በኢትዮጵያ እና በኤርትራ ካቶሊክ ምዕመናን መካከል አንድነትን የሚያጎለብት የቅዳሴ መጽሐፍ ተዘጋጀ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
በርካታ የፕሬስ አባላትን ጨምሮ ጳጳሳት፣ ካህናት፣ ገዳማውያን እና ገዳማውያት እንዲሁም ምእመናን በተገኙበት በኢትዮጵያ ጳጳሳዊ ኮሌጅ ቅጥር ጊቢ በተዘጋጀው ሥነ-ሥርዓት ላይ አዲሱ የግዕዝ ሥርዓት የቅዳሴ መጽሐፍ ተመርቋል።
ቫቲካን ውስጥ በአትክልት ሥፍራ ታንጾ የሚገኘው የኢትዮጵያ ጳጳሳዊ ኮሌጅ፥ በኢትዮጵያ እና በኤርትራ የምሥራቅ ካቶሊካዊ አብያተ ክርስቲያናት መካከል ጥቅም ላይ የሚውለውን አዲሱን የግዕዝ ቋንቋ የቅዳሴ መጽሐፍ ማክሰኞ ግንቦት 19/2017 ዓ. ም. ምሽት አስመርቋል።
በምሥራቅ አብያተ ክርስቲያናት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት መሪነት የተዘጋጀው የቅዳሴ መጽሐፉ፥ የመስዋዕተ ቅዳሴ ሥነ-ሥርዓት መመሪያዎችን እና ጽሑፎችን የያዘ የአምልኮ መጽሐፍ ሲሆን፥ ለአፍሪካ ቀንድ አገራት ኢትዮጵያ እና ኤርትራ የጋራ የሆነ የሥርዓተ አምልኮ መጽሐፍ አስፈላጊነትን የሚሳይ ሲሆን፥ ግዕዝ በኢትዮጵያ እና ኤርትራ ካቶሊካዊ ቤተ ክርስቲያናት እና በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናት ዘንድ ለሥርዓተ ቅዳሴ የሚያገለግል ጥንታዊ የደቡብ ሴማዊ ቋንቋ ነው።
በዝግጅቱ ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የምሥራቅ አብያተ ክርስቲያናት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት አስተባባሪ ብጹዕ ካርዲናል ክላውዲዮ ጉጄሮቲ እንደተናገሩት፥ ተሻሽሎ የቀረበው የግዕዝ የቅዳሴ መጽሐፍ፥ ለኢትዮጵያ እና ለኤርትራ ሕዝቦች “የጸሎት መሣሪያ” ሆኖ እንደሚያገለግል ገልጸው፥ በጽሕፈት ቤቱ ሥር የሚገኝ የሥርዓተ አምልኮ መምሪያ ክፍል ለብዙ አስርት ዓመታት ለምሥራቅ አብያተ ክርስቲያናት የሚያገለግሉ በርካታ የአምልኮ ሥርዓት መጽሕፍት ማዘጋጀቱን ገልጸዋል።
ካርዲናል ክላውዲዮ ጉጄሮቲ አክለውም ይህ ባሕል በግዕዝ የቅዳሴ መጽሐፍ ዝግጅት ላይ “ዘውድ ያጎናጸፈ ነው” ሲሉ ገልጸው፥ “የአምልኮ ሥርዓቱ በሕይወት የመቆየት ችሎታ ምንጭ እና የሕልውና መሠረት ሕዝቡ ነው” ሲሉ አስረድተዋል።
“ሕዝቡ ዜማውን፣ ምድርን እና ሰማይን የሚያስተሳስረውን ስልትን ከተቀማ፥ ሕልውናው እጅግ ጨካኝ እና ድሃ በሆነ የመንፈስ አደጋ ውስጥ ይወድቃል” ያሉት ብጹዕ ካርዲናል ጉጄሮቲ፥ የኤርትራ እና የኢትዮጵያ ሕዝቦች በዚህ የቅዳሴ መጽሐፍ አማካይነት በእግዚአብሔር የፍቅር ቸርነት እና በእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም እንክብካቤ ዘወትር ጥንካሬን ያገኛል” ሲሉ አስረድተዋል።
በኢትዮጵያ የአዲግራት ሀገረ ስብከት ጳጳስ አቡነ ተስፋስላሴ መድኅን የግዕዝ መጸሐፈ ቅዳሴ መታተም በደስታ ተቀብለው፥ በኢትዮጵያ እና በኤርትራ አብያተ ክርስቲያናት መካከል የአንድነት ምንጭ ሆኖ ያገለግላል ብለዋል።
“በጣም አስቸጋሪ በሆኑ ጊዜያት መስዋዕተ ቅዳሴ በአንድነት መንፈስ ሲከበር ውስጣዊ ደስታን፣ ብርታትን እና ተስፋን ይሰጣል” ብለዋል።
“በውል ያልተለየ ማንነት እግዚአብሔር የሰጠን አይደለም” ያሉት አቡነ ተስፋሥላሴ፥ “በቤተ ክርስቲያናችን የሚቀርበው የመስዋዕተ ቅዳሴ ሥነ-ሥርዓት በአዲሱ የቅዳሴ መጽሐፍ መሠረት የሚፈጸም ከሆነ የቅዳሴ መጽሐፉን በሀገረ ስብከታችን ውስጥ እንደ ቅዱስ መሣሪያ በታማኝነት ልንጠቀምበት እንችላለን” ብለዋል።
ብጹዕ አቡነ ተስፋሥላሴ ለቫቲካን የዜና አገልግሎት እንደተናገሩት፥ የኤርትራ እና የኢትዮጵያ ካቶሊካዊ አብያተ ክርስቲያናት ተባብረው እንዳይሰሩ የሚያግዱ ፖለቲካዊ እንቅፋቶች ቢኖሩም፣ ምን ጊዜም አንድነት የሚሻል መሆኑን አስምረውበታል። “በመካከላችን የመከፋፈል መንፈስ የለንም” ያሉት ብጹዕ አቡነ ተስፋሥላሴ፥ “የእኛ የሥርዓተ አምልኮ ታሪካችን ልዩነት አጋጥሞት አያውቅም” ብለዋል።
ብፁዕ ካርዲናል ጉጄሮቲ በምረቃው ሥነ-ሥርዓት ማጠቃለያ ላይ የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ካቶሊክ አብያተ ክርስቲያናትን ወክለው ለቀረቡት ብጹዓን ጳጳሳት አዲሱን የቅዳሴ መጽሐፍ በይፋ አቅርበዋል።
በኤርትራ የከረን ሀገረ ስብከት ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ኪዳኔ ዬቢዮ ለቫቲካን ዜና አገልግሎት እንደተናገሩት፥ የቅዳሴ መጽሐፉን ወደ ፍጻሜ ለማድረስ 25 ዓመታትን እንደፈጀ ተናግረው፥ “ይህም የሆነው ጥንታዊው ግብ ዓቶችን በማሰባሰብ እና የቀደሙ የግዕዝ የቅዳሴ መጽሐፍትን ዋቢ ለማድረግ ጥረት ሲደርግ ነው” ብለዋል።
ብጹዕ አቡነ ኪዳኔ ዬቢዮ፥ “ይህ የቅዳሴ መጽሐፍ ለኢትዮጵያ እና ለኤርትራ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የአንድነት ምንጭ ይሆናል፤ ምክንያቱም እስካሁን ድረስ በተለያዩ መንገዶች ስናከብር ቆይተናል፤ ከአሁን በኋላ ግን ሁላችንም ይህን መጽሐፍ እንደምንከተል ተስፋ እናደርጋለን” ብለዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በቅርቡ ግንቦት 6/2017 ዓ. ም. ለምሥራቅ አብያተ ክርስቲያናት የኢዮቤልዩ በዓል ተሳታፊዎች ባደረጉት ንግግር፥ የምሥራቅ አቢያተ ክርስቲያናት ሥርዓተ አምልኮ ከካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ጋር ኅብረት እንዳለው አጽንተዋል።
ቅዱስነታቸው በዕለቱ ባስተላለፉት መልዕክት፥ “በዛሬው ጊዜ የምሥራቅ ክርስቲያን የሚያበረክተው አስተዋጽኦ እጅግ ብዙ በመሆኑ ቤተ ክርስቲያን ትፈልጋችኋለች” ማለታቸውም ይታወሳል።