ለሰው ልጅ ሕይወት የሚቀርብ የወንጌል ምስክርነት ሐዋርያዊ መልዕክት 30ኛ ዓመት ተከበረ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤቱ የሰው ልጆችን ሕይወት ለመጠበቅ ፣ ለመንከባከብ እና ለማስተዋወቅ ባለው ዓላማ “ሕይወት ሁል ጊዜም መልካም ነው” በሚል ርዕሥ ሥር የቤተ ክርስቲያንን ጥረት ለመጀመር እና ለማስፋፋት የሚያግዝ ሐዋርያዊ ማዕቀፍን ይፋ አድርጓል።
የሰው ሕይወት ክቡር እና ዋጋ ያለው መሆኑን የሚገልጽ የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ 2ኛ ሐዋርያዊ መልዕክት ይፋ የሆነበት 30ኛ ዓመት መጋቢት 16/2017 ዓ. ም. ተከብሮ ውሏል።
ዕለቱ በተከበረበት ቀን በቅድስት መንበር የምእመናን እና የቤተሰብ ሕይወት መምሪያ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት፥ “ለሰው ሕይወት ሊሰጥ የሚገባውን ሐዋርያው እንክብካቤ ለመስጠት እና ለማስተዋወቅ የሚያግዝ ሐዋርያዊ ማዕቀፍን ይፋ አድርጓል።
“ሕይወት ሁል ጊዜም መልካም ነው” በሚል ርዕሥ የተዘጋጀው ሐዋርያዊ ማዕቀፉ በተለይም ሰብዓዊ መብቶች በሚጣሱባቸው አካባቢዎች የሰዎችን ሕይወት ከጥቃት ለመከላከል፣ ለመጠበቅ እና ለማስተዋወቅ ያለመ እንደሆነ ተመልክቷል።
ሐዋርያዊ ማዕቀፉ በጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤቱ ድረ-ገጽ ላይ በእንግሊዝኛ፣ በጣሊያንኛ እና በፖርቱጋልኛ ቋንቋዎች ተተርጉሞ የተቀመጠ በመሆኑ በነጻ ማግኘት የሚቻል ሲሆን በቅርብ ቀናት ውስጥ በፈረንሳይኛ እና በስፓኒሽ ቋንቋዎችም እንደሚገኝ ታውቋል።
በቅድስት መንበር የምእመናን እና የቤተሰብ ሕይወት መምሪያ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት አስተባባሪ ብፁዕ ካርዲናል ኬቨን ፋሬል፥ በሁሉም ሁኔታዎች መካከል ሕይወትን እንዴት መጠበቅ እንደሚገባ የሚያመለክት ሥራን አስተዋውቀዋል።
“እጅግ ከባድ በሆነ ሁኔታ የሰው ልጅ ክብር ለአደጋ በተጋረጠበት ወቅት፣ ብዙ አገሮችን በጦርነት ሁሉም ዓይነት ጥቃቶች በሚደርሱበት በዚህ ወቅት፥ በተለይም በሴቶች ላይ ጥቃት በሚደርስበት ወቅት፣ ሕጻናት ከመወለዳቸው በፊት እና ከተወለዱ በኋላ፣ ወጣቶች፣ የአካል ጉዳተኞች፣ አዛውንቶች፣ ድሆች እና ስደተኞች ሰብዓዊ ክብራቸው ይረገጣል” ሲሉ አጽንዖት ሰጥተዋል። ብፁዕ ካርዲናል ኬቨን ፋሬል፥ “ይህ በሚሆንበት ዓለም ውስጥ ለሰው ሕይወት እውነተኛ ሐዋርያዊ እንክብካቤ የሚደረግበትን መንገድ መፍጠር አለብን ብለዋል።
ዕቅዱን በተግባር ላይ ማዋል
ብፁዕ ካርዲናል ኬቨን ፋሬል ይህን ተግባራዊ ለማድረግ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤታቸው፥ “Dignitas infinita” ወይም ወሰን የሌለው የማያልቅ ክብር” በሚል ርዕሥ በቅርቡ ያወጣው መግለጫ ቁልፍ እንደሆነ ገልጸው፣ እያንዳንዱ ሰው ለሕይወቱ የማይገደብ ክብር እንዳለው፣ በሁሉም ሁኔታዎች መካከል የበላይነት እንዳለው ተናግረዋል።
በመሆኑም የእያንዳንዱ ሰው ሕይወት ሁል ጊዜ ሊከበር እና ሊጠበቅ እንደሚገባ፣ ይህ ምክንያታዊ መርህ በሁሉም ሀገር፣ መንደር እና ቤተሰብ ውስጥ መተግበር እንዳለበት ካርዲናል ፋሬል አሳስበዋል።
ከብጹዓን ጳጳሳት ጋር በዘላቂነት በመካሄድ ላይ ያለው ውይይት ውጤት የሆነው ሐዋርያዊ ማዕቀፍ በዓለም አቀፍ ደረጃ በሚገኙ ሀገረ ስብከቶች ዘንድ ሰፊ በሆነ መንገድ ለሰው ልጅ ሕይወት ሊሰጥ የሚገባውን ሐዋርያዊ እንክብካቤ ለማስተዋወቅ የተሻሻለ ዘዴን እንደሚያቀርብ ታምኖበታል።
በዚህ ምክንያት በቅድስት መንበር የምእመናን እና የቤተሰብ ሕይወት መምሪያ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት፥ እያንዳንዱ ጳጳስ፣ ካህን፣ ገዳማውያን እና ገዳማውያት እንዲሁም ምእመናን ይህን ሐዋርያዊ ማዕቀፍ በማንበብ ለሰው ልጅ ሕይወት የሚሰጥ የተቀናጀ ሐዋርያዊ እንክብካቤን ለማዳበር ጥረት እንዲያደርግ በማሳሰብ፥ ሐዋርያዊ ማዕቀፉ ሠራተኞች፣ መምህራን፣ ወላጆች፣ ወጣቶች እና ልጆች የእያንዳንዱን ሰው ሕይወት ታላቅነት የሚያከብሩበትን ትክክለኛ ዕውቀት እንደሚሰጥ ታውቋል።