ብጹዓን ካርዲናሎች በኢዮቤልዩ ዓመት ቤተ ክርስቲያን ተስፋ እንደሚያስፈልጋት ገለጹ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
በሮም የሚገኙት 177 ብፁዓን ካርዲናሎች ቅዳሜ ሚያዝያ 25/2017 ዓ. ም. ከሰዓት በፊት ባካሄዱት ዘጠነኛ ጠቅላላ ጉባኤያቸው፥ በሂደት ላይ ባለው የኢዮቤልዩ በዓል ወቅት በተስፋ አስፈላጊነት ላይ ተወያይተዋል።የቅድስት መንበር መግለጫ ክፍል ዳይሬክተር አቶ ማቴዎ ብሩኒ ቅዳሜ ማለዳ ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት፥ ለመጪው የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ምርጫ ዝግጅት እንዲሆን በተካሄደ ዘጠነኛው ጠቅላላ ጉባኤ ላይ 177 ብፁዕ ካርዲናሎች መገኘታቸውን ገልጸዋል።
በጸሎት ሥነ-ሥርዓት በሦስት ሰዓት የተጀመረ ጉባኤ
በዘጠነኛው የብጹዓን ካርዲናሎች ጉባኤ ላይ ከተገኙት 177 ካርዲናሎች መካከል 127ቱ መራጭ ካርዲናሎች ሲሆኑ በጉባኤውም 26 ንግግሮች ቀርበዋል።
የካርዲናሎች ጉባኤ ውይይት ያደረገባቸው ርዕሠ ጉዳዮች፥ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያለ ኅብረት እና ዓለም አቀፍ ወንድማማችነት፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ “የወንጌል ደስታ” በሚለው ሐዋርያዊ ማበረታቻቸው አማካይነት የጀመሯቸውን ሂደቶች በመጥቀስ ምስጋና ማቅረብ፣ በአብያተ ክርስቲያናት መካከል ባለው መተጋገዝ እና ትብብር፣ ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ጋር ያለውን ግንኝነት በተመለከተ የከፍተኛ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤቶች ሚና፣ ሰላምን በማስፈን ረገድ የቤተ ክርስቲያን እና የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት አገልግሎት፣ የትምህርት እሴት፣ ተስፋን እጅግ ለተጠማች ቤተ ክርስቲያን ብርሃንን ለማምጣት በሚደረግ ጥረት ውስጥ የአዲሱ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ትንቢታዊነት የሚሉ ርዕሦች ከቅርብ ቀናት ወዲህ ከታዩት ተደጋጋሚ ጭብጦች መካከል እንደ ነበሩ የገለጹት አቶ ማቴዎ ብሩኒ ስለ ሲኖዶሳዊነት እና ኅብረትም በመጥቀስ፥ ኢዮቤልዩ እና የተስፋ ጭብጥ፣ ዓለምን ለቤተ ክርስቲያን ያለው ጥማት እና ፍላጎት፣ ቤተ ክርስቲያን በራሷ ዓለም ውስጥ የምትኖር ኢምንት ሳትሆን ነበር ግን በዓለም ውስጥ ስለ መኖሯ፣ የክርስቲያኖች አንድነት የጋራ ውይይት እና ተልዕኮ በሚሉት ላይ ጉባኤው መወያየቱን ተናግረዋል።
የሮም ቤተ ክርስቲያን የንብረት እና የፋይናንስ ክፍል አስተዳዳሪ የሆኑትን ብፁዕ ካርዲናል ኬቨን ጆሴፍ ፋሬልን በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ እገዛ እንዲያደርጉ በማለት ብፁዕ ካርዲናል ፍራንሲስ ፕሬቮስትን እና ብጹዕ ካርዲናል ማርቼሎ ሰመራሮን ጉባኤው የመረጧቸው ሲሆን፥ ሦስተኛው የኮሚሽኑ አባል ብፁዕ ካርዲናል ራይንሃርድ ማርክስ የኢኮኖሚ ምክር ቤት አስተባባሪ ሆነው ይቆያሉ።
የካርዲናሎች ጠቅላላ ጉባኤ መሪ ብፁዕ ካርዲናል ጆቫኒ ባቲስታ ሬ በግንቦት ወር በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ውስጥ በየሳምንቱ ቅዳሜ ምሽት ከሦስት ሰዓት ጀምሮ የመቁጠሪያ ጸሎት የሚቀርብ መሆኑን አስታውሰው፥ በወሩ ውስጥ በሚውሉ እሑዶች ብፁዓን ካርዲናሎች ሮም ከተማ ውስጥ በሚገኙ ቤተ ክርስቲያኖቻቸው የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት እንደሚያሳርጉ አስታውቀዋል።
ከጋዜጠኞች ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡት የቅድስት መንበር መግለጫ ክፍል ዳይሬክተር አቶ ማቴዎ ብሩኒ፥ በቅድስት ማርታ የጳጳሳት መኖሪያ ውስጥ ካርዲናሎችን ለማስተናገድ የተጀመረ ሥራ ወደ ላቀ ደረጃ ላይ መድረሱን እና እስከ ሰኞ ሚያዝያ 27/2017 ዓ. ም. ድረስ እንደሚጠናቀቅ ገልጸዋል።
ብፁዓን ካርዲናሎቹ ከማክሰኞ ሚያዝያ 28/2017 ዓ. ም. ጀምሮ እስከ ረቡዕ ሚያዝያ 29/2017 ዓ. ም. ጠዋት ድረስ ወደ ቅድስት ማርታ የጳጳሳት መኖሪያ እንደሚገቡ፥ ነገር ግን በተመሳሳይ ዕለት ከአዲሱ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ምርጫ ቀደም ብሎ በሚቀርበው የመስዋዕተ ቅዳሴ ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
ሰኞ ሚያዝያ 27/2017 ዓ. ም. የካርዲናሎች ጠቅላላ ጉባኤ ሁለተኛ ዙር ስብሰባ ከምሽቱ አንድ ሰዓት ላይ ከተጠናቀቀ በኋላ ለጋዜጠኞች ማብራሪያ ሊሰጥ እንደሚችል የተገለጸ ሲሆን፥ ብጹዓን ካርዲናሎች ማክሰኞ ሚያዝያ 28/2017 ዓ. ም. ጠዋቱ በሦስት ሰዓት ላይ ለጠቅላላ ጉባኤ እንደሚሰበሰቡ እና አስፈላጊ ከሆነ ከሰዓት በኋላም የሚሰበሰቡ መሆኑን የቅድስት መንበር መግለጫ ክፍል ዳይሬክተር አቶ ማቴዎ ብሩኒ አስታውቀዋል።