የአውሮፓ ካቶሊካዊ ጳጳሳት በዩክሬን ጦርነት ቆሞ ፍትሃዊ ሰላም መውረድ እንደሚያስፈልግ ተናገሩ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ሰላምን በተመለከተ በተለይም በዩክሬን ያለውን ቀውስ እና የመልሶ ማቋቋም ሥራን በማስመልከት ባደረጉት ንግግር፥ ለጦር መሣሪያ የሚወጣው ወጪ ከፍተኛ ትኩረት ለሚያስፈልጋቸው እና አቅመ ደካማ ለሆኑ ሰዎች የሚደረገውን ድጋፍ እንደሚጎዳ ገልጸው፥ ለብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤዎች ምክር ቤት ካቀረቧቸው ዋና ዋና ጭብጦች መካከል አንዱ ሰላም እንደሆነ ተመልክቷል።
በአውሮፓ ውስጥ የሚታይ አሳሳቢ ጊዜ
የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ምርጫ ከተካሄድ ከጥቂት ቀናት በኋላ እና ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ዕረፍት አንድ ወር በኋላ ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ጋር መገናኘታቸው ትልቅ ትርጉም ያለው መሆኑን የምክር ቤቱ አባላት ተናግረው፥ ቅዱስነታቸው ከሁሉም በላይ ለማዳመጥ ባላቸው ፍላጎት የሰላም ውጥን ሆኖ ለተወለደው የአውሮፓ-ተቋም ተግባራዊነት ከፍተኛ ትኩረት መስጠታቸውን ገልጸዋል።
በያዝነው የጎርጎሮሳውያኑ ዓመት መጀመሪያ ላይ መሪነቱን ከተረከበው አዲሱ የአሜሪካ አስተዳደር ጋር እና እንዲሁም በበርካታ አገራት ውስጥ የሚታዩ ወጥነት የሌላቸው አሳሳቢ የሕዝብ አስተያየቶች መስፋፋት ብዙ ጊዜ ከአውሮፓ ኅብረት ዋና ዋና መርሆዎች ጋር የሚጋጩ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ለጦርነት የሚውል ወጪዎች ለአቅመ ደካሞች የሚደረገውን ድጋፍ ይጎዳል
የአውሮፓ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤዎች ምክር ቤት ምክትል ፕሬዝደንት ሊቀ ጳጳስ አንትዋን ሄሩዋርድ በዕለቱ ባሰሙት ንግግር፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በተለይም በዩክሬን በመካሄድ ላይ ባለው ጦርነት በሰዎች ሕይወት ላይ ላስከተለው ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ መዘዝ አፅንዖት መስጠታቸውን ገልጸዋል።
የፈረንሳዩ ሊቀ ጳጳስ አክለውም፥ የመከላከያ እና የደህንነት ሥርዓቶችን ለማጠናከር ሲባል ተጨማሪ ገንዘብ መመደቡ በስቃይ ወይም በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ለሚገኙ ሰዎች የሚደረገውን ዕርዳታ ሊጎዳ እንደሚችል ቅዱስነታቸው መናገራቸውን በማስታወስ፥ የአውሮፓ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት በሙሉ፥ በዩክሬን ውስጥ በመካሄድ ላይ የሚገኘው ጦርነት ቆሞ ቶሎ ብሎ ፍትሃዊ ሰላም እንዲመጣ መፈለጋቸውን ገልጸዋል።
“በሰላም እና በፍትህ መካከል ያለው ሚዛን መሠረታዊ ነው” ያሉት የምክር ቤት ምክትል ፕሬዝደንት የሊቱዌኒያው ሊቀ ጳጳስ ሪማንታስ ኖርቪላ በበኩላቸው ሲናገሩ፥ “ምንም እንኳን እስካሁን ተጨባጭ መፍትሄዎችን ባናይም፥ ዛሬ ሁሉም የአውሮፓ ሀገራት ጦርነቱ በተቻለ ፍጥነት ለማስቆም ባለን ዓላማ ውስጥ ተሳትፎ ሊሰማቸው ይገባል” ብለዋል።
ስደት በተመለከተ አቀባበልን እና ውህደት ማመጣጠን
ብጹዓን ጳአሳት ከቅዱስነታቸው ጋር ከተወያዩባቸው ርዕሠ ጉዳዮች መካከል ስደት አንዱ ሲሆን፥ ሌላው የምክር ቤት ምክትል ፕሬዝደንት ፖርቱጋላዊው ጳጳስ አቡነ ኑኖ ብራስ ዳ ሲልቫ ማርቲንስ ስደትን በማስመልከት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ተናግረዋል።
በአንድ በኩል በአውሮፓ ውስጥ የታየውን የሕዝብ መቀነስ ለመከላከል አውሮፓ ስደተኞችን መቀበል እንዳለባት በሌላ በኩል ነገር ግን ወደ አገራቱ የሚደርሱ ስደተኞችን ከማኅበረሰቡ ጋር በማዋሃድ ረገድ የተወሰነ ችግር መኖሩን በግልጽ የሚያሳይ መሆኑ አስረድተው፥ ሰብዓዊ ክብርን ማስከበር ክርስቲያናዊ መሠረት ያለው የአውሮፓ ርዕሠ ጉዳይ እንደሆነ ገልጸዋልል።
ወጣቶችን መከታተል እና በቤተሰብ ውስጥ እምነትን ማስተላለፍ
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ በዩክሬን በመካሄድ ላይ ባለው ጦርነት በሰዎች ሕይወት ላይ ላስከተለው ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ መዘዝ አፅንዖት መስጠታቸውን የገለጹ ሲሆን፥ የኮፐንሃገን ጳጳስ እና የስካንዲኔቪያ አገራት የጳጳሳት ጉባኤዎች ተወካይ ምክትል ፕሬዝዳንት አቡነ ቼስላው ኮዞን በተለይም በምስጢረ ጥምቀት መዝገቦች መሰረዝ ላይ አፅንዖት የሰጡ ሲሆን፥ ይህ ክስተት እንደ ቤልጂየም እና ኔዘርላንድስ ባሉ በርካታ አገራት ውስጥ እየጨመረ እንደሆነ ተናግረዋል።
ልጆች ወላጆቻቸውን “በእምነት ምርጫ ላይ ጫና አድርገውብናል” ብለው ከሚወነጅሉት በተጨማሪ መንግሥታት በቤተ ክርስቲያኒቱ ሕይወት እና መዋቅር ውስጥ ጣልቃ መግባታቸው የሃይማኖት ነፃነትን ጥያቄ ውስጥ የሚያስገባ ነው” ሲሉ ገልጸው፥ “ወላጆች ልጆቻቸውን ስለ እምነት የማስተማር መብት እና ግዴታ አለባቸው” ሲሉ ተናግረዋል።
የአውሮፓ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤዎች ምክር ቤት ዋና ፀሐፊ አባ ማኑኤል ባሪዮስ ፕሪቶ በበኩላቸው፥ “ከአሁን በኋላ ከካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን የጥምቀት መዝገብ ውስጥ ስም ወደ መሰረዝ የሚኬድ ከሆነ ይህ በእውነቱ የቤተ ክርስቲያንን ነፃነት እና የራስ ገዝ አስተዳደርን ካለማክበር ጋር የተያያዘ ጥቃትን ያስከትላል” ሲሉ አስረድተዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት በሰው ሠራሽ አስተውሎት ላይ የሰጡት ትኩረት
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ለብጹዓን ጳጳሳቱ ባደረጉት ንግግር፥ በሰው ሠራሽ አስተውሎት ወይም “አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ” ላይ ከፍተኛ ትኩረት የሰጡ ሲሆን፥ “ይህ ርዕሠ ጉዳይ ሐሰተኛ መረጃ ልውውጥን፣ ሰብዓዊ ክብርን፣ ምስጢራዊነትን፣ ማንነትን እና ነፃነትን የሚያካትት፥ ውጤቱም በሥራ ዕቅድ ላይ መዘዝ ማስከተል ነው” ሲሉ ቅዱስነታቸው አስረድተዋል።