MAP

ብፁዕ ካርዲናል ፕረቮስት ለርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጤንነት የመቁጠሪያ ጸሎት በቫቲካን ሲያደርጉ ብፁዕ ካርዲናል ፕረቮስት ለርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጤንነት የመቁጠሪያ ጸሎት በቫቲካን ሲያደርጉ  (VATICAN MEDIA Divisione Foto)

ብፁዕ ካርዲናል ፕረቮስት የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮን የጤና ሁኔታ ለማርያም አደራ እንስጥ አሉ!

በስምንተኛው ተከታታይ ምሽት ምእመናን በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ተሰብስበው ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የመቁጠሪያ ጸሎት ማድረጋቸው ተገልጿል።

የዚህ ዜና አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

ሰኞ የካቲት 24/2017 ዓ.ም ማምሻውን በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የጤና ሁኔታ ይሻሻል ዘንድ የመቁጠሪያ ጸሎት የተደርገ ሲሆን ይህንን የመቁጠሪያ ጸሎት የመሩት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ ካርዲናል ሮበርት ፕሪቮስት “ለቅዱስ አባታችን ፍራንችስኮስ ጤና ለየት ባለ ሁኔታ ጸሎት እንዲደረግ ጥሪ ያቀረቡ ሲሆን ከቤተክርስቲያን እናት ማርያም ጋር በጸሎት እንኑር ሲሉ በጸሎቱ መግቢያ ላይ መናገራቸው ተገልጿል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከየካቲት 07/2017 ዓ.ም ጀምሮ በብሮንካይተስ በሽታ ምክንያት በሆስፒታል ውስጥ ይገኛሉ፣ የጤና ሁኔታቸው የተረጋጋ እንደሆነም ተዘግቧል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ በሆስፒታል ውስጥ ብዙ ቀናትን ካሳለፉ በኋላ ቫቲካን ለጳጳሱ ጤንነት መደበኛ የምሽት የመቁጠሪያ ጸሎት ማድረግ መጀመሯን ገልጻ እንደ ነበረ እና በዚህ መሰረት የመቁጠሪያ ጸሎት በምሽት መደረግ ጀመረ፣  በሮም የሚገኙ ካርዲናሎች ከምእመናን ጋር በጋራ በመሆን ጸሎቱን ይመራሉ።

በሰኞ እለት የተደረገውን የመቁጠሪያ ጸሎት የመሩት ካርዲናል ፕሬቮስት፣ ማርያም፣ “የቅዱስ ተስፋ እናት፣ የእርሷን እርዳታ የሚፈልጉትን ሁሉ ትረዳለች፣ ታድሳለች፣ እና ታጽናናለች” በማለት አፅንዖት ሰጥተው የተናገሩ ሲሆን እሷም “የመጽናናት እና የተረጋገጠ የተስፋ ምልክት” እንደምትሆን ያላቸውን ተስፋ ገልጸው ነበረ።

በሮም የሰዓት አቆጣጠር ከምሽቱ 3 ሰዓት (በኢትዮጲያ የሰዓት አቆጣጠር ከምሽቱ 5 ሰዓት) ላይ የሚካሄደው የምሽት የጸሎት ጊዜ የሚከናወነው በቅዱስ ጴጥሮስ ባሲሊካ በረንዳ ላይ ሲሆን  "የቤተ ክርስቲያን እናት ማርያም" ምስል በተገኘበት ይካሄዳል። ብፁዕን ካርዲናሎች፣ ጳጳሳት፣ ካህናት፣ ገዳማዊያን/ገዳማዊያት ወንዶች እና ሴቶች፣ እና በመቶዎች የሚቆጠሩ ምእመናን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከሕመማቸው ያገግሙ ዘንድ  ለቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት በአደራ ለመስጠት በየምሽቱ ተገናኝተው ጸሎት እንደምያደርጉ ይታወቃል።

05 Mar 2025, 13:36