MAP

በጋዛ የተከሰተው ውድመት በጋዛ የተከሰተው ውድመት  (AFP or licensors)

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ጦርነት ‘ትርጉም አልባ’ መሆኑን ጠቆሙ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ሮም ከሚገኘው ጀሜሊ ሆስፒታል ዓለም አቀፋዊ ኃይሎች ወታደራዊ ሃይላቸውን እንደገና ለማጠናከር እየተጣደፉ በሚገኙበት በአሁኑ ወቅት ጦርነት “ትርጉም አልባ” መሆኑን ባረጋገጡበት መልዕክት ላይ የቫቲካን ዜና ኤዲቶሪያል ዳይሬክተር ሃሳባቸውን ሰንዝረዋል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

ሮም ከሚገኘው ጀሜሊ ሆስፒታል ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ የጦርነትን ከንቱነት የበለጠ ግልፅ እና በማያሻማ ሁኔታ እንደሚመለከቱት ተናግረዋል።
ምናልባትም ብጹእነታቸው የተናገሩት ጥቂት ቃላቶች ብቻ ሊሆኑ ይችላሉ፥ ነገር ግን ትርጉም ያላቸው ነበሩ። በተመሳሳይ ጊዜ፥ በሚያሳዝን ሁኔታ በመካከለኛው ምስራቅ፣ በጋዛ ውስጥ የእስራኤል ወታደራዊ ሃይሎች አዳዲስ የቦምብ ጥቃቶች እንደገና ማድረሳቸውን በቀጠሉበት በአሁኑ ወቅት እነዚህ ቃላቶች ትልቅ ትርጉም አላቸው።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ማክሰኞ ማለዳ ለንባብ ለሚቀርበው ‘ኮሪየር ዴላ ሴራ’ ለሚባለው የጣሊያን ጋዜጣ ዳይሬክተር በተላከ ደብዳቤ ላይ ጦርነት ማህበረሰቦችን እና አካባቢን እያወደመ መሆኑን በመጥቀስ፣ መጥምቁ ዮሐንስ በምድረ በዳ እንደጮኸው ሁሉ ቅዱስ አባታችንም ድምፃቸውን በድጋሚ አሰምተዋል።

አውሮፓን ጨምሮ ዓለም ብዙ ገንዘብ ኢንቨስት በማድረግ ቀድሞውንም ታጥቆ የነበረውን እና የሰው ልጅን አስር እጥፍ ሊያጠፋ የሚችለውን የጦር መሳሪያ እንደገና ለመታጠቅ እየተጣደፈ በሚገኝበት በአሁኑ ወቅት፥ በህመም የተዳከሙት እና ህክምና ላይ የሚገኙት የጴጥሮስ ተተኪ ወደ ሶስተኛው የዓለም ጦርነት የምናደርገውን እሽቅድምድም የምናቆምበትን መንገድ ከማሳየት አልተቆጠቡም።

ብጹእነታቸው በመልዕክታቸው፥ መጀመሪያ እና ከሁሉም በላይ ቃላቶቻችንን እና አእምሮአችንን ነፃ እንድናደርግ ጋብዘውናል። ከዚህም ባሻገር ምድርን ከጦር መሳሪያ ነፃ እንድናደርግ ጋብዘውናል።

የተለያዩ ድርድሮች እና የመሪዎች ስብሰባዎች እንኳን በዓለም አቀፍ ቴሌቭዥን በሚካሄዱበት፣ አንድን ሃሳብ የሚቃወሙ ሰዎችን አጋንንት ማድረግ በተለመደበት፣ አክራሪነት በነገሰበት እና የውሸት ዜናዎች በብዛት በሚሰራጩበት በዚህ ወቅት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ሁሉም ሰው በማሰላሰል፣ በእርጋታ እና የእውነታውን ውስብስብነት በመረዳት እንዲሳተፍ ጋብዘዋል።

ከምንም በላይ ዲፕሎማሲ የተረሳ በሚመስልበት ዓለም ውስጥ ይሄንን እንደገና እንድናበረታታ፣ እንዲሁም እንደገና መጠናከር ለሚገባቸው ዓለም አቀፍ ድርጅቶች አዲስ ህይወት እና ታማኝነትን እንድንሰጥ ጋብዘውናል።

በቅድስት መንበር የሞሮኮ ኤምባሲ ሰኞ ዕለት ባዘጋጀው የኢፍጣር ሥነ ስርዓት ላይ የቅድስት መንበር ዋና ጸሃፊ ብጹእ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን ስለ አውሮፓ አዲሱ ራስን በጦር መሳሪያ እንደገና ስለማደራጀት ፕሮጄክት ተጠይቀው፥ ‘መንገዱ ትጥቅ የማስፈታት እንጂ የማስታጠቅ መሆን ዬለበትም’ ሲሉ አስታውሰዋል።

ካርዲናሉ በማከልም “እንደ አዲስ የጦር መሳሪያ ለመታጠቅ የሚመርጡ ሃገራት፣ ይዋል ይደር እንጂ የጦር መሳሪያዎች ምንም ያህል የታገዱ ቢመስሉም ጥቅም ላይ ሊውሉ ይችላሉ የሚለውን እውነታ መጋፈጥ አለባቸው” ካሉ በኋላ፥ በዓለም አቀፍ ደረጃ አጠቃላይ እና ቁጥጥር የሚደረግበት ትጥቅ ማስፈታት (ጦር መሳሪያ ቅነሳ) ሥራ መስራት ይገባል፥ ይህ አቋም ከአንደኛው የዓለም ጦርነት ጊዜ ጀምሮ የቅድስት መንበር ፖሊሲ መሆኑ እና ወደፊትም የማያቋርጥ ነው” በማለት የቫቲካንን አቋም አስረድተዋል።

ብጹእ ካርዲናል ፓሮሊን በመጨረሻም “ሆኖም ግን የምንወስዳቸው አቅጣጫዎች በቂ ባይሆኑም፥ በተቃራኒው የጦር መሳሪያዎች መጠናከርን እያየን ነው” ብለዋል።
 

20 Mar 2025, 13:48