MAP

በቅዱስ አንድሬያ ዴላ ቫሌ ባዚሊካ ውስጥ የቀረበ የመስዋዕተ ቅዳሴ ሥነ-ሥርዓት በቅዱስ አንድሬያ ዴላ ቫሌ ባዚሊካ ውስጥ የቀረበ የመስዋዕተ ቅዳሴ ሥነ-ሥርዓት  (VATICAN MEDIA Divisione Foto)

ሊቀ ጳጳስ አቡነ ፊዚኬላ፥ የእግዚአብሔር ምሕረት ሕይወታችንን እንደሚያስተካክለው ገለጹ

በቅድስት መንበር የስብከተ ወንጌል አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት አስተባባሪ ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ሪኖ ፊዚኬላ፥ የላቲን ሥርዓተ አምልኮን በምትከተል ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ዘንድ በዐብይ ጾም አራተኛው እሑድ በቀረበውን መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ፥ የእግዚአብሔር ምሕረት ሕይወታችንን እንደሚያስተካክለው ገልጸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ሊቀ ጳጳስ አቡነ ሪኖ ፊዚኬላ በማዕከላዊ ሮም በሚገኘው በቅዱስ አንድሬያ ዴላ ቫሌ ባዚሊካ ውስጥ ከምሕረት ሚሲዮናውያን ማኅበር አባላት ጋር ባሳረጉት የኢዮቤልዩ ዓመት መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ የአባካኙን ልጅ ምሳሌ መሠረት በማድረግ ባሰሙት ስብከት፥ ማንም ሰው ከእግዚአብሔር ቤት ውጭ መኖር እንደማይችል እና በዚህም እያንዳንዳችን የእግዚአብሔር ፍቅር ምን ያህል ታላቅ እንደሆነ ልንገነዘብ እንችላለን” ብለዋል።

የጠፋው ልጅ ምሳሌ “እያንዳንዳችን የእግዚአብሔር ፍቅር ምን ያህል ታላቅ እንደሆነ ለማወቅ በኢየሱስ ክርስቶስ ተገልጧል” ሲሉ አስገንዝበው፥ ከዚህም በላይ ያ ፍቅር ከኛ ፍቅር እጅግ የተለየ እንደሆነ እና ወደ ምስጢሩ ጥልቀት ለመግባት እና የእርሱን የማስታረቅ ጸጋን እንዲሰጠን በውስጣችን ልንቀበለው ይገባል ብለዋል።

የጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤቱ አስተባባሪ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ሪኖ ፊዚኬላ ይህን የገለጹት እሑድ መጋቢት 21/2017 ዓ. ም. የዐብይ ጾም አራተኛው እሑድ በማስመልከት ባሰሙት ስብከታቸው እንደነበር ታውቋል።

ከአባቱ ዘንድ የራቀ ልጅ ውድቀት

በሉቃስ ወንጌል ምዕ. 15 ላይ በተነገረው ምሳሌ ላይ በማስተንተን በቅዱስ አንድሬያ ዴላ ቫሌ ባዚሊካ ውስጥ ለተሰበሰቡት ሚስዮናውያን እና ምእመናን ስብከታቸውን ያሰሙት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ፊዚኬላ፥ “ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔርን ፍቅር እና ምሕረት በማስመልከት በሰብዓዊ ቃል እና ባሕርይ የበለጠ ትርጉም መስጠት እንደማይችል ገልጸው፥

በራሳችን እና በሁለቱ ወንድ ልጆቻች መካከል ያለውን የጋራ ባህሪያትን እንድናገኝ አግዘውን፥ “በውድቀታችን ምክንያት እንደ መጀመሪያው ልጅ ይዋል ይደር ሁላችንም ድርሻችንን እንጠይቃለን፣ ነጻ ለመሆንም የራሳችንን ህልውና መቆጣጠር እንፈልጋለን” ብለው፥ ከእግዚአብሔር ቤት እና ከቤተ ክርስቲያን በመራቅ “ከንቱ ሥራን እንድንሠራ፣ ከንቱ ሐሳብን እንድናስብ፣ ከፍቅር ምንጭ ርቀን እንድንሰቃይ የሚያደርግንን መንገድ እንከተላለን” ሲሉ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ሪኖ ፊዚኬላ አስገንዝበዋል።

የወንድሙ ኃጢአት ለእግዚአብሔር ቅርብ ነው!

“የሁለተኛው ልጅ ታሪክ ከሁላችንም ታሪክ ጋር ተመሳሳይነት ያለው ነው” ያሉት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ፊዚኬላ፣ ወንድሙ ከሄደበት ሲመለስ በቁጣ እና በንዴት ምላሽ እንደሰጠው አስታውሰው፥ እንደ ታላቅ ወንድሙ ለዓመታት ያህል በታማኝነት ማገልገላችን፣ የአገልግሎት ዋጋ ቢስነት እና ግራ መጋባት በእግዚአብሔር ላይ እንድናምጽ ሊያደርገን ይችላል” ሲሉ አስረድተዋል።

“ልጄ ሆይ! አንተ ሁልጊዜ ከእኔ ጋር ነህ፤ የእኔም የሆነው ሁሉ የአንተ ነው” የሚለው የእግዚአብሔር ምላሽ የኛን ኃጢአት ግልጽ እንደሚያደርገው በማስረዳት፥ “ወደ አምላክ መቅረብ ያለውን ጠቀሜታ አንረዳውም” ሲሉ ሊቀ ጳጳሱ አቡነ ፊዚኬላ ተናግረዋል።

ከእግዚአብሔር ጋር የመሆንን ጸጋ ማወቅ

ሊቀ ጳጳስ አቡነ ፊዚኬላ ለካህናቱ ባደረጉት ንግግር፥ “አገልግሎታችንን ስንለመደው ሁሉም ነገር ተደጋጋሚ ስለሚሆን ከእግዚአብሔር ጋር የመገናኘት ስሜትን ማጣጣም አንችልም” ብለዋል።

አክለውም “በየቀኑ ከእርሱ ጋር እንድንሆን ጸጋ እንደተሰጠን የምናውቅ ከሆነ፥ ክህነት የአብ ፍቅር የሚገለጽበት እና ስለዚህም የተጠራነው ሁሉን ነገር ከእርሱ ጋር ለመካፈል በአምላክ እንድንጸና ነው” ብለዋል።

የራቀውን ልጅ ለማግኘት መሄድ

በቅድስት መንበር የስብከተ ወንጌል አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት አስተባባሪ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ሪኖ ፊዚኬላ፥ በጠፋው ልጅ ምሳሌ ላይ ሁሉም ሰው የእግዚአብሔርን አባታዊ ስሜት እንዲያውቅ እና “በክርስቲያን ማኅበር ውስጥ በሩቅ እና በቅርብ የሚገኙት መኖራቸውን በፍጥነት ማየት እንዲችል ጥሪ አቅርበው፥ “ወደ እኛ የሚቀርቡትን ለመቀበል ልባችንን እና አእምሯችንን በመክፈት አጭር አስተሳሰብን እና ባህሪን መተው አለብን” በማለት አሳስበዋል።

“በምሳሌው ውስጥ አባት ጠፍቶ የተገኘውን ልጅ ለመቀበል እንደሮጠ ሁሉ፥ ካኅንም በኑዛዜ መቀበያ ቦታ ብቻ ሳይቀመጥ ነገር ግን አንድ ምዕመን ገና ሩቅ ሳለ እንዴት ማግኘት እንዳለበት ማወቅ ይኖርብታል” ሲሉ አሳስበው፥ አንድ ሰው ኃጢአት በሠራው ልጅ አማካይነት፥ ፍቅር ኃጢአትን እንደሚረሳ እና ይቅርታ ወደ ፊት እንድንመለከት እንደሚያስገድደን ሊያውቅ እንደሚችል ጠቁመዋል።

ማንም ከእግዚአብሔር ቤት ውጭ ሊሆን አይችልም

ሊቀ ጳጳስ አቡነ ፊዚኬላ አባት ለሁለተኛው ልጅ ያለውን ትዕግሥት ገልጸው፥ በመገሠጽ ሳይሆን ነገር ግንፍቅር ሕይወትን እንደሚለውጥ፣ ይቅርታ ወደ አዲስ ሕይወት እንደሚመልስ መገንዘብ እና ያለንን ለሌሎች ማካፈል የልግስና ፍሬ መሆኑን አስታውሰዋል።

በቅድስት መንበር የስብከተ ወንጌል አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት አስተባባሪ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ሪኖ ፊዚኬላ ስብከታቸውን ሲያጠቃልሉ፥ “ሁለቱ ልጆች ወንድማማቾች መሆናቸውን ተገንዝበው ወደ አባታቸው ቤት እንደገና አብረው እንዲገቡ፥ አንድ ላይ በመሆን ብቻ የአባትን ፍቅር ታላቅነት ማወቅ እንደሚችል እና ማንም ሰው ከእግዚአብሔር ቤት ውጭ ሊሆን እንደማይችል፥ ከእግዚአብሔር ቤት ውጭ መሆን ወደ ትርጉም የለሽነት ሕይወት እንደሚመራ እና ሙሉ እርቅ እያንዳንዱ ወንድም ማንነቱን እንደገና እንዲያውቅ ያስችለዋል” ሲሉ አስረድተዋል።

የምሕረት ሚስዮናውያን ልዩ የእርቅ መሣሪያዎች ናቸው

“የምሕረት ሚስዮናውያን ልዩ የእርቅ መሣሪያዎች ናቸው ያሉት” ሊቀ ጳጳስ አቡነ ሪኖ ፊዚኬላ፥ ኢየሱስ ክርስቶስ በምሳሌው እንደገለጸው፥ “የእግዚአብሔር ፍቅር ምን ያህል ታላቅ እነደሆነ፣ ከእኛ ፍቅር የተለየ ነው” በማለት ሁሉንም የምሕረት ሚስዮናውያንን ተግባራቸውን አስታውሰዋቸዋል።

ከዚህም በላይ ቅዱስ ቁርባን የይቅርታ ምንጭ እና በእግዚአብሔር አብ የተጠየቀው ግብዣ እንደሆነ፣ እውነተኛ እና ፍጹም እርቅ የተገኘበት የኢየሱስ ክርስቶስ መስዋዕትነት ከፍተኛ መገለጫ መሆኑን አስገንዝበዋል። በዚህም መሠረት የማስታረቅ አገልግሎት የእምነታችንን ምስጢር በሙላት ለመግለጽ ቅዱስ ቁርባን አስፈላጊ ነው ሲሉ አጽንዖት ሰጥተዋል።

እሁድ መጋቢት 21/2017 ዓ. ም. ከሰዓት በኋላ ሚስዮናውያንን እና በዝግጅቱ ላይ ለመገኘት ለሚፈልግ ማንኛውም ሰው ተከታታይ አምስተኛ ዙር የኢዮቤልዩ ዓመት ኮንሴርት መቅረቡ ታውቋል።ለጣሊያናዊው የሙዚቃ አቀናባሪ ኤንዮ ሞሪኮን መታሰቢያ ይሆን ዘንድ በሮማ ሲንፎኒ ኦርኬስትራ፣ በአዲሱ የሮማኖ ሲንፎኒ እና በሮማ የቶር ቬርጋታ ዩኒቨርሲቲ መዘምራን የተዘጋጀ ነፃ የኮንሴርት ዝግጅት ቀርቧል።

 

31 Mar 2025, 16:23