ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሌዮ 14ኛ፥ ለጠንካራ የእርስ በርስ ግንኙነት ጥሪ አቀረቡ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ብፁዕነታቸው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሌዮ 14ኛን ምርጫ በማስመልከት ባዘጋጀው ሥነ-ሥርዓት ላይ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር፥ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሌዮ 14ኛ መመረጥ ለካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ብቻ ሳይሆን የበለጠ ፍትሃዊነትን፣ አንድነትን እና ሰላማዊ ዓለምን ለሚሹት በሙሉ የመታደስ አጋጣሚ እንደሆነ አስረድተዋል።
የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብፁዕ ካርዲናል ፒየትሮ ፓሮሊን ለተባበሩት መንግሥታት አባል አገራት ተወካዮች ባደረጉት ንግግር፥ አዲስ የተመረጡት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሌዮ 14ኛ፥ በትሕትና የሚያዳምጥ፣ በርኅራኄ የሚሠራ እና ከምንም በላይ የጋራ ጥቅምን የሚያስቀድም ጠንካራ የእርስ በርስ ግንኙነት ወይም “ዲፕሎማሲ” ሊኖር እንደሚገባ ማሳሰባቸውን ገልጸዋል።
በተመሳሳይም ቅድስት መንበር በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሌዮ 14ኛ ሐዋርያዊ መሪነት ወቅት ከዓለም መንግሥታት ተወካዮች ጋር በመተባበር፥ ሰብዓዊ ክብርን ለማጎልበት፣ አቅመ ደካሞችን ለመንከባከብ እና መተማመን በጠፋበት ሁሉ አስተማማኝ የሆነ የእርስ በርስ ግንኝነትን ለማሳደግ እንደምትሠራ ብፁዕ ካርዲናል ፒየትሮ ፓሮሊን ቃል ገብተዋል።
በሰላም፣ በፍትህ እና በእውነት ላይ የተመሠረተ ዲፕሎማሲ
ብፁዕ ካርዲናል ፓሮሊን ወሳኝ ሚናቸው ዓለም አቀፍ ትብብርን መሠረት ማድረግ እንደሆነ አጽንዖት ሰጥተው፥ ይህም “በሰላም፣ በፍትህ እና በእውነት ላይ የተመሠረተ ዲፕሎማሲያዊ እንቅስቃሴ” የሚለውን የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሌዮ 14ኛ ራዕይን ለማሳካት ካላቸው ቁርጠኝነት ጋር የሚስማማ እንደሆነ አስረድተዋል።
ቅድስት መንበር በተመሳሳይም፥ ለእውነት እና ለፍትህ ቁርጠኛ ከመሆኗ በተጨማሪ ድሆችን እና የተቸገሩትን ለመከላከል፣ ሰላምን ለማስፈን እና ለሰው ልጆች ሁሉን አቀፍ ዕድገትን ለማምጣት የሚያስችል ሞራላዊ ድምጿን ማሰማት እንደምትቀጥል ተናግረዋል።
ብፁዕ ካርዲናል ፓሮሊን በመቀጠልም፥ ዲፕሎማቶች የሰላም ተልዕኮአቸውን በመወጣት ለቅዱስ አባታችን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሌዮ 14ኛ ጥሪ ምላሽ ሊሰጡ እንደሚችሉ ያላቸውን ተስፋ ገልጸው፥ በሥነ-ሥርዓቱ ላይ የተገኙትን በሙሉ፣ ቤተሰቦቻቸውን እና የሚወክሏቸውን አገራት ከባረኩ በኋላ በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሌዮ 14ኛ ተስፋ እና ራዕይ በመታገዝ በኅብረት ወደፊት እንዲጓዙ አደራ ብለዋል።