MAP

ካርዲናል ጉጄሮቲ፥ የምሥራቅ ቤተ ክርስቲያን ኩላዊነትን ማሳደግ እንዳለባት አሳሰቡ

በካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን የምሥራቅ አብያተ ክርስቲያናት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት የቀድሞው ተጠሪ ብጹዕ ካርዲናል ክላውዲዮ ጉጄሮቲ፥ በብርሃነ ትንሳኤው ላይ ባለን እምነት በተለይም በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ዕረፍት ላይ በማስተንተን ስብከታቸውን አሰምተዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ብጹዕ ካርዲናል ክላውዲዮ ጉጄሮቲ፥ በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ውስጥ ዓርብ ሚያዝያ 24/2017 ዓ. ም. የቀረበውን የሐዘን ቀናት ሰባተኛ መስዋዕተ ቅዳሴን በመሩበት ወቅት ባሰሙት ስብከት፥ “ሞት በሰው ልጅ ተፈጥሮ ላይ የመጣ ክስተት ሳይሆን ነገር ግን በእግዚአብሔር መንፈስ በኩል የመጣው ነው” ሲሉ አስገንዝበዋል።

በዚሁ ተመሳሳይ መንፈስ የሰው ልጅ ከፍጥረት ሁሉ ጋር ሆኖ አባባ በማለት ወደ እግዚአብሔር የሚጮህ መሆኑን አስረድተው፥ ይህ ቢሆንም ነገር ግን ፍጥረት እና የሰው ልጅ ለዚህ እውነት ዝቅተኛ ዋጋ የሚሰጡ ቢሆንም በሰው ልጅ እና በተፈጥሮ መካከል ያለው ትስስር ጽኑ መሆኑን ተናግረዋል።

ፍጥረት ለሰው ልጅ የጉዞው አጋሩ መሆኑን የጠቆሙት ብጹዕ ካርዲናል ክላውዲዮ ጉጄሮቲ፥ “ፍጥረት ከሰው ልጆች ጋር ዘወትር የሚተባበር እና በምላሹም አንድነታችንን በተጨባጭ የሚፈልግ ነው” በማለት፥ ይህ በመካከላቸው ያለው ግንኙነት ለቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እጅግ የተወደደ ጭብጥ እንደ ነበር አስረድተዋል።

በምሥራቅ እና በምዕራብ አብያተ ክርስቲያናት መካከል ያለው ወንድማማችነት

በካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን የምሥራቅ አብያተ ክርስቲያናት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት የቀድሞው ተጠሪ ብጹዕ ካርዲናል ክላውዲዮ ጉጄሮቲ፥ በምሥራቅ ቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊነት ላይ በማስተንተን ባቀረቡት ስብከታቸው፥ ምንም እንኳን በምሥራቅ እና በምዕራብ ክርስቲያኖች መካከል ልዩነታች ቢኖሩም በመስዋዕተ ቅዳሴ አማካይነት አንድ መሆናቸውን አስረድተው፥ ታሪካቸው በክርስትና መጀመሪያ ማለትም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተወለደበት ምድር መዓዛ ላይ የተመሠረተ መሆኑን አስታውሰዋል።

ዓርብ ሚያዝያ 24/2017 ዓ. ም. በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ውስጥ በቀረበው የመስዋዕተ ቅዳሴ ሥነ-ሥርዓት ላይ በርካታ የምሥራቅ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያናት ምዕመናን የተገኙ ሲሆን፥ ብፁዕ ካርዲናል ጉጄሮቲ፥ ምዕመናኑ በተሞክሮአቸው፣ በባህላቸው እና በመንፈሳዊነታቸው የቤተ ክርስቲያንን ኩላዊነት እንዲያሳድጉ የቀረበላቸውን ግብዣ መቀበላቸውን አድንቀዋል።

ብጹዕ ካርዲናል ጉጄሮቲ፥ “በታሪክ ውስጥ አንዳንድ ጊዜ እኛ ምዕራባውያን በምሥራቁ የሚገኙ ወንድሞቻችንን እና እህቶቻችንን መረዳት ተስኖን ነበር” ሲሉ ተናግረዋል።

የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ዕረፍት ምክንያት በማድረግ በታወጁት ዘጠኝ የሐዘን ቀናት መካከል በሰባተኛው ዕለት የቀረበውን የመስዋዕተ ቅዳሴ ሥርዓት በንባባት እና በዜማ የመሩት የምሥራቅ አብያተ ክርስቲያናት ምዕመናን እንደነበሩ ያስታወሱት ብጹዕ ካርዲናል ጉጄሮቲ፥ “የክርስቲያኖችን የአምልኮ ሥርዓት አገላለጽ እና በመካከላቸው ያለውን ልዩነት እንድንወድ ያስተማሩን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ ከእርሳቸው ጋር ለእርሳቸው በተደረገው ጸሎት ላይ አንድ መሆናችንን በማየታቸው ደስታኛ ናቸው” ሲሉ ገልጸዋል።

ብጹዕ ካርዲናል ጉጄሮቲ፥ በምሥራቅ አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ የሚገኙ ወንድሞች እና እህቶች በእምነታቸው እንዲጸኑ መርዳት እንደሚገባ አሳስበው፥ “በተለይ በአሁኑ ጊዜ ብዙ ምዕመናን ጥንታዊት እና ቅድስት ከነበረች አገራቸው ለመሰደድ መገደዳቸውን አስታውሰዋል።

በካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን የምሥራቅ አብያተ ክርስቲያናት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት የቀድሞው ተጠሪ ብጹዕ ካርዲናል ክላውዲዮ ጉጄሮቲ በስብከታቸው ማጠቃለያ፥ ብጹዓን ካርዲናሎች ከመጪው የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ምርጫ በፊት፥ የምሥራቅ ቤተ ክርስቲያን አባት እና አዲስ የነገረ መለኮት ምሑር የሆነውን ቅዱስ ሲሞንን በጸሎታቸው እንዲያስታውሷቸው አደራ ብለዋል።

ብጹዕ ካርዲናል ክላውዲዮ ጉጄሮቲ፥ “እውነተኛ ብርሃን ሆይ! የዘላለም ሕይወት ሆይ! የተደበቀ ምሥጢር ሆይ! ሥፍር ቁጥር የሌለው ሃብት ሆይ! በቃል ሊገለጽ የማይችል እውነት ሆይ! በአዕምሮ ሊታሰብ የማይችል እና ወሰን የሌለው ደስታ ሆይ! ጨለማ የማይታይበት ብርሃን ሆይ! ለሚድኑ ሁሉ የማይጠፋ ተስፋ ሆይ ወደ እኛ ናልን!” በማለት ጸሎታቸውን አቅርበዋል።

03 May 2025, 16:48