MAP

ብጹዕ ካርዲናል ክላውዲዮ ጉጄሮቲ፥ ብጹዕ ካርዲናል ክላውዲዮ ጉጄሮቲ፥ 

ካርዲናል ጉጄሮቲ፥ የቅድስት ሀገር ክርስቲያኖች የዕርዳታን እጅ በመጠበቅ ላይ እንደሚገኙ አስታወቁ

በጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት የምሥራቅ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያናት አስተባባሪ የሆኑት ብጹዕ ካርዲናል ክላውዲዮ ጉጄሮቲ፥ “የቅድስት ሀገር ክርስቲያኖች የዕርዳታ እጆችን በመጠበቅ ላይ እንደሚገኙ አስታወቁ። እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በመጭው የሕማማት ሳምንት ከሚከበረው ስቅለተ ዓርብ ቀደም ብሎ ከመላዋ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ምዕመናን የሚሰበሰብ ዕርዳታ ሙሉ በሙሉ ለቅድስት ሀገር ክርስቲያኖች እንዲውል በማሳሰብ ወደ ሰላም የሚያደርስ ውይይት እንዲደረግም ጥሪ አቅርበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በቅድስት መንበር የምሥራቅ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያናት ዋና አስተባባሪ ብጹዕ ካርዲናል ክላውዲዮ ጉጄሮቲ የዘንድሮው የስቅለት ዓርብ የዕርዳታ ማሰባሰብ አስፈላጊነትን ለመግለጽ መጋቢት 8/2017 ዓ. ም. ለብጹዓን ጳጳሳት በላኩት መልዕክታቸው፥ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በአመፅ እና በግጭት ምክንያት ቅድስት ሀገርን የጎዳትን ለቅሶ፣ ተስፋ መቁረጥ እና ውድመት አስታውሰዋል።

ብፁዕ ካርዲናል ክላውዲዮ ጉጄሮቲ የዕርዳታ ጥሪ መልዕክታቸውን ካስተላለፉ በኋላ ከቫቲካን መገናኛ ብዙኃን ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፥ “ይህ ለቅድስት አገር ክርስቲያኖች ያቀረቡት የዕርዳታ ጥሪ በአካባቢው አገራት ውስጥ በሕዝቦች ላይ የደረሰውን ውርደት በአስቸኳይ እንዲያስወግድ፣ እንደ ግል ንብረት ተቆጥሮ ዝርፊያ የተፈጸመበት የሕዝብ መሬት ለሕዝብ እንዲመለስ በማለት ተማጽነዋል

እውነተኛ እና ትርጉም ያለው ውይይት እንደገና እንዲደረግ በማድረግ አስፈላጊነት ላይ በማሰላሰል፣ “አንዳንድ ጊዜ ውይይት ማድረግ እጅግ ከባድ ቢሆንም ነገር ግን ሕይወትን እንደሚያድን እና እርስ በርስ ወደ መከባበር ሊያደርስ እንደሚችል አስረድተዋል።

ዓለም ዝም ብትልም ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ዝም አላሉም

ብፁዕ ካርዲናል ጉጄሮቲ በጋዛ፣ በዌስት ባንክ፣ በሶርያ እና በሊባኖስ እየተከሰቱ ያሉ ቀውሶች፣ እንዲሁም በዩክሬን፣ በአፍሪካ እና በኤዥያ ያሉ ግጭቶችን በመጥቀስ ሰላም የሚገኘው የጥቂቶችን ፍላጎት ብቻ በሚያረጋግጥ ወታደራዊ ሃይል እንደማይሆን አስምረውበታል። በእነዚህ ሁሉ ጉዳዮች ላይ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለሰላም ጠንካራ ድምጽ እንደሆኑ ጠቁመዋል።

ቅዱስነታቸው በቅርቡ ባደረባቸው ሕመም ምክንያት ድምጻቸው አለመሰማቱ የሚያስፈራ እና የሚያጽናና እንደሆነ ከብዙዎች መስማታቸውን የተናገሩት ካርዲናል ጉጄሮቲ፥ “ቅዱስነታቸው ዝም ሲሉ ዓለምም ዝም ይላል” ብለዋል። ድምጻቸው ስለ ሰው ክብር የሚናገር ስለሆነ ዝም በሚሉበት ጊዜ ሌላ ድምጽ አይሰማም ብለዋል።

የሰብዓዊ ክብርን መጠበቅ

ቤተ ክርስቲያን ዘወትር የሕይወትን ቅድስናን ለመጠበቅ ቁርጠኛ መሆኗን የገለጹት ብፁዕ ካርዲናል ጉጄሮቲ፥ ይህ ዛሬ ይበልጥ ቅድሚያ የሚሰጠው እና አንገብጋቢ ጉዳይ ነው ሲሉ አስረድተዋል።

ከቅድስት ሀገር ተንከባካቢ ጽ/ቤት የወጣው ዘገባ እንደሚያመለክተው፥ ለችግር የተጋለጡ ወገኖቻችን ለመርዳት በሚያስች አስቸኳይ ዕርዳታ ላይ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት እንደሚገባ አሳስቦ፣ ለቅድስት ሀገር ታቅደው የነበሩ በርካታ ፕሮጀክቶች መቀነሳቸውን፣ መዘገይታቸውን፣ መታገዳቸውን ወይም መሰረዛቸውን አስታውቋል።

እንቅልፍ የሚያሳጣ ኢ-ሰብአዊነት

ከቅድስት ሀገር በሚወጡ እንቅልፍ በሚነሱ ምስሎች ላይ ያስተነተኑት ብፁዕ ካርዲናል ጉጄሮቲ፥ እየሆነ ያለው ኢ-ሰብአዊ ድርጊት ነው” ሲሉ ገልጸዋል።

ከዚህም ጋር ከቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳስ ቅዱስ ጳውሎስ ስድስተኛ ጊዜ ጀምሮ የነበረውን የስቅለተ ዓርብ ዕለት የዕርዳታ ማሰባሰብ ተነሳሽነት አስፈላጊነት በድጋሚ አረጋግጠው፥ የተሰበሰበው የዕርዳታ ሃብት ሳይበታተን ለቅድስት ሀገር ሐዋርያዊ እና ማኅበራዊ አገልግሎት እንዲውል በመልዕክታቸው ማሳሰባቸውን ገልጸዋል።

የቤተ ክርስቲያን ድምጽ

ብፁዕ ካርዲናል ጉጄሮቲ ዕርዳታው በተለምዶ ቅዱሳን ቦታዎችን ለመንከባከብ ያለመ ቢሆንም አሁን ግን ዋናው ጉዳይ የክርስቲያን ማኅበረሰቦችን መጠበቅ እንደሆነ አስረድተዋል።

“የኢየሱስ ክርስቶስን መዓዛ የተሸከሙትን አገሮች ትተው ክርስቲያኖች ለስደት እንዲጋለጡ መፍቀድ አንችልም” በማለት ተናግረዋል። “እነዚህ ሰዎች ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ያልተቋረጠ ግንኙነት ያላቸው ህያው ምስክሮች ናቸው፣ ድምፃችንን የምናሰማው በሰብዓዊነት ምክንያት ብቻ አይደለም” ሲሉ ተናግረው፥ በእርግጥ ቤተ ክርስቲያን ድምጿን የምታሰማው ለሚሰቃዩት፣ ለደከሙት እና ለተገለሉት ጭምር መሆኑን አስረድተዋል።

የተሻለ ዓለም እንዳለ ማመን

በቅድስት አገር የቀጠለው ብጥብጥ በነጋዲያ ላይ አስከፊ ተጽእኖ ማሳደሩን የገለጹት ብፁዕ ካርዲናል ጉጄሮቲ፥ መንፈሳዊ ንግደት ምእመናን የተቀደሱ ቦታዎችን እና የእግዚአብሔርን በምድር ላይ መገኘት እንዲለማመዱ እንደሚያስችላቸው፥ በዛሬው ዘመን የሚደረጉ መንፈሳዊ ንግደቶች ተጨማሪ ትርጉም እንዳላቸው፥ ይኸውም በፍትሕ መጓደል ለሚሠቃዩ ሰዎች ምስክርነትን እና አጋርነትን ማሳየት እንደሆነ አስረድተዋል።ብፁዕ ካርዲናል ጉጄሮቲ በርካታ የምሥራቅ ቤተ ክርስቲያን ምዕመናን በጦርነት እና በድህነት ምክንያት ለኢዮቤልዩ ወደ ሮም መሄድ እንደማይችሉ ገልጸዋል።

“እኛ ክርስቲያኖች የተሻለው ዓለም ትንቢት እናምናለን፤ እንደሚመጣ እርግጠኞች ነን፤ ነገር ግን በተቻለ መጠን አስቀድመን የመጠበቅ ግዴታ አለብን። ኃጢአትን ማሸነፍ አለብን፤ እነዚህ መከራዎች በሙሉ  ማኅበራዊ ኃጢአቶች ብቻ ሳይሆኑ ፖለቲካዊ ጉዳዮችም ጭምር ናቸው” ሲሉ አስገንዝበዋል።

 

26 Mar 2025, 15:26