ሊቀ ጳጳስ ጋላገር የሰላም እና ሃይማኖታዊ መልዕክቶችን ይዘው ወደ ሃንጋሪ መጓዛቸው ተነገረ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
ቫቲካን ከተለያዩ አገራት እና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር የምታደርገውን ግንኙነት በበላይነት የሚቆጣጠረው የቅድስት መንበር ጽ/ቤት ዋና ኃላፊ የሆኑት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ፖል ሪቻርድ ጋላገር ከመጋቢት 18 እስከ 21 ቀን 2017 ዓ.ም. በማዕከላዊ አውሮፓ ሃንጋሪ ሲያደረጉት የነበረውን ጉብኝት አጠናቀው ወደ ቫቲካን ተመልሰዋል።
በጉብኝታቸው ወቅት ለተለያዩ ተቋማት የእምነት ቃል እና የሰላም ጥሪ በማቅረብ፥ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስን ሰላምታና ቡራኬን ያስተላለፉ ሲሆን፥ እ.አ.አ. ከ 1930 እስከ 1945 ዓ.ም. ድረስ በቡዳፔስት የቅድስት መንበር ሐዋሪያዊ ተወካይ የነበሩት ብሎም አይሁዶች በጀርመኑ ናዚ በጅምላ ሲጨፈጨፉ በነበረበት በሆሎኮስት ወቅት እነሱን ለማዳን ባደረጉት ጥረት “በአሕዛብ መካከል የተገኘ ጻድቅ” በመባል የሚታወቁት እና በ 1965 ዓ.ም. ከዚህ ዓለም ድካም ያረፉትን ሊቀ ጳጳስ አንጄሎ ሮታ ሕልፈት 60ኛ ዓመት የመታሰቢያ በዓል ላይ ተሳትፈዋል።
ሊቀ ጳጳስ ጋላገር ከሀንጋሪ የውጭ ጉዳይ እና ንግድ ሚኒስትር ፒተር ስዚጃርቶ እና ሃንጋራዊያን አምባሳደሮች ጋር መጋቢት 19 ባደረጉት ወሳኝ የሆነ ውይይት 'ዓለም አቀፍ የሰላም ግንባታ፡ በግጭት አፈታት ውስጥ የሃይማኖት እና የዲፕሎማሲ ሚና' በሚል ጭብጥ ንግግር ያደረጉ ሲሆን፥ በተለይም “በዩክሬን እየተካሄደ ያለው ጦርነት የአውሮፓን የጸጥታ መሰረት ያናጋ መሆኑን፣ እንዲሁም በመካከለኛው ምስራቅ የእስራኤል እና የፍልስጤም ግጭቶች እየተባባሱ መሄዳቸውን” በማንሳት ውይይቱ ወቅታዊ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ሃይማኖትን በአግባቡ በመጠቀም ለእርቅ ማዋል
“ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየበረቱ የመጡት የተለያዩ ግጭቶች ታሪካዊ ቅሬታዎች፣ የግዛት አለመግባባቶች እና የሃይማኖት ውዝግቦች እንዴት እንደሚገናኙ በድጋሚ አሳይቷል” ያሉት ብጹእነታቸው፥ ይህም ሰላም ላይ ከጊዜ ወደ ጊዜ ተጽዕኖ እያሳደረ መምጣቱን በመግለጽ፥ በተመሳሳይም በሶሪያ፣ በየመን እና በሳህል አካባቢ እየተከሰቱ ያሉ ግጭቶች እና በተለያዩ የዓለም ክፍሎች የጂኦፖለቲካዊ ውጥረቶች እየተከሰቱ መሆኑን በቁጭት ተናግረዋል።
ሊቀ ጳጳስ ጋላገር “ለእነዚህ ግጭቶች የተለመዱ የፖለቲካ መፍትሄዎች ብቻቸውን ብዙ ጊዜ በቂ እንዳልሆኑ ያሳያሉ” ካሉ በኋላ፥ “ዘላቂ፣ ፍትሃዊ እና ቀጣይነት ያለው ሰላምን ለማስፈን ዲፕሎማሲ ብቻ ሳይሆን ሃይማኖት ከጥንት ጀምሮ ጠብቆ ያቆየውን የሞራል እና የሥነ ምግባር ጉዳዮችን የሚያቀናጅ ጥልቅ ግንኙነትን ይጠይቃል” በማለት ሰላም ግንባታ ላይ ሃይማኖት ያለውን ሚና አብራርተዋል።
በዚህ አግባብ ሃይማኖት ‘ለአብዛኛዎቹ የዓለማችን ሕዝቦች ትልቅ ጠቀሜታ እንዳለው’ እና በተገቢ ሁኔታ ጥቅም ላይ ሲውል ክፍፍሎችን የመሻገር፣ እርቅን የማጎልበት ብሎም ፖለቲካዊ መፍትሄዎች ብቻቸውን ሊያስገኙ የማይችሉትን የውይይት ዓይነት የማበረታታት ኃይል እንዳለው የቫቲካኑ ባለስልጣን አስታውሰዋል።
በወሳኝ ጊዜ ለሰላም ቁርጠኝነት
ከዚህም በተጨማሪ ሊቀ ጳጳስ ጋላገር በሃንጋራዊያን አምባሳደሮች ዓመታዊ ጉባኤ ላይ ከተካፈሉ በኋላ የሊቀ ጳጳስ ሮታ ሞት መታሰቢያ መርሃ ግብር ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉ ሲሆን፥ በጉባኤው ወቅት ባደረጉት ንግግር በቡዳፔስት ድጋሚ በመገኘታቸው ልዩ ኩራት እንደሚሰማቸው በመግለጽ፥ “በዚህ ወሳኝ ወቅት በዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ ቅድስት መንበር ሰላምን፣ ፍትህን እና ስምምነትን ለማስፈን በትጋት እየሰራች ትገኛለች” ብለዋል።
ከዚህም በተጨማሪ “በሩሲያ እና በዩክሬን መካከል እየተደረገ ያለው ጦርነት፣ የእስራኤል እና የሃማስ ግጭት፣ ሶሪያ፣ የመን እና ሊባኖስን የሚያጠቃልለው በመካከለኛው ምስራቅ እየታዩ ያሉ ትግሎች እና ሁከቶች፣ ዴሞክራሳዊት ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ ሱዳን እና የሳህል ክልሎችን ያካተተው በአፍሪካ ግዛቶች ውስጥ እየታየ ያለው የማያቋርጠው ብጥብጥ፣ እንዲሁም በዓለም ዙሪያ ያሉ ሌሎች ቀውሶች ጂኦፖለቲካዊ ተግዳሮቶችን ብቻ ሳይሆን አስቸኳይ እና አጠቃላይ ምላሾችን የሚሹ አስከፊ ሰብአዊ ቀውሶችንም ይወክላሉ” በማለት ሊቀ ጳጳስ ጋላገር ተናግረዋል።
የቫቲካን የሀገራት እና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ግንኙነት ጽህፈት ቤት ዋና ሃላፊው በማከልም “ቅድስት መንበር የሰውን ልጅ ክብር ግምት ውስጥ ያስገቡ ድርድሮች እና ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶች መደገፏን እንደሚትቀጥል” ጠቁመዋል።
“ቅድስት መንበር የድርድሮች እና የመፍትሄ ሃሳቦች ፍሬ ሃሳብ ውስጥ የሰውን ልጅ ክብር ግምት ውስጥ ያስገቡ ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶች መደገፏን አጠናክራ ትቀጥላለች”
ሊቀ ጳጳስ ሮታ ለተሰደዱት ያደረጉት የማያወላውል ጥበቃ
ሊቀ ጳጳስ ጋላገር የሊቀ ጳጳስ ሮታ ሞት መታሰቢያ ላይ በዚህ ወቅት በጦርነት እና በመከራ ውስጥ ላሉት በሙሉ ጸሎት እያደረጉ የሚገኙትን የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮን ልባዊ ቡራኬ ያቀረቡ ሲሆን፥ ብጹእነታቸው ባደረጉት ንግግር “የሊቀ ጳጳስ አንጀሎ ሮታን የሙት ዓመት በምናከብርበት በዚህ ልዩ ቀን ላይ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአደራ የሰጠንን ሰላም ለመጠበቅ በተቀደሰው ተልእኮአችን ጸንተን ለተቸገሩት እና ለተሰደዱት በማያወላውል መልኩ ድምፃችንን እንድናሰማ የእርሳቸው ምሳሌነት እንዲያነሳሳን መጸለይ ይገባል” በማለት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
ከዚህም በተጨማሪ የቫቲካን የውጪ ሃገራት እና የዓለም አቀፍ ድርጅቶች ግንኙነት ክፍል ዋና ጸሃፊው ሊቀ ጳጳስ አቡነ ጋላገር የቡዳፔስት ሜትሮፖሊታን ሊቀ ጳጳስ ከሆኑት ከብፁዕ ካርዲናል ፔተር ኤርዶ፣ ከሃንጋሪ ብጹአን ጳጳሳት ጉባኤ ፕረዚዳንት ብጹእ አቡነ አንድራስ ቬረስ እና ሌሎች የቤተክርስቲያን መሪዎች ጋር በመገናኘት ውይይት ያደረጉ ሲሆን፥ ቅዳሜ፣ መጋቢት 20 ቀን 2017 ዓ.ም. በፓኖን-ሃልማ የሚገኘውን የቅዱስ ማርቲን የቤኔዲክት ገዳምን እና የፓኖን-ሃልሚ ቤንሴ ጂምናዚየም ተማሪዎችን ጎብኝተዋል።
የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ሰላምታ
በመጨረሻው ቀን፣ እሑድ መጋቢት 21 ቀን 2017 ዓ.ም. በቡዳፔስት በሚገኘው የቅዱስ እስጢፋኖስ ካቴድራል የተካሄደውን መሥዋዕተ ቅዳሴ የመሩ ሲሆን፥ በሥነ ስርዓቱም ላይ “የቅዱስ አባታችንን መንፈሳዊ ቅርበት እና ጸሎት ሁሌ ከእናንተ ጋር እንደሆነ አረጋግጥላችኋለው” በማለት በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ስም ለሁሉም ሰላምታ በማቅረብ፥ “ቅዱስነታቸው በዚህ የመከራ እና ታመው ሆስፒታል በነበሩበት ወቅት ላደረጋችሁት እና አሁንም እያደረጋችሁት ላለው ጸሎት ምስጋና አቅርበዋል” ካሉ በኋላ፥ “ቅዱስ አባታችን ከህመማቸው እያገገሙ ባሉበት በአሁኑ ወቅት አባታዊ ቡራኬ ልከውላችኋል” በማለት በድጋሚ አረጋግጠውላቸዋል።
ሊቀ ጳጳስ ጋላገር በመጨረሻም ብፁዕ ካርዲናል ኤርዶ በመስዋዕተ ቅዳሴው ላይ እንዲገኙ ስለጋበዟቸው ምስጋናቸውን ገልጸው፥ በዕለቱም ባደረጉት ቃለ ምዕዳን ስለ አባካኙ ልጅ ምሳሌ ላይ በማስተንተን፣ ጌታ ለልጆቹ ያለውን ምንጊዜም መሐሪ የሆነውን ፍቅር በድጋሚ አስታውሰው፥ “በዚህ ጉዞ ውስጥ ያለንበት ቦታ ምንም ለውጥ አያመጣም፥ አባት ሁል ጊዜ የልጆቹን ቃላት፣ ውሳኔዎች እና ድርጊቶች ከማየት ይልቅ ለልጆቹ ያለውን ፍቅር ያስበልጣል ወይም ያምናል” ብለዋል።