MAP

ሚያዝያ 28 ቀን 2017 ዓ.ም. የተካሄደው የመጨረሻው እና 12ኛው የብጹአን ካርዲናሎች አጠቃላይ ጉባኤ  ሚያዝያ 28 ቀን 2017 ዓ.ም. የተካሄደው የመጨረሻው እና 12ኛው የብጹአን ካርዲናሎች አጠቃላይ ጉባኤ   (@Vatican Media)

12ኛው ጠቅላላ ጉባኤ አዲስ የሚመረጡት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት አስፈላጊ በሆኑ ባህሪያት ላይ ያተኮረ ነበር ተባለ

የዝግ ጉባኤ ወይም ኮንክሌቭ ከመጀመሩ በፊት አንድ ቀን ቀደም ብሎ አስራ ሁለተኛው እና የመጨረሻው የብጹአን ካርዲናሎች አጠቃላይ ጉባኤ፥ አዲስ የሚመረጡት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ጠባቂ እረኛ፣ አገናኝ ድልድይ እና የተሃድሶ አራማጅ መሆንን ጨምሮ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ሊኖራቸው የሚገባቸውን አስፈላጊ በሆኑ የተለያዩ ባህሪያት ላይ አተኩሮ መወያየቱ ተገልጿል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

አዲስ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳትን ለመምረጥ የሚከናወነው የብጹአን ካርዲናሎች ዝግ ጉባኤ ከመጀመሩ አንድ ቀን ቀደም ብሎ ማክሰኞ፣ ሚያዝያ 28 ቀን 2017 ዓ.ም. የተካሄደው የመጨረሻው እና 12ኛው የብጹአን ካርዲናሎች አጠቃላይ ጉባኤ ላይ 130 መራጭ ካርዲናሎችን ጨምሮ 173 ብፁዓን ካርዲናሎች መካፈላቸውን የቅድስት መንበር የጋዜጣዊ መግለጫ ጽህፈት ቤት ዳይሬክተር ማትዮ ብሩኒ ከጋዜጠኞች ጋር ባደረጉት ቆይታ አስረድተዋል።

እንደተለመደው ጉባኤው በሮም ሰዓት አቆጣጠር ከጥዋቱ 3 ሰዓት ላይ በጸሎት መጀመሩን ጠቁመው፥ በጉባኤው ወቅት ከተነሱት በርካታ ርዕሰ ጉዳዮችን መካከል 26 የሚሆኑ ንዑስ ሃሳቦች ላይ በስፋት መወያየታቸውን ገልጸዋል።

ከተነሱት ሃሳቦች መካከል ለአብነት ያክል ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ቤተክርስቲያኒቱ ውስጥ የሚፈጸሙ በደሎችን፣ ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮችን፣ የሮማውያን ኩሪያን፣ ሲኖዶሳዊነትን፣ የሰላም ግንባታ ሥራዎችን እና ለፍጥረታት እንክብካቤ ማድረግን አስመልክተው ያደረጓቸው የማሻሻያ ህጎች ወደፊት ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው ውይይት ያደረጉ ሲሆን፥ የብጹአን ካርዲናሎቹ ጉባኤ ዋና ጭብጥ የነበረው አዲስ የሚመረጡት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ጠባቂ እረኛ፣ አገናኝ ድልድይ፣ የሳምራዊት ቤተ ክርስቲያን ነጸብራቅ፣ የሰብዓዊነት ተምሳሌት እና የተሃድሶ አራማጅ መሆንን ጨምሮ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ሊኖራቸው የሚገባቸውን አስፈላጊ በሆኑ የተለያዩ ባህሪያት ላይ አተኩሮ መወያየቱ የተገለጸ ሲሆን፥ ከዚህም ባለፈ በጦርነት፣ በዓመፅ እና ጥልቅ የጽንፈኝነት ተግባራት በሰፈነበት ወቅት፥ ምሕረትን፣ ሲኖዶሳዊነትን እና ተስፋን የሚሰጡ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ያስፈልጋሉ በማለት መክረዋል።

ስለ ቀኖና ሕግ እና ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ስለሚኖራቸው ስልጣን፣ ቤተ ክርስቲያኒቷ ውስጥ ስላለው ክፍፍል እና ብጹአን ካርዲናሎቹ በቤተክርስቲያን ውስጥ ስላላቸው ሚና፣ አንድ ላይ ሊታሰብበት ስለሚገባው ስለ ክርስቶስ ንጉሥ ክብረ በዓል እና በቅርቡ ስለሚከበረው ስለ የዓለም የድሆች ቀን፣ እንዲሁም ‘ኮንሲስቶሪ’ ተብሎ በሚታወቀው የብጹአን ካርዲናሎች ምክር ቤት ጉባኤ ወቅት የብጹአን ካርዲናሎች ህብረት ስብሰባዎች አስፈላጊነት ላይ ውይይት ማድረጋቸው ተነግሯል።

ከዚህም በተጨማሪ ከተነሱት ርዕሰ ጉዳዮች ውስጥ ክርስቲያናዊ ህንጸት እና ምስረታ በሚስዮናዊነት፣ በግጭት አካባቢዎች እና የእምነት ነፃነት በተገደበባቸው አካባቢዎች የእምነት ሰማዕታትን ምስክርነት ስለማስታወስ እና አስቸኳይ የአየር ንብረት ለውጥ ጉዳዮች የተነሱ ሲሆን፥ የትንሳኤ በዓል ቀንን፣ የኒቂያ ጉባኤ እና የክርስቲያናዊ ህብረት ውይይት ርዕሰ ጉዳይም ተጠቅሰዋል።

አቶ ብሩኒ በተጨማሪም እንዳስታወቁት ‘የአሳ አስጋሪው ቀለበት’ ተብሎ የሚታወቀው እና ርዕሰ ሊቃነ ጳጳስት በስልጣን ዘመናቸው እንደ ማህተም የሚጠቀሙበት ቀለበት ባዶ መደረጉን፣ እንዲሁም በተለያዩ ግጭቶች ውስጥ ለሚሳተፉ ወገኖች በተላለፈ ጥሪ ዘላቂ የተኩስ አቁም እና ድርድር እንዲደረጉ ብሎም ፍትሃዊ እና ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ጥሪ አቅርበዋል።

ጉባኤው ከቀኑ 6፡30 ላይ የተጠናቀቀ ሲሆን፥ አቶ ብሩኒ ከዚህ በኋላ ሌላ ተጨማሪ ጠቅላላ ጉባኤ እንደሌለ አረጋግጠዋል።

ዝግ ጉባኤውን አስመልክቶ የወጣ የጊዜ ሰሌዳ
የቅድስት መንበር የጋዜጣዊ መግለጫ ጽህፈት ቤት ዳይሬክተሩ የብጹአን ካርዲናሎቹ ዝግ ጉባኤ የጊዜ ሰሌዳን በተመለከተ ተጨባጭ ዝርዝሮችን ያብራሩ ሲሆን፥ ረቡዕ ጥዋት በመስዋዕተ ቅዳሴ የሚጀመረው ዝግ ጉባኤው በዕለቱ ምንም ውጤት ካልተገኘ፥ ሃሙስ ዕለት ይቀጥልና በሮም ሰዓት አቆጣጠር ከጥዋቱ 1፡45 ላይ ብፁአን ካርዲናሎቹ ከቅድስት ማርታ መኖሪያ ቤት ወደ ሐዋርያዊት ቤተ መንግሥት በማቅናት፥ 2፡15 ላይ በቅዱስ ጳውሎስ ቤተ ክርስቲያን መስዋዕተ ቅዳሴ እንደሚያሳርጉ፥ በመቀጠልም 3፡15 ላይ በሲስቲን ጸሎት ቤት ውስጥ የማለዳ ፀሎት ይደረጋል ብለዋል። በጥዋቱ ዝግ ጉባኤው ወቅት ውጤት ከተገኘ ከረፋዱ 4፡30 ላይ ነጭ ጭስ እንደሚለቀቅ፥ ካልሆነ ግን ከሰዓት በኋላ ከ 9፡30 ጀምሮ የሚደረገው ዝግ ጉባኤ ውጤት እንደሚጠበቅ አስረድተዋል።

አቶ ብሩኒ በመጨረሻም የድምጽ አሰጣጥ ሂደቱ ከተጠናቀቀ በኋላ በሲስቲን ጸሎት ቤት ውስጥ የምሽት ጸሎት ይደረግና ከምሽቱ 1፡30 ላይ መራጭ ብጹአን ካርዲናሎቹ ወደሚያርፉበት የቅድስት ማርታ መኖሪያ ህንፃ እንደሚመለሱ አብራርተዋል።
 

08 May 2025, 13:50