MAP

ብጹዓን ካርዲናሎች በስምንተኛ ጠቅላላ ጉባኤያቸው በስብከተ ወንጌል እና በተልዕኮ ላይ ተወያዩ

በቫቲካን የሚገኙት ብጹዓን ካርዲናሎች ዓርብ ዕለት ባካሄዱት 8ኛ ጠቅላላ ጉባኤያቸው፥ ስብከተ ወንጌል፣ ወንድማማችነት፣ ሲኖዶሳዊነት እና አንድነት በሚሉት ርዕሠ ጉዳዮች ላይ ውይይት አደርገውባቸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የቅድስት መንበር መግለጫ ክፍል ዳይሬክተር አቶ ማቴዎ ብሩኒ፥ ዓርብ ሚያዝያ 24/2017 ዓ. ም. ማለዳ ላይ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፥ በስምንተኛው ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ከ180 የሚበልጡ ብጹዓን ካርዲናሎች መሳተፋቸውን እና ለመጪው የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ምርጫ ዝግጅት በማድረግ ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል።

ጉባኤያቸውን ዓርብ ዕለት ከጠዋቱ ሦስት ላይ በጸሎት ከጀመሩት 180 ካርዲናሎች መካከል ከ120 በላይ የሚሆኑት መራጭ ካርዲናሎች ሲሆኑ ባለፉት ጥቂት ቀናት ውስጥ ከደረሱት አንዳንድ ካርዲናሎች ጋር በኅብረት ጠዋት ላይ ቃለ-መሃላ መፈጸማቸው ታውቋል።

በጉባኤው ላይ የተደረጉ 25 ንግግሮችን መሠረት በማድረግ ውይይት ከተደረገባቸው ርዕሠ ጉዳዮች መካከል፥ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ዋና ትኩረት የሆነው የወንጌል ስርጭት፣ የቤተ ክርስቲያን ወንድማዊ የወንጌል ሰባኪነት፣ ወንጌልን በተለይም ለወጣቶች የመመስከር አስፈላጊነት፣ የምሥራቅ አብያተ ክርስቲያናት መከራ እና ምስክርነት፣ በሁሉም ደረጃዎች ማለትም ከቁምስናዎች እስከ ቅድስት መንበር ከፍተኛ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ድረስ የወንጌል ምስክርነትን ውጤታማ ስለ ማድረግ፣ “እርስ በርሳችሁ ብትዋደዱ ደቀ መዛሙርቴ መሆናችሁን ሰዎች ያውቃሉ” በሚለው የቅዱስ ወንጌል ጥቅስ መሠረት ስለ ወንጌል ምሥክርነት እና ስለ አንድነት ግዴታ፣ ጾታዊ በደልን ጨምሮ ገንዘብን አለ አግባብ መጠቀም ሊያስከትል ስለሚችለው አደጋ፣ የሥርዓት አምልኮ ማዕከላዊነት፣ የሕገ ቀኖና አስፈላጊነት፣ ሲኖዶሳዊነት እና አንድነት፣ ሲኖዶሳዊነት እና ተልዕኮ፣ ሲኖዶሳዊነት እና ዓለማዊነት፣ በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ፣ በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቤነዲክቶስ 16ኛ እና በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራችስኮስ አስተምህሮዎች መካከል ያለው ቀጣይነት፣ ቅዱስ ቁርባን በሚስዮናዊነት አገልግሎት ውስጥ ያለው ሚና አስፈላጊነት የሚሉት ርዕሦች ይገኙባቸውል።

ከቀኑ በስድስት ሰዓት ተኩል በተጠናቀቀው ጉባኤ ላይ የቅድስት መንበር መግለጫ ክፍል ዳይሬክተር አቶ ማቴዎ ብሩኒ፥ ከካርዲናል ፒየትሮ ፓሮሊን የጤና ሁኔታ ጋር በተያያዘ ከጋዜጠኛው ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ፥ “ይህ እውነት አይደለም” ሲሉ አስተባብለዋል። በካርዲናል ፒየትሮ ፓሮሊን የጤና ሁኔታ ዶክተሮች ወይም ነርሶች ጣልቃ ገብተዋል የተባለውንም አቶ ማቴዎ ብሩኒ በተጨማሪ አስተባብለዋል።

 

 

 

03 May 2025, 16:55