በአውሮፓ ህብረት የቅድስት መንበር ሃዋሪያዊ ተወካይ ‘ሰላም እና እምነትን ለቀጣይ ትውልድ ማስተላለፍ ያስፈልጋል አሉ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
በአውሮፓ ኅብረት የቅድስት መንበር ሐዋርያዊ ተወካይ የሆኑት ሊቀ ጳጳሱ በአውሮፓ ውስጥ የሚገኙ ቤተሰቦች እምነትን ወደ ቀጣዩ ትውልድ እንዲያስተላልፉ እና ወጣቶች ከእግዚአብሔር ጋር ያለውን ግንኙነት እንዲጠሙ ማበረታታት በጣም አስፈላጊ እንደሆነ ገልጸው፥ በተመሳሳይ መልኩ ዓለማችን በአውሮፓ ምድር እንኳን ሳይቀር በተለያዩ ጦርነቶች ምክንያት ሰላም ማጣቷ በጣም እንደሚያሳስባቸው በተደጋጋሚ ገልጸዋል።
ሊቀ ጳጳስ በርናርዲቶ አውዛ ከቫቲካን ዜና ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፣ በአውሮፓ ኅብረት የጳጳሳት ጉባኤዎች ኮሚሽን (COMCE) አመራር አባላት አርብ ጠዋት ከርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ጋር ተገናኝተው በተወያዩበት ወቅት ይሄንን ጉዳይ ማንሳታቸውን ጠቅሰዋል።
ሊቀ ጳጳሱ ግንቦት 15 ቀን 2017 ዓ.ም. ከቫቲካን መገናኛ ብዙኃን ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ላይ፥ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ከአውሮፓ ኅብረት የጳጳሳት ጉባኤዎች ኮሚሽን አባላት ጋር ያደረጉትን 'ጠንካራ' ውይይት በማስታወስ፥ ብጹእነታቸው በውይይቱ ወቅት ሁሉንም በጥሞና ያዳምጡ እንደነበር ገልጸዋል።
ሊቀ ጳጳሱ ከኮሚሽኑ አመራሮች ጋር በመሆን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱን ባነጋገሩበት ወቅት በዩክሬን እየተካሄደ ስላለው ጦርነት ያላቸውን ታላቅ ስጋት ገልጸው፥ ፍትሃዊ የሆነ ሰላም አስፈላጊነት ላይ ደጋግመው መናገራቸውን አስታውሰዋል።
ከዚህም በላይ እጅግ በጣም ችግረኛ እና አቅመ ደካሞችን ለመደገፍ ይውል የነበረው ገንዘብ በጦርነቱ ምክንያት ወታደራዊ ወጪ ላይ በመዋሉ፥ የመከላከያ እና የደህንነት ሥርዓቶችን ለማጠናከር ሲባል ተጨማሪ ገንዘብ መመደቡ በስቃይ ወይም በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ለሚገኙ ሰዎች የሚደረገውን ዕርዳታ ሊጎዳ እንደሚችል እና ይህ ጉዳይ ቅዱስ አባታችንን በጣም እንዳሳሰባቸው ለመረዳት ችለናል ብለዋል።
በዩክሬን ፍትሃዊ እና ዘላቂ ሰላም ያስፈልጋል
ሊቀ ጳጳስ በርናርዲቶ አውዛ በአውሮፓ ህብረት የቅድስት መንበር ሃዋሪያዊ ተወካይ ሆነው የተሾሙት እና አሁን እየተወጡት የሚገኘውን ሚና የጀመሩት በያዝነው ዓመት መጋቢት ወር መጨረሻ ላይ ሲሆን፥ ይህን አስመልክተው እንደተናገሩት ከአንድ ቀን በፊት ብራስልስ እንደደረሱ፥ ነገር ግን እስከአሁን ወደ ቅድስት መንበር ሃዋሪያዊ ጽህፈት ቤቱ እንዳልሄዱ፥ ምክንያቱም አየር ማረፊያ እንደደረሱ ከርዕሰ ሊቃነ ጳጳሱ ጋር ለነበራቸው ውይይት ላይ ለመገኘት ቀጥታ ወደ ሮም በረራ እንዳደረጉ ገልጸው፥ “የአጋጣሚ ነገር ሆኖ አዲሱን ተልእኮዬን ከአውሮፓ ህብረት እና ከህብረተሰቡ ጋር ዛሬ ጀምሬያለሁ” ብለዋል።
ሊቀ ጳጳስ አውዛ በአውሮፓ ኅብረት ውስጥ ሐዋርያዊ አገልጋይ ሆነው ከመሾማቸው በፊት በስፔን የቅድስት መንበር ተወካይ እንዲሁም የአንዶራ ራስ ገዝ አስተዳደር ሆነው እንዳገለገሉ የተገለጸ ሲሆን፥ ከዚህም ባለፈ በኒውዮርክ በተባበሩት መንግስታት የቅድስት መንበር ቋሚ ታዛቢ በመሆን ለረጅም ጊዜ አገልግለዋል።
ስለዚህም ሃዋሪያዊ ተወካዩ ልዩ በሆነ መንገድ ሰላምን ለማስፈን እና በተለይም የዩክሬን ጦርነትን ለማስቆም ጥረት ማድረግ እንደሚገባ በውይይቱ ላይ ግንባር ቀደም ሃሳቦች ሆነው እንደተነሱ አስታውሰዋል።
በዓለም ላይ እየተካሄዱ ባሉ በርካታ ጦርነቶች እና “እጅግ ብዙ ግጭቶች” ባሉባቸው ቦታዎች ለመደራደር ወይም ስምምነትን ለማስፈን ፈታኝ ሊሆን እንደሚችል የጠቆሙት ሃዋሪያዊ ተወካዩ፥ “ቅዱስ አባታችን በግልጽ እንደተናገሩት ቅድስት መንበር የበኩሏን አስተዋጽኦ ማድረግ ትችላለች” ብለዋል።
ወጣቱ ለእምነት ያለው ከፍተኛ ጥማት
ሊቀ ጳጳስ አውዛ እንደገለፁት በቤተሰብ በኩል እምነትን ወደ ቀጣይ ትውልድ የማስተላለፍ አስፈላጊነትን እና ስደተኞችን በአግባቡ እና በአክብሮት መያዝን ጨምሮ ሌሎች ጭብጦችም በውይይቱ ወቅት ትኩረት ተሰጥቶባቸው እንደነበር ገልጸው፥ በተለይም በወጣቶች መካከል ስለሚታየው ስለ ቤተ ክርስቲያን እና እምነት ያላቸው ከፍተኛ ፍላጎትን አንስተው መወያየታቸውን ከገለጹ በኋላ፥ “በብዙ አገሮች ውስጥ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያንን የበለጠ ለማወቅ አዲስ ፍላጎት በከፍተኛ ደረጃ ይታያል” ብለዋል።
“የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስን ኅልፈት እና የአዲስ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት መመረጥም ለዚህ ፍላጎት እንደገና መነቃቃት አስተዋጽኦ አድርጓል” ያሉት ሊቀ ጳጳሱ፥ ስለ ርዕሰ ሊቃነ ጵጵስና ምንም ዕውቀቱ ያልነበራቸው እንኳን ሳይቀር ነገሩን ለማወቅ እንደተነሳሱ እና ክስተቱ የሁሉም ሰው ቤት፣ የሁሉም ሰው ቴሌቪዥን፣ የሁሉም ሰው የኢንተርኔት ግንኙነት ውስጥ መግባቱን ተናግረዋል።
ትውልደ ፊሊፒናዊው ሊቀ ጳጳስ አክለውም ቤተክርስቲያኒቷ “አዲስ መነቃቃትን” እንደምትሰጥ ትልቅ ተስፋ መኖሩን በቃለ ምልልሱ ወቅት ጠቁመው፥ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ በውይይታችን ወቅት፥ ምንም እንኳን የተለያዩ ትርክቶች በተቃራኒው ለመጠቆም ቢሞክሩም፥ ወጣቶች እና ሕፃናት እምነትን ለማወቅ ያላቸውን ፍላጎት በድጋሚ ማረጋገጣቸውን አስታውሰዋል።
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ “ሰዎች፣ ማኅበራት እና መንግሥታት ‘ከትናንሽ ልጆች ጋር መነጋገር አያስፈልጋችሁም ወይም አያስፈልገንም’ ይላሉ፥ ምክንያቱንም ሲገልጹ ልጆቹ ወይም ወጣቶቹ ስለ ሃይማኖት እና ስለ እግዚአብሔር ፍላጎት የላቸውም ይላሉ፥ ይህ ግን ስህተት ነው፥ በህፃናት እና ወጣቶች ዘንድ ከፍተኛ እግዚያብሄርን መሻት አለ” ማለታቸውን ጠቅሰዋል።
በክርስቶስ እና በቤተክርስቲያን ላይ ያለው አዲስ ፍላጎት
ሊቀ ጳጳስ አውዛ የአውሮፓ ኅብረት የጳጳሳት ጉባኤዎች ኮሚሽን ምክትል ፕሬዚዳንት የሆኑት የዲጆን ሊቀ ጳጳስ ብጹእ አቡነ አንትዋን ሄሩርድ ይህ በጣም እውነት መሆኑን ማረጋገጣቸውን በማስታወስ፥ ይህ በአንዳንድ አከባቢዎች በትምህርተ ክርስቲያን ክፍል ውስጥ የሚሳተፉትን እና ለሚስጥረ ጥምቀት የሚመጡትን ህፃናት ቁጥር አይቶ መፍረድ እንደሚቻል ጠቅሰው፥ “በወጣቶች ውስጥ ብዙ የሚታደስ ሃይል ያለ ይመስላል” ማለታቸውን ገልጸዋል።
"አሁንም ተስፋ አለ፥ ከብዙ ዓመታት በኋላ ወደ እምነት የመመለሻ ጊዜ እንዳለ ታያላችሁ፣ ምናልባት፣ 'በፍጹም ይህን አልሰማንም፣ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ አልሰማንም' የሚሉ ድምፆች ሊኖሩ ይችላሉ፥ ስለዚህ እኛ ማድረግ የምንችለው ብዙ ነገር ያለ ይመስለኛል” በማለት ሃሳባቸውን አካፍለዋል።
እምነትን ከአንድ ትውልድ ወደ ሌላው የሚያስተላልፉ ቤተሰቦች ያስፈልጋሉ
ሊቀ ጳጳሱ እምነትን ከትውልድ ወደ ትውልድ ማስተላለፍ ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ በድጋሚ አረጋግጠው፥ “የ ‘አዲስ የወንጌል ስርጭት’ ጥያቄ በመሠረቱ እምነትን ከአንድ ትውልድ ወደ ቀጣዩ ትውልድ የማስተላለፍ ጥያቄ ነው” ካሉ በኋላ፥ ምንም ዓይነት የማስተላለፊያ ቻናል ባለመኖሩ ይህ በእውነቱ መዋቅራዊ ችግር መሆኑን ገልጸው፥ ይህም በመሆኑ ወላጆች ከእንግዲህ ስለ እምነት አይናገሩም፣ ወደ ቤተ ክርስቲያንም አይሄዱም ማለት ነው” ብለዋል።
በእነዚህ ምክንያቶች ሕፃናት ብዙ ጊዜ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ እንደማይታዩ በማስታወስ፥ “ህፃናት ለራሳቸው መምረጥ የሚችሉ አዋቂዎች እስኪሆኑ ድረስ ወደ ቤተክርስቲያን ማምጣት ተገቢ አይደለም” በሚል እሳቤ፥ ሕፃናት እንዳይጠመቁ ወይም ስለ ሃይማኖት እንዳይማሩ የሚከለክል እንቅስቃሴ ተፈጥሯል በማለት በቁጭት ገልጸዋል።
በአውሮፓ ህብረት የቅድስት መንበረ ተወካይ በመጨረሻም “እምነትን ከትውልድ ወደ ትውልድ በማስተላለፍ ረገድ የቤተሰብ ሚና ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰው፣ እንዲያውም ምንም በማያጠያይቅ ሁኔታ በዚህ ጉዳይ ከሰበካዎች በበለጠ የቤተሰብ ሚና ከፍተኛ ነው” በማለት አረጋግጠዋል።