MAP

ብጹዕ ካርዲናል ፒየትሮ ፓሮሊን፥ ብጹዕ ካርዲናል ፒየትሮ ፓሮሊን፥   (ANSA)

ብፁዕ ካርዲናል ፓሮሊን፥ በዩክሬን እና በጋዛ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን አሳሰቡ

የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ፒየትሮ ፓሮሊን፥ ከተጀመረ ሦስተኛ ቀኑን በያዘው እና በስደተኞች ጉዳይ በሚመክር ጉባኤ ላይ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር፥ ቅድስት መንበር ለሰላም፣ ለውይይት እና ለአብሮነት ያላትን የረዥም ጊዜ ቁርጠኝነትን በድጋሚ ገልጸዋል። የዓለም መሪዎችም ለሰው ልጅ ክብር እና ዓለም አቀፍ መረጋጋት ቅድሚያን በመስጠት ዲፕሎማሲያዊ መፍትሄዎችን እንዲቀበሉ አደራ በማለት በዩክሬን እና በጋዛ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን አሳስበዋል። የቅድስት መንበርን አቋም መሠረት በማድረግ በዩክሬን ፍትሃዊ እና ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን እና ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ድርድር እንዲደረግ ጥሪ አቅርበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ብጹዕነታቸው ስደትን፣ ስደተኞችን ማስተናገድን እና ማኅበራዊ ማካተትን በማስመልከት በተወያየው ስብሰባ ላይ ባደረጉት ንግግር፥ ጋዛ ውስጥ የፍትሃዊነት ስሜት እንዲታይ ጥሪ አቅርበው ሃማስ እና እስራኤል ወደ ሁከት ከመሄዳቸው ይልቅ ለችግሮቻቸው መፍትሄ እንዲፈልጉ አሳስበዋል። የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን መልዕክት በመጥቀስ፥ የኒውክሌር ጦር መሣሪያዎችን መያዝ ሥነ-ምግባር የጎደለው እንደሆነ በማስገንዘብ በጥብቅ አውግዘው፥ “በዓለም አቀፍ ሰብዓዊነት ሕግ ላይ ስልታዊ ጥሰት እየተፈጸመ ነው” ሲሉም ተናግረዋል።

ወደ ግጭት የሚውስዱ ቃላትን ማስወገድ 

ብፁዕ ካርዲናል ፓሮሊን፥ ቋንቋ በዓለም አቀፍ የፖለቲካ መድረክ ላይ ስላለው ኃይል ሲናገሩ፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቅርቡ ለጣሊያን ዕለታዊ ጋዜጣ በጻፉት መልዕክት፥ “ወደ ግጭት የሚወስዱ ቃላትን ማስወገድ ይገባል” በማለት ማብራሪያ መስጠታቸውን አስታውሰዋል።

አዲሱ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ እና ግብረ አበሮቻቸው በቅርቡ አውሮፓውያን “ጥገኛ ተውሳኮች” ናቸው ሲሉ የተናገሯቸውን አስተያየቶች ጨምሮ በስብሰባው ላይ ከተገኙት አባላት ጋር ባደረጉት ውይይት፥ “ቃላት ወደ ጦርነት እንዳይቀይሩ መቆጠብ አስፈላጊ ነው” ሲሉ ተናግረዋል።

“ይህ ሁሉንም ሰው የሚመለከት በመሆኑ ውጥረት በበዛበት በዛሬው የዓለም አቀፍ ሁኔታ ውስጥ በመጠኑ መናገር፣ ወይም ቃላትን በጥበብ መጠቀም፣ ካልሆነ ደግሞ ዝምታን መምረጥ እንደሚገባ በማሳሰብ፥ ከመከፋፈል ይልቅ ውይይት እና አንድነት ይመረጣል” ሲሉ አስረድተዋል።

የኒውክሌር መሣሪያዎች መጠቀም ኢ-ሞራላዊነት

ብፁዕ ካርዲናል ፓሮሊን የሰላምን መዳከም በማጉላት ከሕግ ባለሙያ ጋር ያደረጉት ውይይት፥ ብዙዎች ሰላምን አቅልለው እንደወሰዱት ገልጸው፥ ይህ አመለካከት አዲስ ግጭት እንዲቀሰቀስ የሚያደርግ እንደሆነ ጠቁመው፥ “የችግሩ መንስኤ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣው ግላዊ የዓለም አመለካከት እና የጋራ መተማመን በመቀነሱ ነው” ሲሉ አስረድተዋል።

ይህን የእምነት መሸርሸር ከወታደራዊ ግንባታ ጋር የገናኙት ብፁዕ ካርዲናል ፓሮሊን፥ የዲፕሎማሲ እጦት ሀገራት መሣሪያን እንዲታጠቁ በማበረታታት ለጦርነት እንዲዘጋጁ እንደሚያደርግ በመግለጽ፥ በመሆኑም የኒውክሌር ጦር መሣሪያ ባለቤትነት አስከፊ መዘዝ እንደሚያስከትል በመግለጽ፥ “የኒውክሌር ጦር መሣሪያ ባለቤትነት ሥነ-ምግባር የጎደለው” ነው በማለት የቅድስት መንበርን ጽኑ አቋም በድጋሚ ገልጸዋል።

በዚህ ላይ የዓለም አቀፍ ተቋማት ሚና

በቅርቡ በበጎ ፍቃደኞች ጥምረት በፓሪስ የተካሄደውን ስብሰባ ያስታወሱት ብጹዕ ካርዲናሉ ፒየትሮ ፓሮሊን፥ ዓለም አቀፋዊ ሥርዓት የሚመካው መንግሥታት የጸደቁ ስምምነቶችን ለማስከበር ባላቸው ፍላጎት ላይ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል።

“ያለ ፖለቲካዊ ፍላጎት ሰላማዊ እና ገንቢ የሆነ ዓለም አቀፍ አስተዳደር ሊመሠረት አይችልም” ሲሉም አክለዋል። ዓለም አቀፍ ድርጅቶች የተመሠረቱት በቀዝቃዛው ጦርነት ወቅት እና ከ20ኛው ክፍለ ዘመን አስከፊ ዓለም አቀፍ ግጭቶች በኋላ ቢሆንም እነዚህ ተቋማት ከዘመናዊው ዓለም ጋር ለመላመድ ሲታገሉ እንደነበር ጠቁመዋል።

ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን እነዚህን ሥርዓቶች መልሶ ለማምጣት በሚደረግ ጥረት መካከል ሆነው ተስፋ መቁረጥ ሊኖር እንደሚችል አስጠንቅቀው፥ “ተስፋ መቁረጥ ዛሬ በአስጨናቂ ሁኔታ ውስጥ በጋራ የሚሰሩት የኅብረተሰቡን እውነተኛ ፈተናዎች እንዳይፈቱ ይከለክላቸዋል” በማለት አስረድተዋል።

“ለውጥ ለማምጣት እውነተኛ ፍላጎት አለ ወይ?” ከሚለው ጋር ደካማ የትብብር መርሆዎች ዓለም አቀፍ ፖለቲካን እየመሩ ይገኛል ወይ? በማለት፥ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች እውነታዎችን ግልጽ ለማድረግ አዲስ ጥረት እንዲያደርጉ አሳስበዋል።

ቤተ ክርስቲያን በሰላም እና በስደት ጉዳዮች ላይ ያላት ቁርጠኝነት

የመገናኛ ብዙሃን የሰላም እና የውይይት መልዕክቶችን ለማስተላለፍ ያላቸውን ሚናን አንስቶ በተወያየው ስብሰባ ላይ የተናገሩት ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን፥ በብሔራዊ ጥቅም ወይም በሚዲያ ቸልተኝነት ምክንያት ወደጎን ለሚባሉ ጉዳዮች ትኩረት መስጠት የክርስቲያኖች ግዴታ ነው” ሲሉ አስገንዝበዋል።

ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን አውሮፓውያን በስደት ላይ ያላቸውን አመለካከት በማስመልከት ሲናገሩ፥  አውሮፓውያን ስለ ስደት አሉታዊ ግንዛቤ ቢኖራቸውም፥ አውሮፓ ስደተኞችን በአስቸኳይ እንደምትፈልግ አስረድተዋል። አሁን ያለው ትኩረት ሕገ-ወጥ ስደትን ለመቀነስ ያለመ እንደሆነ ገልጸው፥ ነገር ግን የሕዝቡን አመለካከት ከፍርሃት ማላቀቅ አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመዋል።

አውሮፓ በስደተኞች መወረሯ ብዙዎች እንዳስፈራቸው የገለጹት ብፁዕ ካርዲናል ፓሮሊን፥ ነገር ግን ይህ መወገድ ያለበት የተሳሳተ ግንዛቤ እንደሆነ ተናግረው፥ ከድህነት ወይም ግጭት የሚሸሹ ወንድሞቻችንን እና እህቶቻችንን የሚጠቅም የበለጠ አዎንታዊ አካሄድን በመከተል የሚያርፉባቸውን ቦታዎች መስጠት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።

የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ፒየትሮ ፓሮሊን፥ በመካከለኛው ምሥራቅ አገራት ውስጥ የሚታየው የክርስቲያኖች ስደት ከሃይማኖትም ሆነ ከማኅበረሰብ አንፃር አሳዛኝ እንደሆነ በቁጭት ተናግረው፥ በክልሉ የክርስቲያኖች ቁጥር እየቀነሰ መምጣቱ ታሪካዊ ሃይማኖታዊ መሠረቶችን ከማዳከም ባለፈ ውጥረቶችን ለማርገብ የሚያግዘውን ጥረት እንደሚያስወግድ አስጠንቅቀው፥ “ክርስቲያን የሌለበት ማኅበረሰብ አክራሪ እና ጽንፈኛ የመሆን አደጋ ያጋጥመዋል” በማለት ንግግራቸውን ደምድመዋል።

 

29 Mar 2025, 16:01