ር. ሊ. ጳ. ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ የወንጌልን ሕይወት በተጨባጭ የኖሩ ናቸው ተባለ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ከሃያ ዓመታት በፊት የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ የቅርብ አገልጋይ የነበሩ እና ዛሬ በሐዋርያዊ ጽሕፈት ቤት የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት የበጎ አድራጎት ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት አስተባባሪ የሆኑት ብጹዕ ካርዲናል ኮንራድ፥ በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ሕይወት ላይ በማሰላሰል ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል።
የብጹዕ ካርዲናል ኮንራድ ምስክርነት
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ መስዋዕተ ቅዳሴን ለመምራት ከመቅረባቸው በፊት ከእግዚአብሔር ጋር በጸሎት ይነጋገሩ እንደ ነበር፣ በመንበረ ታቦት ላይ እግዚአብሔርን በመወከል ለምዕመናኑ የሚያሰሙት ቃለ-ምዕዳን ልብን የሚነካ እና ሕይወትን የሚቀይር እንደ ነበር ተናግረው፥ “የትኛውም ክብረ በዓል ከመጀመሩ በፊት በቤተ መቅደስ ውስጥ በጸሎት መንፈስ ከእግዚአብሔር ጋር ይገናኙ ነበር” ብለዋል። “ይህ የቅድስናቸው ምልክት መሆኑን በወቅቱ አላወቅሁም ነበር” ብለው፥ ላለፉት ሰባት ዓመታት፥ በሳምንት ብዙ ጊዜ ቅዱስነታቸውን በዚህ መልክ ማየታቸውን አስታውሰዋል።
የቤተሰብነት ስሜት ይሰማን ነበር
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ባረፉበት በመጋቢት 24 ምሽት ቫቲካን ውስጥ ከነበሩት መካከል አንዱ የሆኑት ካርዲናል ክራየስኪ፥ ከእኩለ ሌሊት በኋላ ዓለም ባለበት የቆመ ይመስል እንደ ነበር እና በርካታ ቁጥር ያለው ሕዝብ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለጸሎት ተንበርክኮ እንደ ነበር አስታውሰዋል።
በቫቲካን ዙሪያ ያሉት መንገዶች በሰዎች መጨናነቃቸውን፣ በአካባቢው ፍጹም ጸጥታ መስፈኑን፣ ሱቆች እና ሬስቶራንቶች ተዘግተው በአካባቢው የነበረው ከፍተኛ ውጥረት በድንገት ተለውጦ ሁሉም ሰው በጸሎት መንፈስ ማስተንተን የጀመረበት ጊዜ እንደ ነበር በማስታወስ፥ ከሌሎች ባልደረቦቻቸው ጋር ሆነው፥ “እርሳቸው ቅዱስ ሲሆኑ እኛም እንደ እርሳቸው ለምን ቅዱስ አልሆንንም? የእርሳቸው የቅርብ አገልጋዮች ሆነን ሳለ ለምን ቅዱሳን አልሆንንም” በማለት መጠየቃቸውን አስታውሰዋል።
በመገናኛ ብዙኃን አማካይነት ሁሉም ሰው ክስተቱን በቅርብ መከታተል የሚችልበት ወቅት እንደ ነበረ ተናግረው፥ “ያ ጊዜ ከየትኛውም ጊዜ በተለየ ሁኔታ መላው ዓለም ለአፍታ ቆም ያለ ይመስል ነበር” ሲሉ ተናግረዋል።
ወንጌልን በተግባር መኖር
ብጹዕ ካርዲናል ኮንራድ ከቫቲካን የዜና አገልግሎት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፥ ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ጋር አብረው የሠሩበትን ጊዜ በማስታወስ እንደተናገሩት፥ ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ወንጌልን በተግባር ይኖሩ እንደ ነበር አስታውሰው፣ ሥራቸው፣ ምግባራቸው፣ በዓለም እና በዙሪያው ያሉ ችግሮችን ለመፍታት የወሰዱት መንገድ በአራቱ ወንጌላት ላይ ብቻ የተመሠረተ እንደ ነበር አስረድተዋል።
በአንድ ሰው የወንጌል ሕይወት ላይ አስተያየት መስጠት እና ገለጻ ማድረግ አስፈላጊ እንዳልሆነ ገልጸው፥ “አስተያየት መስጠት ወንጌልን ማዛባት ይሆናል” ብለዋል። በማከልም አንድ ሰው ራሱን ለእግዚአብሔር እና ለሰዎች አገልግሎት ሙሉ በሙሉ በመስጠት በትሕትና መኖር ሲጀምር ከፍ እንደሚል ተናግረው፥ “ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊም ቅዱስ የሆኑት ለዚህም ነው” ሲሉ አስረድተዋል።
ዛሬ ለእኛ አስፈላጊው መልዕክት የቱ መሆን እንዳለበት የተጠየቁት ብጹዕ ካርዲናል ኮንራድ፥ ወንጌልን በሙላት መኖር እንደሆነ አስረድተው፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ሕይወት በወንጌል የታገዝ እንደሆነ እና የዓለምን ችግሮች ወንጌልን መሠረት በማድረግ ለመፍታት ችለዋል ሲሉ አጽንዖት ሰጥተው፥ “በእግዚአብሔር እውነት መኖር ከቀጠልን ይህ ይፈጸማል” በማለት አስገንዝበዋል ።
የአንድነት ምልክት
በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ መቃብር ዙሪያ የቀረቡ የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎቶች አጀማመርን ያስታወሱት ብጹዕ ካርዲናል ኮንራድ፥ በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ መካነ መቃብር አጠገብ የቀረበውን የመጀመሪያውን መስዋዕተ ቅዳሴ፥ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በጸሎተ ሐሙስ ዕለት ካዘጋጃቸው የቅዱስ ቁርባን እና የክህነት ምስጢራት ጋር የተዛመደ መሆኑን አስታውሰዋል።
በቅዳሴው ሥነ-ሥርዓት ላይ የተነበበውን የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ኑዛዜን በማስታወስ፥ ክርስቲያኖች መስዋዕተ ቅዳሴን እና ሌሎች ጸሎቶችን እንዲያቀርቡ መጠየቃቸውን ተናግረው፥ ከዚያን ቀን ጀምሮ በየሳምንቱ ሐሙስ የሚቀርቡ መስዋዕተ ቅዳሴዎች በባዚሊካው ምድር ቤት እና ከብጽዕናቸው በኋላም በባዚሊካው ውስጥ በሚገኝ በቅዱስ ሴባስቲያን ጸሎት ቤት ውስጥ እንደሚቀርቡ አስረድተዋል።
በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ መካነ መቃብር ፊት ለፊት የሚቀርብ መስዋዕተ ቅዳሴ ከጸሎተ ሐሙስ ዕለት በቀር ላለፉት ሃያ ዓመታት ሳያቋርጥ፥ ሮም ውስጥ የሚኖሩ በርካታ ፖላንዳውያን እና በተለይም በያዝነው የኢዮቤልዩ ዓመት ወደ ሮም የሚመጡ በርካታ ነጋዲያን በሚሳተፉበት ሥነ-ሥርዓት እንደሚፈጸም ታውቋል።
ከቅርብ ጊዜያት ጀምሮ ከ 100 በላይ ካኅናት የሚሳተፉበትን ሳምንታዊ መስዋዕተ ቅዳሴን የቫቲካን ሬዲዮ እና በፖላንድ የሚገኙት ካቶሊካዊ ሬድዮ ጣቢያዎች የሚያስተላልፉትን የቀጥታ ስርጭት የፖላንድ ምዕመናን በመንፈስ በመተባበር እንደሚከታተሉት ብጹዕ ካርዲናል ኮንራድ ገልጸው፥ “ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ወደ ኅብረት ጎዳና የሚመሩን የአንድነት ምልክት ናቸው” ሲሉ በማስረዳት ቃለ ምልልሳቸውን ደምድመዋል።