ቅድስት መንበር ጥረቶችን በማስተባበር ዘመናዊ ባርነትን መዋጋት እንደሚገባ አሳሰበች
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
የባርነት ሰለባዎችን እና በአትላንቲክ የባሪያ ንግድ የተጎዱትን ለማስታወስ ተብሎ በታወጀው ዓለም አቀፍ ቀን ላይ የአሜሪካ መንግሥታት ድርጅት ቋሚ ምክር ቤት ተወካይ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ሁዋን አንቶኒዮ ክሩዝ ሰርራኖ፥ ባርነት ያለፈ ታሪክ ሳይሆን ነገር ግን ዛሬም እየተፈጸመ ያለ መቅሰፍት መሆኑን አስታውሰው፥ ለዚህ ክስተት ዓይናችንን እና ጆሯችንን የምንዘጋ ከሆነ እኛም የክስተቱ ተባባሪዎች እንሆናለን ብለዋል።
የቅድስት መንበር ቋሚ ታዛቢው ለምክር ቤቱ አባላት ባስተላለፉት መልዕክት፥ የባርነት ታሪክ እና የባሪያ ንግድ ሁሌም መታወስ እንዳለበት ገልጸው፥ ነገር ግን ያ ትውስታ የዘመናዊው ባርነት እውነታን እንድንዘነጋ የሚያደርገን መሆን እንደሌለበት አሳስበዋል።
አቡነ ሁዋን አንቶኒዮ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን ንግግር በማስታወስ እንደተናገሩትም፥ ባርነት ወደ ዕቃነት የወረዱት ወንዶችና ሴቶች ለሌሎች ሰዎች በሚሰጡት ጥቅም መጠን ያሳንሳቸዋል ብለዋል።
የዘመኑን ባርነት መቅሰፍት ማስወገድ
ሊቀ ጳጳስ አቡነ ሁዋን አንቶኒዮ ይህን የተናገሩት በአሜሪካ ውስጥ የሚገኙ አፍሮ-አሜሪካውንን በማስመልከት ለስምንተኛ ጊዜ በተካሄደው የኢንተር-አሜሪካ ሳምንት ጉባኤ ላይ ሲሆን፥ ዘመናዊ ባርነት የእነዚህን እውነታዎች ክብደት እና ስፋት እንድንገነዘብ ይረዳናል ብለዋል።
ይህም ስለ ጉዳዩ ግንዛቤ ማስጨበጥ እና ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመዋጋት የሚደረገውን ጥረት በተሻለ መልኩ ለማስተባበር መነሳሳትን መፍጠር አለበት ብለው፥ ይህንን መቅሰፍት ለማጥፋት እነዚህ ጥረቶች አንድ መሆን አለባቸው ብለዋል።
ስለሆነም በሕዝቦች መካከል የሚፈለገውን ሰላማዊ መግባባት ለመፍጠር ሂደቶችን መጀመር እና ለሰብዓዊ ክብር እውቅናን መስጠት ማዕከላዊ ቦታን መያዝ አለበት ብለዋል።
ቅድስት መንበር ብዙውን ጊዜ የማይታዩ እና ያልተሰሙ ነገር ግን በማኅበረሰቡ ውስጥ የተሸሸጉ እና ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ሰለባዎች ተሞክሮዎችን በሚያካትት የሥነ-ምግባር፣ ማኅበራዊ እና መንፈሳዊ ትምህርት ላይ ያላትን ቁርጠኝነት ለምክር ቤቱ አባላት አረጋግጠዋል።
ሊቀ ጳጳስ አቡነ አቡነ ሁዋን አንቶኒዮ በመጨረሻም፥ ቅድስት መንበር በጋራ ሰብዕና ውስጥ ላለው ወንድማማችነት እውቅናን በመስጠት ፍትሃዊ የሆነ ማኅበረሰብ ለመፍጠር የሚያግዝ በቂ የትምህርት እና የስልጠና ዋስትናን ለመስጠት ቁርጠኛ መሆኗን አረጋግጠዋል።