የሥነ-ሕይወት ጥናት ጳጳሳዊ አካዳሚ፥ የሰው ልጅ ዕድሜን በማስመልከት ስብሰባ አካሄደ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
በቫቲካን ጳጳሳዊ የሕይወት አካዳሚ የጊዜ ተግዳሮትን በማስመልከት ትናንት ሰኞ መጋቢት 15/2017 ዓ. ም. ከሰዓት በኋላ ሮም በሚገኘው በቅዱስ አጎስጢኖስ ገዳም ጳጳሳዊ ኢንስቲትዩት ውስጥ ስብሰባ መካሄዱን፥ ስብሰባውን አስመልክቶ የወጣ የቅድስት መንበር መግለጫ አስታውቋል።
በስብሰባው ላይ ንግግር ያደረጉት፥ የሥነ-ሕይወት ጥናት ጳጳሳዊ አካዳሚ ፕሬዚደንት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ቪንቼንሶ ፓሊያ፣ የስብሰባው አዘጋጅ ኮሚቴ ሰብሳቢ አባ አልቤርቶ ካራራ፣ የነርቭ ቀዶ ጥገና ሐኪም እና የፋውንዴሽኑ መሥራች ዶክተር ጁሊዮ ማይራ፣ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ 2009 ዓ. ም. በኬሚስትሪ ጥናት የኖቤል ተሸላሚ የነበሩት ዶክተር ቬንካትራማን ራማክሪሽናን እና የህዋስ ባዮሎጂ እና ማንሰራሪያ ሕክምና ሊቃውንት ዶ/ር ሁዋን ካርሎስ ኢዝፒሱዋ ቤልሞንቴ እንደሆኑ ታውቋል።
በር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ከሆስፒታል መውጣት የተሰማው ደስታ እና የቅዱስነታቸው ሰላምታ
የቅድስት መንበር መግለጫ ክፍል ምክትል ዋና ዳይሬክተር ክርስቲያን መሬይ፥ ቅዱስነታቸው ወደ ቫቲካን በመመለሳቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልጸው፥ በቀጣይ የማገገሚያ ወቅትም በጸሎት ከጎናቸው እንደሚሆኑ ገልጸዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ አረጋውያን የኅብረተሰቡ ትዝታ እና ጥበብ መሆናቸውን ደጋግመው መናገራቸውንም አስታውሰው፥ በመሆኑም የዕድሜ ባለጸግነት ጸጋ እንጂ ስብዕናን የማሽቆልቆል ጉዳይ አይደለም ሲሉ ተናግረዋል።
ሊቀ ጳጳስ አቡነ ፓሊያ በስብሰባው ላይ ለተገኙትን አራት ወይም አምስት ትውልዶች አቀባበል አድርገው፣ በትውልዶች መካከል የእርስ በርስ ትውውቅ እጥረት እንዳለ በመገንዘብ ለጉዳዩ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ አሳስበዋል።
የጳጳሳዊ አካዳሚው ፕሬዘዳንት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ፓሊያ፥ “አረጋውያን የኅብረተሰቡ ሸክም ሳይሆኑ ነገር ግን ጠቃሚ ግብዓት እንደሆኑ በማስረዳት፥ ልምዳቸው እና ጥበባቸው የማይተካ ባህላዊ እና ሰብዓዊ ቅርስ ነው” ሲሉም አክለዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ “አረጋውያንን የማይንከባከብ ማኅበረሰብ የወደፊት ዕጣ ፈንታው ባዶ ነው” ማለታቸውን በማስታወስ፥ “የዕድሜ ባለጸግነት እሴትን የሚገነዘብ እና የአረጋውያንን መገለል የሚያስቀር ባህልን ማስተዋወቅ እንደሚያስፈልግ አጽንኦት ሰጥተዋል።
ሊቀ ጳጳስ አቡነ ፓሊያ በዐውደ-ጽሑፋቸው፥ የሳይንሳዊ ግኝቶች ፍትሃዊ ተደራሽነት ዋና ርዕሠ ጉዳይ እንደሆነ በማስረዳት፥ ባዮሜዲካል ፈጠራዎች ለጥቂቶች ብቻ የተሰጠ ዕድል ሳይሆን ነገር ግን ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ደረጃቸው ምንም ይሁን ምን የሁሉንም ሰው የሕይወት ጥራት ለማሻሻል የሚረዱ መሣሪያዎች መሆን እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።
“ዋና ግቡ ረዘም ያለ ጊዜ መኖር ብቻ ሳይሆን የተሻለ ኑሮ መኖር ነው” በማለት አጽንኦት ሰጥተው፥ በሽታዎችን ለመከላከል እና ሁሉም ሰው ጤናማ እና የተከበረ የእርጅና ጊዜ እንዲኖረው ለማድረግ በርትቶ መሥራት እንደሚገባ አደራ ብለዋል።
የወደፊት ማኅበረሰቦች አስመልክቶ የቀረቡ ጥያቄዎች
እንደ ጎርጎርሳውያኑ በ2009 ዓ. ም. በኬሚስትሪ ጥናት የኖቤል ተሸላሚ የሆኑት ዶ/ር ቬንካትራማን ራማክሪሽናን በበኩላቸው፥ በምርምር ውስጥ ሰዎች ብዙ ዕድሜ እንዲኖሩ ማድረግ ሳይሆን ጤናማ ሕይወት እንዲኖራቸው ማድረግ እንደሆነ አሳስበው፥ ይህንን ተግባራዊ ማድረግ ሙሉ በሙሉ ግልፅ አይደለም ብለዋል። “ሁላችንም ረጅም ዕድሜ መኖር ከጀመርን ምን ዓይነት ማኅበረሰብ ይኖረናል?” ሲሉ ጠይቀዋል።
በተለይ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ልዩነት ሊኖር እንደሚችል ጠቁመው፥ ይህም የበለጸጉ አገሮችን ሲጠቅም ሌሎችን ደግሞ ለችግር ሊዳርግ እንደሚችል አስረድተዋል። ረጅም ዕድሜን እና አዲስ የሕክምና ዘዴዎችን የሚያስተዋወቁ ከሆነ ሁለት-ደረጃ ያለው ማኅበረሰብ ሊኖር እንደሚችል እና ይህም በአንዳንድ የበለጸጉ አገሮች ውስጥ ብዙ ዓመት የመኖር ዕድልን በማመቻቸት ልዩነት እንደሚፈጥር በማስረዳት ይህ የማይቀር በመሆኑ ግምት ውስጥ ሊገባ ይገባል ብለዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችኮስን በቅርቡ ያጋጠማቸውን ሕመም በተመለከተ ጥያቄ የቀረበላቸው ሊቀ ጳጳስ አቡነ ፓሊያ፥ እርጅና በአቅመ ደካማነት እንደሚገለጽ ተናግረው፣ ይህ አገላለጽ ማግለልን ወይም መነጠልን ለማስከተል ሳይሆን ለዕድሜ ባለጸጎች እንክብካቤ ማድረግ እንደሚገባ የሚያሳስብ መሆኑን በማስረዳት፥ ሁላችንም ተሰባሪዎች በመሆናችን ለሕይወታችን ትልቅ ትርጉም ሊሰጠው ይገባል ብለዋል።
ሮም ውስጥ ከሚገኝ ጄሜሊ ሆስፒታል ጋር ግንኙነት ያላቸው ፕሮፌሰር ማይራ በበኩላቸው፥ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የጤና ሁኔታ አሳሳቢነትን በመግለጽ፥ ለቅዱስነታቸው አስፈላጊው እንክብካቤ እና ትክክለኛ የማገገሚያ ጊዜ እንደሚያስፈልጋቸው በማመን፥ ተመሳሳይ ችግር እንደገና እንዳይከሰት ማረጋገጥ ዶክተሮች ዘወትር ለታካሚዎች የሚሰጡት ትኩረት እንደሆነ አስረድተዋል።