ካርዲናል ፓሮሊን፥ በኢስታንቡል የሚደረግ ንግግር የሰላም መንገድ እንደሚከፍት ያላቸውን ተስፋ ገለጹ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
“የሁሉም ሰው ትኩረት ቱርክ ላይ ነው” ያሉት ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን፥ አዲሱ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሌዮ 14ኛ፥ የኒቂያ ጉባኤ 1,700ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ ለሚያደርጉት የመጀመሪያ ሐዋርያዊ ጉብኝት ኢስታንቡል መድረሻ እንደሆነች ተናግረዋል። የሩሲያው እና እና የዩክሬኑ ፕሬዚዳንቶች በአካል ተገናኝተው ሐሙስ ግንቦት 7/2017 ዓ. ም. በኢስታንቡል ቀጥተኛ የተኩስ ማቆም ድርድር እንደሚካሂዱ ታውቋል።
በዩክሬን የግሪክ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ድጋፍ በሮም በሚገኝ ጎርጎሮሳዊ ጳጳሳዊ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ “ለዩክሬይን እና ከዩክሬይን ወደሚጠበቅ ሥነ-መለኮታዊ ተስፋ” በሚል ርዕሥ በተዘጋጀ ስብሰባ ላይ የተገኙት የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ፒየትሮ ፓሮሊን፥ ከጋዜጠኞች ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተዋል። በአሜሪካ ሸምጋይነት የሚካሄደው ቀጥተኛ የሰላም ንግግር፥ ፕሬዝዳንት ዘሌንስኪን እና ፕሬዝደንት ፑቲንን ለመጀመሪያ ጊዜ በአካል እንደሚያገናኛቸው ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።
ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን ለተለያዩ ሚዲያዎች በሰጡት ምላሽ፥ ዘወትር ለሰላም ዕድል መኖሩን ተናግረው፥ ሁለቱ መሪዎች በመጨረሻ ቀጥታ ንግግር ማድረግ የሚችሉበት ዕድል መገኘቱ እንዳስደሰታቸው በመግለጽ፥ “አሉ የሚባሉ ችግሮች በኢስታንቡል ስብሰባ ተፈትተው እውነተኛ የሰላም ሂደት እንደሚጀመር ተስፋ እናደርጋለን” ብለዋል።
እንደ ቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ፒየትሮ ፓሮሊን ገለጻ መሠረት፥ የንግግራቸው ፍሬ ምን ሊሆን እንደሚችል መተንበይ አዳጋች ቢሆንም፥ ነገር ግን ተስፋው በኢስታንቡል የሚካሄደው ስብሰባ ጦርነቱን ለማቆም ጥሩ መነሻ እንደሆነ ገልጸዋል።
ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት የኪየቭን ጉብኝት ጊዜው ገና ነው
ፕሬዝደንት ዘሌንስኪን ሰኞ ግንቦት 4/2017 ዓ. ም. ማለዳ ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሌዮ 14ኛ ጋር በነበራቸው የስልክ ጥሪ ዩክሬይንን እንዲጎበኙ ግብዣ ቢያቀርቡላቸውም ቅዱስነታቸው በዩክሬን ሐዋርያዊ ጉብኝት የሚያደርጉበትን ወቅት ለማወቅ ጊዜው ገና እንደሆነ ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን ገልጸዋል
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሌዮ 14ኛ ያለፈው እሁድ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ከተሰበሰቡት ምዕመናን ጋር ሆነው ወደ እመቤታችን የሰማይ ንግሥት ጸሎት ባደረሱበት ወቅት ባሰሙት ንግግር፥ በጦርነት በተጎዱ አካባቢዎች ሰላም እንዲወርድ በማለት ጥሪ ማቅረባቸው ይታወሳል።
ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳስነት ሹመት ጀምሮ በተደጋጋሚ እንደተናገሩት ሁሉ፥ ጦርነቱ እንዲቆም ጥሪ ማቅረብን የሚቀጥሉ መሆኑን ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን አረጋግጠዋል። “ስለ ቅድስት መንበር የሽምግልና ዕድል መናገር ባይቻልም ነገር ግን ቢያንስ ስብሰባዎች የሚካሄድባቸው ቦታዎችን ለማመቻቸት ፈቃደኞች ነን” ብለው፥ “ቫቲካን በሌሎች ቀጣይ ሂደቶች ላይ ጣልቃ መግባት አትፈልግም” ሲሉ ተናግረዋል።
ህጻናትን ወደ አገራቸው የመመለሱ ዘዴ እየተመቻቸ ይገኛል
የቅድስት መንበር አቋም በጦርነት ውስጥ የሚገኙ ሁለቱን ወገኖች ለማቀራረብ መጣር እንደሆነ ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን ተናግረዋል።
በግዳጅ ወደ ሩሲያ የተወሰዱ አንዳንድ የዩክሬን ሕጻናት ውደ አገራቸው እንዲመለሱ ለማድረግ የተጀመረው የብጹዕ ካርዲናል ማቴዮ ዙፒ ተልዕኮ እና ዘዴ አሁንም በሂደት ላይ እንደሚገኝ ካርዲናል ፓሮሊን አረጋግጠዋል።
ይህም በዋናነት የሕጻናቱን ስሞችን በቅድስት መንበር እንደራሴ ጽሕፈት ቤት በኩል መለዋወጥ ከዚያም የአካባቢያቸውን ማረጋገጫ እና ምላሾችን እንደሚያካትት ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን ገልጸው፥ የሕጻናቱ ቁጥር አሁንም እጅግ አከራካሪ ቢሆንም ዋናው ጉዳይ ቀስ በቀስ ከቤተሰቦቻቸው እና ከሚወዷቸው ዘመዶቻቸው ጋር እንዲቀላቀሉ ማድረግ ነው” ስሉ ተናግረዋል።
በጋዛ ያለው ግጭት እንዲያበቃ ማድረግ
“መካከለኛው ምሥራቅን በተመለከተ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሌዮ 14ኛ እና ቅድስት መንበር ከዚህ በፊት ነፍስሔር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ባስቀመጡት መንገድ ይቀጥላሉ” ያሉት ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የጋዛን ግጭት ለማስቆም፣ የታጋቾችን መፈታት ለማሳካት እና ለጋዛ ነዋሪዎች ሰብዓዊ ዕርዳታ ለመስጠት የማያቋርጥ ጥሪዎችን ሲያቀርቡ እንደ ነበር አስታውሰዋል። በእነዚህ ጉዳዮች ላይ ከመራጭ ካርዲናሎች ጉባኤ በፊት በነበሩ ጠቅላላ ጉባኤዎች ላይ፥ “በመካከለኛው ምሥራቅ ያለው የክርስቲያኖች ቁጥር እያሽቆለቆለ ነው” ከሚለው ስጋት ጋር ጠንካራ ውይይቶች እንዲደረጉ ጥሪ መቅረቡን እና ለዚህ ከባድ ችግር ምላሽ ማግኘት እንደሚገባ ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን ተናግረዋል።
የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሌዮ 14ኛ የሰላም ጥረቶች
ከብጹዓን ካርዲናሎች ዝግ የምርጫ ጉባኤ በፊት እና በኋላ ስለተደረጉ ውይይቶች ከመናገር ይልቅ በምትኩ አዲስ በተመረጡት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ላይ በማትኮር እጅግ አዎንታዊ አስተያየቶችን እና ተቀብለው፥ “ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሌዮ 14ኛ ለምዕመናን ካደረጓቸው ከመጀመሪያዎቹ የሰላምታ ንግግሮች ጀምሮ ሰላምን የሚፈልጉ እና ሰላምን የሚገነቡ ናቸው” ሲሉ አስረድተዋል።
ወደ ኒቂያ የሚደረግ ሐዋርያዊ ጉብኝት
የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ፒየትሮ ፓሮሊን በመጨረሻም፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሌዮ 14ኛ በመጀመሪያ ስለሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት በማስመልከት ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ፥ ስለ ኒቂያ ጉባኤ መታሰቢያ በዓል እንደሚያስቡ እና ይህም ለካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን እና ለክርስቲያኖች አንድነት ጠቃሚ መሆኑን ተናግረው፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በኒቂያው ጉባኤ 1,700ኛ መታሰቢያ ላይ ለመገኘት በእርግጠኝነት አቅደው የነበረ በመሆኑ፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሌዮ 14ኛም ይህንኑ መንገድ እንደሚከተሉ ያላቸውን ግምት ገልጸዋል።