የካርዲናሎች የመጀመሪያ ቀን ዝግ ጉባኤ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳትን ሳይመርጥ ተጠናቀቀ
የካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን 267ኛ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ለመምረጥ የመጀመሪያ ቀን ዝግ ጉባኤ ወይም “ኮንክላቭ” ያካሄዱት መራጭ ካርዲናሎች ጉባኤያቸውን ያለ ምርጫ አጠናቅቀዋል።
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ረቡዕ ሚያዝያ 29/2017 ዓ. ም. ከምሽት ሦስት ሰዓት ላይ በቫቲካን የሲስቲን ጸሎት ቤት በኩል የታየው ጥቁር ጭስ፥ መራጭ ካርዲናሎች በዝግ ጉባኤያቸው የመጀመሪያ ድምጽ ቢሰጡም ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳትን ሳይመርጡ ማጠናቀቃቸውን አሳይቷል።
በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ የተሰብሰቡት በ 45,000 የሚገመቱ ሰዎች እስከ አንድ ሰዓት ድረስ ይታወቃል የተባለውን የምርጫ ውጤት እስከ ምሽቱ ሦስት ሰዓት ድረስ ለመጠበቅ ተገደዋል።
በአደባባዩ ከነበሩት መካከል ታንዛኒያዊው ካቶሊክ ዲያቆን ኒኮላስ ንኮሮንኮ ለቫቲካን የዜና አገልግሎት እንደተናገረው፥ “ከልዩ ልዩ አገራት ወደ ቫቲካን የመጣን ካቶሊካዊ ምዕመናን ሚና ከሌሎች ክርስቲያን ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን ጋር ሆነን ጠቅላላ ሂደቱን መንፈስ ቅዱስ እንዲመራው መጸለይ ነው” ብሏል።
ዲያቆን ንኮሮንኮ አክሎም፥ “የሚመረጡት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት፥ ከአፍሪካ፣ ከእስያ ወይም ከአሜሪካ ይሁን ነገር ግን ቤተ ክርስቲያንን በቅድስና የሚያስተዳድሩ እና የሚመሩ እንዲሆኑ እንፈልጋለን” ሲል አሳስቧል።
08 May 2025, 09:09