የሕሙማን ኢዮቤልዩ በዓል፥ በቅዱስ ዓመት ዝግጅቶች ዝርዝር 7 ኛ ደረጃን መያዙ ተገለጸ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
መጋቢት 27 እና 28/2017 ዓ. ም. በሮም የሚካሄደው ሰባተኛው የኢዮቤልዩ በዓል ዝግጅት ታካሚዎችን፣ ዶክተሮችን፣ ነርሶችን፣ ፋርማሲስቶችን፣ የጤና ባለሙያዎችን እና ቴክኒሻኖችን ጨምሮ 20,000 የሚሆኑ ከ90 በላይ ሀገራት የሚመጡ ሰዎችን እንደሚያሳትፍ ተገልጿል።
ወደ ቅዱስ በር የሚደረግ ንግደት
ቅዳሜ መጋቢት 27/2017 ዓ. ም. የሚጀምረው የሁለት ቀናት ዝግጅት የቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ቅዱስ በር ለመሻገር ዕድል እንደሚሰጥ ታውቋል። “ከከተማ ጋር የሚደረግ ውይይት” በሚል ርዕሥ በማኅራት፣ በድርጅቶች እና በልዩ ልዩ እንቅስቃሴዎች የተዘጋጁ ባህላዊ፣ መንፈሳዊ እና ሥነ-ጥበባዊ ዝግጅቶች በሮም ከተማ አደባባዮች ላይ ዛሬ ከሰዓት በኋላ ቀርበዋል።
የተስፋ፣ የመስጠት እና የመንከባከብ ዝግጅቶች
“የመስጠት እና የአንድነት እሴት” በሚል ርዕስ በጣሊያን የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ቅዳሜ ከቀትር በኋላ በፒያሳ ዲ ስፓኛ በተዘጋጀው በዓል ላይ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ሪኖ ፊዚኬላ፣ የጣሊያን የጤና ጥበቃ ሚኒስትር፣ የሮም ከተማ ከንቲባ እና ሌሎች የሲቪል ማኅበራት ተወካዮች ተገኝተው ንግግር አድርገዋል።
“ተስፋ” በሚል ርዕሥ በዕለቱ የቀረቡ የተለያዩ የኢዮቤልዩ በዓል ዝግጅቶችን በጋራ ያስተባበሩት በሮም የሚገኙ የቅዱስ መስቀል ጳጳሳዊ ዩኒቨርሲቲ እና ካምፓስ ባዮ-ሜዲካል ዩኒቨርሲቲዎች ሲሆኑ፥ ፈውስ ለሌለው ሕመም የሚሰጥ እንክብካቤ በሚል ርዕሥ ስብሰባ መካሄዱ ታውቋል።
የአሜሪካ የልብ ሕሙማን ማኅበር ፈውስ ለሌለው ሕመም የሚሰጠውን እንክብካቤ በማስመልከት በእንግሊዝኛ፣ በስፓኒሽ፣ በፈረንሳይኛ፣ በፖላንድ እና በጀርመንኛ ቋንቋዎች የቴክኒክ ትምህርቶችን በመስጠት ተግባራዊ ድጋፍ ማድረጉ ታውቋል። “ፍራትረስ” የተባለ ማኅበርም በበኩሉ ከማዕከላዊ አውሮፓ ኢኒሼቲቭ ብሔራዊ የጤና ጥበቃ ሐዋርያዊ አገልግሎት ቢሮ ጋር በመተባበር በፒያሳ ሳን ጆቫኒ በቀረበው ዝግጅት የደም ልገሳን በማስመልከት ግንዛቤን አስጨብጧል።
ከሕክምና እስከ ቅድስና ጉዳይ
በቅድስት ሞኒካ ቤተ ክርስቲያን ቅጥር ግቢ በቀረበው ዝግጅት ባልተለመደ ሕመም ከዚህ ዓለም በሞት በተለየች የሕክምና ተማሪ በነበረች በብጽዕት ቤነዴታ ቢያንኪ ፖሮ ላይ የተደረገ ስብሰባ የተካሄደ ሲሆን፥ በስብሰባው ላይ እህቷ ኢማኑኤላ እና የሕይወት ታሪኳ ጸሐፊ አባ አንድሪያ ቬና ንግግር አድርገዋል።
በዝግጅቱ ላይ የቅዱስ ቁርባን ስግደት ሥነ-ሥርዓት ከመፈጸሙ በተጨማሪ ሕሙማንን በመንከባከብ የሚታወቁ የልዩ ልዩ ገዳማት ተወካዮች የትህርተ ክርስቶስ አስተምህሮዎችን አቅርበው፥ በከተማው ውስጥ በሚገኙ ልዩ ልዩ ቤተ ክርስቲያናት ውስጥ የጸሎት ሥነ-ሥርዓት ተካሂዷል።
በቅዱስ ዓመት በተዘጋጀ የሕሙማን ኢዮቤልዩ ሁለተኛ እና የመጨረሻ ቀን ላይ ሕሙማንን እና የዓለም ጤና አጠባበቅን በማስመልከት በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ እሑድ መጋቢት 28/2017 ዓ. ም. የሚቀርበውን የመስዋዕተ ቅዳሴ ሥነ-ሥርዓተ የሚመሩት በቅድስት መንበር የስብከተ ወንጌል አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ሃላፊ ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ሪኖ ፊዚኬላ እንደሚሆኑ ታውቋል።