክርስቲያኒቱ የሐዋርያዊ መንበሩ "ሴዴ ቫካንቴ" (ባዶ መንበር) የመሆን አጋጣሚ ስለገጠማት አዲስ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ምርጫ እንዲካሄድ ተደርጎ ነበር።
በዚያን ጊዜ ከ 20 መራጭ ካርዲናሎች መካከል 19 ቱ የጴጥሮስ ተተኪን ለመምረጥ በሚደረገው ጉባኤ ላይ ለመሳተፍ ወደ ቪቴርቦ የተጓዙ ሲሆን፥ ይህ ምርጫ በቤተክርስቲያን ታሪክ ውስጥ ረጅሙ ጉባኤ እንደሚሆን ማንም አልገመተም ነበር።
በወቅቱም በተለያየ ምክንያት አዲስ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሳይመረጡ አንድ ዓመት ስለሆነው፥ የቪቴርቦ ዜጎች ጉዳዩን በቅርበት መከታተል እንደጀመሩ እና ብጹአን ካርዲናሎቹ ውሳኔ እንዲያደርጉ ግፊት ለማድረግ ሲሉ ካፒቴን ራኒዬሮ ጋቲ ከተባለ ሰው ጋር በመሆን በርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ መኖሪያ ህንፃ ውስጥ የሚገኙትን መራጭ ካርዲናሎችን በላቲን ቋንቋ “ኩም ክሌቭ” በሚባል ቁልፍ እንደቆለፉባቸው፣ በዚህም መሰረት አሁን ላይ የምርጫ ሥነ ስርዓቱ ‘ኮንክሌቭ’ ተብሎ እንደሚጠራ የቤተክርስቲያኒቱ ታሪክ የሚያሳይ ሲሆን፥ ከውጭ የተቆለፈባቸው መራጭ ካርዲናሎች ዳቦ እና ውሃ ብቻ ይሰጣቸው እንደነበር ይገለፃል።
በመጨረሻም፣ ከሦስት ዓመታት በላይ ያለ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ከቆዩ በኋላ በ 1271 ዓ.ም. መስከረም ወር ላይ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ግሪጎሪ 10ኛ ተመርጠዋል።
የተገኙ ትምህርቶች
በቪቴርቦ የተደረገውን ልምድ በመከተል፥ አንዳንድ ብጹአን ካርዲናሎች ረጅሙ እና መደበኛ ያልሆነው ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳትን የመምረጥ ሂደት ጊዜ ያለፈበት መሆኑን የተገነዘቡ ሲሆን፥ በወቅቱ የተመረጡት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ግሪጎሪ 10ኛ አዲስ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳትን ለመምረጥ የሚያስችል ተጨባጭ ሕጎችን የያዘ “ኡቢ ፔሪኩለም” የተባለ ሐዋርያዊ መተዳደሪያ ደንብ አሳትመው እንዳወጡ እና ይህ ሐዋርያዊ ሕገ መንግሥት ወይም መተዳደሪያ ደንብ ቤተክርስቲያን ዛሬም ለምትጠቀምበት የዘመናችን የምርጫ ሂደት መሠረት ሆኖ እያገለገለ እንደሚገኝ ይገለፃል።
እነዚህ አዳዲስ ሕጎች ታትመው ቢወጡም፥ አዲሱ የምርጫ ሂደት ወዲያውኑ ተቀባይነት እንዳላገኘ የሚታወቅ ሲሆን፥ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ቦኒፌስ ስምንተኛ ‘ኡቢ ፔሪኩለምን’ በቀኖና ሕግ ውስጥ በማካተት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳትን የመምረጥ ብቸኛ መንገድ አድርገው ደንግገዋል።
በዚህም መሰረት በታሪክ ውስጥ ረጅሙ የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ምርጫ የተደረገባት እና የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ከተማ ተብላ የምትጠራው ቪቴርቦ የኮንክሌቭ ወይም ዝግ ጉባኤ ጽንሰ ሃሳብ መነሻ ቦታ ሆናለች።