MAP

ብጹዕ ካርዲናል ፒየትሮ ፓሮሊን፥ ብጹዕ ካርዲናል ፒየትሮ ፓሮሊን፥  

ካርዲናል ፓሮሊን፥ “ለሰብዓዊነት ሕግ ክብር እየተሰጠው አይደለም” ሲሉ ተናገሩ

የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ፒየትሮ ፓሮሊን፥ “በዓለም አቀፍ ሰብዓዊነት ሕግ ላይ ስልታዊ ጥሰት እየተፈጸመ ነው” ሲሉ ተናግረዋል። በተለይም በሲቪሎች ላይ የሚደርስ የቦምብ ጥቃት እና የዕርዳታ ሠራተኞች ግድያ እንዳሳሰባቸው ገልጸዋል። ብጹዕነታቸው በተጨማሪም የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን የማገገሚያ ጊዜን በማስመልከት በሰጡት አስተያየት፥ ቅዱስነታቸው እጅግ አስፈላጊ በሆኑ የቤተ ክርስቲያን ጉዳዮች ላይ መሥራት እንደሚቀጥሉ ገልጸው፥ ነገር ግን የዕረፍት ጊዜም እንደሚያስፈልጋቸው ተናግረዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“በዓለም አቀፍ ሰብዓዊነት ሕግ ላይ ስልታዊ ጥሰት እየተፈጸመ ነው” ያሉት ብጹዕ ካርዲናል ፒየትሮ ፓሮሊን፥ በዓለም ዙሪያ የተለያዩ ግጭቶች እንደገና መቀስቀሳቸው ቅድስት መንበርን እንደሚያሳስባት ገልጸው፥ በተለይም በቅርቡ እስራኤል በጋዛ ሰርጥ የፈጸመችውን ጥቃትት እንደማሳያ ጠቅሰዋል።

ይህን ተግባር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እሑድ መጋቢት 14/2017 ዓ. ም. ሕክምናቸውን ሲከታተሉ በቆዩበት ጄሜሊ ሆስፒታል ዙሪያ ከተሰበሰቡት ወደ ሦስት ሺህ ከሚጠጉ ምዕመናን ጋር ሆነው ካደረሱት የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት ቀጥለው ባስተላለፉት መልዕክት ማውገዛቸውንም ብፁዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን አስታውሰዋል።

በቅድስት መንበር የእስራኤል ኤምባሲ ሰኞ መጋቢት 15/2017 ዓ. ም. ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በኤክስ ገጹ በኩል በሰጠው ምላሽ፥ “እስራኤል በዓለም አቀፍ ሕግ መሠረት እየሠራች ትገኛለች” ሲል ገልጿል።

በቫቲካን “የረጅም ዕድሜ ጸጋን መቃወም አይገባም” በሚል ርዕስ የሰው ልጅ ረጅም ዕድሜን በማስመልከት በቅዱስ አጎስጢኖስ ማኅበር ገዳማውያን ማዕከል ብፁዕ ካርዲናል ፒየትሮ ፓሮሊን ትናንት ሰኞ ከሰዓት በኋላ በተዘጋጀው ስብሰባ ላይ ተገኝተው እንደተናገሩት፥ “የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጥሪ፥ ሁከት ቆሞ በውይይት የሰላም መንገዶችን መፈለግ እንደሚገባ የሚያሳስብ ነው” ሲሉ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።

በቅርቡ ከዓለም አቀፍ ቀይ መስቀል ማኅበር ጋር መነጋገራቸውን ያስታወሱት ብጹዕ ካርዲናል ፒየትሮ ፓሮሊን፥ ማኅበሩ እጅግ አስቸጋሪ ወቅት ላይ እንደሚገኝ መግለጹን ጠቁመው፥ በሲቪሎች ላይ የቦምብ ጥቃት መፈጸም እና በዕርዳታ አገልግሎት ሠራተኞች ላይም ግድያ መፈጸም፥ እነዚህ ድርጊቶች በሙሉ በትክክል የሰብዓዊነት ሕግን የሚቃረኑ መሆናቸውን፣ እነዚህ የሕግ ጥሰቶች በዚህ ወቅት ከሚከሰቱ ታላላቅ አደጋዎች መካከል እንደሚቆጠሩ ተናግረው፥ “የስባዓዊ ዕርዳታ ሕግ እየተከበረ አይደለም” ሲሉም ገልጸዋል።

የቅዱስነታቸው የጤና ሁኔታን በተመለከተ

ሮም በሚገኝ ጄሜሊ ሆስፒታል ውስጥ ለ 38 ቀናት ሕክምናቸውን ሲከታተሉ ቆይተው በቅርቡ ወደ ሐዋርያዊ መንበራቸው የተመለሱት የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የጤና ሁኔታን የተጠየቁት ካርዲናል ፒየትሮ ፓሮሊን፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በዚህ ወቅት በማገገም ሂደት ላይ እንደሚገኙ ገልጸው፥ ዕረፍትም እንደሚያስፈልጋቸው ተናግረዋል።

የርዕሠ ሊቃነ ጳጳት ፍራንችስኮስ የወደፊት ዕቅዳቸው ምን እንደሚመስል ለመተንበይ ጊዜው ገና እንደሆነ ተናግረው፥ እጅግ አስፈላጊ በሆኑ የቤተ ክርስቲያን ጉዳዮች ላይ መሥራትን እንደሚቀጥሉ፥ ከመጠን በላይ ሸክም እንዳይሆንባቸው በማለት እጅግ አስፈላጊ እና ውሳኔን የሚሹ ጉዳዮች ብቻ ወደ ቅዱስነታቸው ዘንድ እንደሚቀርቡ ተናግረዋል።

ካርዲናል ፓሮሊን ለጉባኤው ያስተላለፉት መልዕክት

የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ፒየትሮ ፓሮሊን፥ “የረጅም ዕድሜ ጸጋን መቃወም አይገባም” በሚል ርዕሥ የሰው ልጅ የሚኖረውን ረጅም ዕድሜን በማስመልከት ቫቲካን በጠራው ስብሰባ ላይ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር፥ “የእርጅና ጉዳይ ከዘመናችን ትላልቅ ፈተናዎች መካከል አንዱ ነው” ሲሉ አጽንኦት ሰጥተው፥ ምክንያቱም የሕክምና ጉዳይ ብቻ ሳይሆን ኢኮኖሚን፣ ባህልን፣ ሥነ-ምግባርን እና መንፈሳዊነትን የሚያጠቃልል፣ መላውን ኅብረተሰብ የሚነካ ጉዳይ ነው” ሲሉ አስገንዝበዋል።

“እርጅናን እንደ ችግር ቆጥሮ በመደበቅ በርካታ ውስንነቶች እና ድክመቶች በሚታይበት ዘመን ላይ ነው እንገኛለን” ብለዋል። ሕይወት የእግዚአብሔር ስጦታ ከሆነ እና በእያንዳንዱ የሕልውና ደረጃ ውስጥ ያለውን እሴት የሚጠብቅ ከሆነ እውነተኛ ሙላት የሚገኘው በዕድሜ ብዛት ሳይሆን ነገር ግን በሰዎች የእርስ በርስ ግንኙነቶች ጥራት፣ ፍቅርን ሰጥቶ ፍቅር መቀበልን፣ በጥልቀት ሲታሰብ ደግሞ የማኅበረሰብ አካል መሆኑን በመዘንጋት ረጅም ዕድሜን ብቻ መመኘት ችግርን ያስከትላል” ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

በዚህ ምክንያት ሳይንሳዊ እና ቴክኖሎጂያዊ ምርምር በሰው ልጅ ሁለንተናዊ ጥቅም፣ ሰብዓዊ ክብር እና የወንድማማችነት አገልግሎት ላይ ያተኮረ እንዲሆን አሳስበዋል። “የረጅም ዕድሜ ጸጋ ለጥቂቶች ብቻ የተሰጠ ልዩ መብት ወይም አዲስ የማኅበራዊ እኩልነት መንገድ ሊሆን አይችልም” በማለት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ያስተላለፉትን መልዕክት ጠቅሰዋል።

የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ፒየትሮ ፓሮሊን በመጨረሻም፥ በወጣቶች እና በአረጋውያን መካከል ያለው ግንኙነት ዓለም አቀፋዊ አንድነትን ለማምጣት እና የግለኝነት ባህልን ለማስወገድ አስፈላጊ እንደሆነም አሳስበዋል።

 

25 Mar 2025, 16:21